2023-05-04 14:19:19
https://www.capitalethiopia.com/2023/05/02/esl-forwards-files-to-nbe-to-acquire-two-gigantic-vessels/
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ/ኢባትሎ ሊገዛ ላቀደው ሁለት ግዙፍ መርከቦች የውጭ ምንዛሬ ፍቃድ ለማግኘት ለብሄራዊ ባንክ ለሁለተኛ ጊዜ የፕሮጀክት ማብራሪያ ሰነድ ማስገባቱን ይፋ አደረገ፡፡
ተቋሙ ላለፉት ከሁለት አመታት ቀደም ለሚል ጊዜ የጭነት አቅማቸው አሁን ካሉት መርከቦች ከፍ የሚሉ ሁለት ሁለገብ መርከቦችን ለመግዛት ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ነበር፡፡
ፕሮጀክት ቀርጾ ሲንቀሳቀስ የቆየው ኢባትሎ የጥናት እና ዝግጅት ምእራፎችን አልፎ እና ጨረታ አውጥቶ ዚያንግዩ የተሰኘ የቻይና ድርጅት ለሁለቱ አልትራማክስ መርከቦች ግንባታ ስራ መምረጡንም አስታውቋል፡፡
በግዥ እቅዱ መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመርከብ ግዥው 70 በመቶ ብድር እንዲያመቻች ከባንኩ ጋር ስምምነት የተደረሰ ሲሆን፤ ክፍያው ግን በውጭ ምንዛሬ እንደመሆኑ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ብሄራዊ ባንክን ማስፈቀድ አስፈልጎ ነበር፡፡
በዚህም መሰረት ኢባትሎ ቀደም ሲል ዝርዝር ሂደቱን የሚያስረዳ ሰነድ ለማእከላዊ ባንኩ አስገብቶ ነበር፡፡
በቅርቡም በድጋሜ በብሄራዊ ባንክ ማብራሪያ እንዳስገቡ የሎጅስቲክ ድርጅቱ ሃላፊዎች ለካፒታል ተናግረዋል፡፡
የመርከብ ግንባታው ሂደት ቢያንስ ሁለት አመት የሚፈጅ ሲሆን ክፍያውም በ5 ዙር የሚከናወን በመሆኑ ለውጭ ምንዛሬ አመዳደብ አመቺ እንደሚሆን የተቋሙ ሃላፊዎች አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ማእከላዊ ባንኩ ጥያቄውን እንደሚቀበል ነው ያላቸውን ተስፋ የገለጹት፡፡
በእቅዱ መሰረት የውጭ ምንዛሬ አመንጭው ተቋም 30 በመቶ የሚሆነውን የመርከብ ግንባታ ወጪ ሚሸፍን ሲሆን የቀረው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚቀርብ ይሆናል፡፡
አዲስ የሚገዙት አልትራማክስ መርከቦች የመጫን አቅማቸው 63 ሺ ቶን እንደሚሆን የሚጠበቅ ሲሆን ይህን አይነት መርከብ ሚባትሎ አስከቅርብ ጊዜ ድረስ ኖሮት አያውቅም፡፡
ኢባትሎ በቅርቡ ከአስር አመት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦቹን ሰባት አመት እድሜ ባላት በአንድ አልትራማክስ መቀየሩ ይታወሳል፡፡
ቅያሬው ከመደረጉ በፊት የሚያስተዳድራቸው መርከቦች የመጫን አቅማቸው 28 ሺ ቶን ግድም ነበር በመሆኑም አዲስ የተቀላቀለችው መርከብ በመጫን አቅሟ ለኢባትሎ አድስ ምእራፍ የምትከፍት ናት፡:
369 views11:19