2022-08-24 07:46:06
እርሱ መሪያችን ነው
አምላካችን ራሱ በሰጠን የተስፋ ቃል “አስተምርሃለሁ፣ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፡ አይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ” ይለናል።
በአለማችን ከምናየው የእውቀት ፍንዳታና የመረጃ ጎርፍ ጋራ ተያይዞ ትክክለኛውን ትምህርትና ምሪት ማግኘት እጅግ አዳጋች እየሆነ መጥቶአል። እውነት አንጻራዊ ሆኖ፣ ጥርጣሬና ግራ መጋባት የምርምር መደምደሚያ ሲሆኑ ስናይ፣ በእርግጥም ሁሉን በሚያውቀው አምላክ መመራት እጅግ የከበረ እድል ነው። የእርሱ እውቀት የማይመረመር ጥልቅ ሲሆን የመጀመሪያውን ከመጨረሻው ማየት የሚችል አምላክ ስለሆነ ከእርሱ የምናገኘው ትምህርት ዘላለማዊ ዋጋ ያለው የከበረ እንቁ ነው።
ታዲያ ይህ አምላካችን በክፍል ውስጥ መጥቶ መረጃን አካፍሎ እንደሚሄድ አስተማሪ ሳይሆን፣ ደግሞ ባስተማረን በዚያ ህይወታችን መመራት ይችል ዘንድ በምንሄድበት መንገድ የሚመራንም መልካም እረኛ ነው። ከፊታችን ቀድሞ የሚወጣ፣ በመልካም አርአያነት ዱካውን ከፊታችን በማስቀመጥ ጎዳናችንን የሚያቀና ታማኝ መሪያችን ነው። እርሱን ልንከተለው ብንፈቅ “ከእኔ ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሁትን ነኝ” ሲለን እንሰማዋለን።
በመንገዳችን በሚገጥመን በማንኛውም አደናጋጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነን አይኖቻችንን ወደ እርሱ ስናነሳ ደግሞ “አይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ” ካለው ጌታ ጋር አይን ለአይን እንገጣጠማለን። እርሱም ትክክለኛውን አቅጣጫ ይጠቁመናል። ወቅታዊና ገጣሚ የሆነ ምሪት ይሰጠናል።
“ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዘወር ብትል ጆሮህ ከኋላህ፣ “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” የሚል ድምፅ ይሰማል።” ኢሳ 30:21።
ይህንን ድንቅ የሆነ የእግዚአብሔርን ምሪት ለማግኘት ቅዱስና ህያው የሆነውን ቃሉን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ልናነብ ይገባናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ኮከብ ቆጣሪ (ሆሮስኮፕ) ዛሬ “ይሄ ይገጥምሃል፣ እንዲህ ትሆናለህ፣…” የሚል መረጃ የለውም፤ ነገር ግን ህይወታችን ሊመራበት የሚገባውን መለኮታዊ መርህ ያስተምረናል። መርሆዎቹን ወደ ህይወታችን ዝርዝር ጉዳዮች ለመተርጎም እንድንችል ደግሞ በጸሎት በፊቱ ስንቀርብ መንፈስ ቅዱስ ለመንፈሳችን በመመስከር ልባችን የሚያርፍበትን ውሳኔ እንድንወስን ይረዳናል።
እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ውሳኝ እውነታ እግዚአብሔር የሚመራን ከሆነ መንገዳችን አልጋ ባልጋ ይሆናል ማለት እንዳልሆነ ነው።
አብርሃምን ታላቅ ተስፋ አሰንቆ ከተወለደበት ምድር ሲያወጣው በመንገዱ ላይ ረሃብና ሌሎችም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥመውት ነበር።
ዮሴፍ ገና በልጅነት ያየው ህልም ከከፍታ ላይ ጉብ አድርጎት የነበረም ቢሆን ከዚያ ጫፍ ለመድረስ ግን በባርነትና በእስርቤት ሸለቆ ውስጥ ማለፍ ነበረበት።
እስራኤላውያን ከግብጽ ወጥተው ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከንአን ለመድረስ የሄዱበት መንገድ በብዙ ተግዳሮቶች የተሞላ ነበር።
ዳዊት በጎቹን ከሚጠብቅበት ሜዳ ተጠርቶ ለንጉስነት ቢቀባም በዙፋኑ ላይ ከመቀመጡ በፊት “በእኔና በሞት መካከል እንድ ስንዝር ቀረ” እስከሚል ድረስ በከባድ መከራ ውስጥ አልፎ ነበር።
የጌታችን ደቀ መዛሙርትም “መንገድ እውነትና ህይወት”የሆነው ኢየሱስን በመከተል በተጓዙት ጎዳና ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል።
ይሁን እንጂ እነዚህና ሌሎች ብዙ ምሳሌዎችን ስንመለከት ጌታችን ልጆቹን በመንገዳቸው በሚገጥማቸው ነገር ሁሉ እየመራ የሚያሻግር፣ እርሱ ካሰበላቸውም ፍጻሜ የሚያደርስ አምላክ መሆኑን እርግጠኞች ሆነን ማመን እንችላለን።
እኛም ዛሬ የእርሱን ምሪት ፍለጋ ወደ እርሱ እንቅረብ፣ እርሱ በሚመራን መንገድ ላይ በሚያጋጥመን ማንኛውም አይነት ችግር አንደናገጥ፣ ይልቁንም አይኖቹን በእኛ ላይ ወደ አጠናው ጌታ አይኖቻችንን በማንሳት የእርሱን ምሪት እንከተል።
አባት ሆይ፣ ልጆችህን በመምራት እንደ አንተ ያለ ማንም የለምና እናመሰግንሃለን። እኛም ባንተ በመመራት መኖር እንድንችል እርዳን። አሜን
324 views04:46