2023-04-11 10:54:41
https://www.capitalethiopia.com/2023/04/10/will-ethiopia-appease-global-partners/
እየተካሄደ ከሚገኘው የአለም ባንክ/የአለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት የጋራ የፀደይ ወቅት ስብሰባ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በቀጣይ የውጭ ድጋፍ ለማግኘት ከአለምአቀፍ ተቋማት እና አባል አገሮች ጋር ንግግሮችን እንደምታደርግ ይጠበቃል፡፡
ለውይይቱ ውጤታማነት ከኢትዮጵያ መንግስት በአጋሮች እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላት እንደሚጠበቅ ምንጮች ለካፒታል ተናግረዋል፡፡
በዋናነት የሚጠቀሰውም ከሰሜኑ ግጭት ጋር ተያይዞ በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው የሰላም ስምምነት እና መርሆዎቹ እንደሆኑ ነው ምንጮች የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ ከሰሜኑ ግጭት መነሳት ወዲህ ከአጋሮች ምንም ሊባል በሚችል መልኩ ድጋፍ ሳታገኝ ቆይታለች፡፡
አገራት እና ተቋማት በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደር በወሰዱት እርምጃ ቀደም ሲል የተፈቀደ እንዲሁም መለቀቅ ጀምሮ የነበረ የውጭ ድጋፍ በዋናነት መቋረጡ ይታወሳል፡፡ ይህም የመንግስትን የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ ከመጉዳት ባለፈ የበጀት ጉድለትን ለመሸፈን ወደ ቀጥታ ብድር እንዲገባ አስገድዶት ነበር፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የአለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሞያዎች በአዲስ አበባ የነበራቸውን ቆይታ ጨርሰው ሲመለሱ ባወጡት መግለጫ ከመንግስት ሃላፊዎች ጋር የነበራቸው ውይይት አመርቂ እንደነበር ጠቅሰው ውይይቱ በተያዘው ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ በአለም ባንክ/የአለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት የጋራ የፀደይ ወቅት ስብሰባ እንደሚቀጥል ጠቅሰው ነበር፡፡
የዚህ ሳምንት ውይይት የተቋማቱ ወሳኝ የሚባሉ አባል አገራት ሹመኞች የሚገኙበት እንደመሆኑ ለኢትዮጵያ በቀጥታ ተገናኝቶ ለመነጋገር መልካም አጋጣሚ ነው ተብሏል፡፡
ጉዳዩን የሚከታተሉ እንደሚናገሩት ለውይይቱ ውጤታማነት በመንግስት በኩል ከሰላም ስምምነቱ ጋር ተያይዞ ቁርጠኛ የፖለቲካ ትግበራ ሂደትን ማሳየት ይጠበቃል ተብሏል፡፡
452 views07:54