2022-08-22 12:55:17
ቅዳሴ ማርያም
ቅዳሴ ማርያም በምእመናን እና በካህናት ዘንድ እጅግ ተወዳጅ እና በዚሁ ፆመ ማርያም ወቅት በሁሉም ቀናት የምትቀደስ ቁጥሯ ከአኮቴተ ቀርባን መጽሐፍት ውስጥ ስትሆን ቅዳሴ ጎሥዐ ተብላም ትታወቃለች ምክንያቱም ቅዳሴው በዚሁ ቃል ስለሚጀምር አንዳንድ መጽሐፍት በጀመሩበት ቃል የመጠራት ልምድ አላቸውና ነው።
#ደራሲው #ማን #ነው
ስደራሲዎ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጣሉ እነሱም
፩ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት መጽሐፉ በአባ ሕርያቆስ መደረሱን ሲናገሩ(፩)
፪ መጽሐፉን ያጠኑ የሥነ ድርሳን ሙህራን ወይ በአባ ጊዮርጊስ አልያም ስማቸውን መጥቀስ ባልፈለጉ ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት ተደርሷል ብለው ይናገራሉ ።
#አባ #ሕርያቆስ #ማን #ነው?
በቤተክርስቲያን ውስጥ ታዋቂነት ያለው አባት ሲሆን ከእርሱ ጋር ተያይዞ የሚተረኩ ትውፊቶች አሉ
፩ ቅዱስ ያሬድ ማኅሌታይ በማይ ኪራህ ሳለ እመቤታችን ተገልፃለት ከቅዱስ ኤፍሬም እና ከአባ ሕርያቆስ ጋር ሆኖ እንዳወደሳት ይነገራል (፪)
፪ የታሪኩ መቼት ልክባይሆንም በድርሳነ ዑራኤልም ሌላ ታሪክ ይተረክለታል።
በቅዳሴ ማርያም ብቻ ሳይሆን በላሐ ማርያም ፣በመጽሐፈ ዕርገታ ለማርያም፣በመጽሐፈ ዶርሆ እና በስምዐ ጲላጦስ ድርሰቶቹም ይታወቃል።
የእረፍት በዓሉ የቤተክርስቲናችን ስንክሳር እንደሚነግረን ጥቅምት ፪(2) ሲሆን በግብፅ ባለችው ቤተክርስቲያናችን ባለው ስንክሳር ግን በእለተ ቀኑ ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ ብቻ ያስባል እንጂ በዚያ እለት ይህን አባት አያነሳም።
ምንአልባት በእነርሱ ዘንድ ስሙ ሌላ ሆኖ ይሆን? በእርግጥ ስማቸው ከስንክሳሩ የሌሉ ቅዱሳንን ቤተክርስቲያኒቱ ስለምታከብር የዚህን አባትም ጉዳይ ከእዚያው ጋር አያይዘን ማየት እንችላለን።
ሐገረ ስብከቱ ብሕንሳ ግን በሌላ ስሟ መኑፍ ትባላለች።
ስለ እዚህ አባት ያጠኑ ምሁራን እንዲህ ይላሉ "አባ ሕርያቆስ የኖረበት ዘመን ዐረበኛ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሥርዓተ አምልኮ ቋንቋ ከሆነበት ከ12ኛው ምእት ዓመት በኋላ ነው የሚል አስተያየት የሰጡ ምሁራን አሉ አንዳንዶቹም ዘመኑን ከ14-15ኛው ከፍ አድርገዋል።
ነገርግን በአንዳንድ ጽሑፎች ውስጥ በዘመነ አትናቴዎስ (4ኛው ምእት ዓመት) እንደኖረ ስለተናገረና Sahidic በተሰኘው የኮፕቲክ ቋንቋ የተጻፉ ጽሑፎቹ ስለተገኙ አባ ሕርያቆስ የኖረው በ4ኛው ምእት ዓመት ወይም Conti rossni በመጽሐፈ አክሱም እንደነገረን በ6ኛው ምእት ዓመት ነበር ወደሚል ድምዳሜ ተደረሷል"(፫)
ቅዳሴ ማርያም በቤተክርስቲያናችን ትውፊት መሰረት ከጥንትም ጀምሮ በአባ ሕርያቆስ ስም ነው የሚጠራው (ባለቤትነቱን ለአባ ሕርያቆስ ነው የሚሰጠው።)
ለዚህም ገድለ አቡነ ዳንኤል ዘገርዓልታን መጥቀስ ይቻላል።
#የቅዳሴ #ማርያም #ምንጮች
አንድ ጽሑፍ ሲጻፍ ምንጭ አለው በተለይም የቤተክርስቲያን መጽሐፍት መገለጫቸው የቤተክርስቲያንን ቅዱስ ሕያው ትውፊት በየትውልዱ ሁሉ ማስቀጣላቸው እና በምእመናን ኅሊና መሳል ነው።
በዚህ ረገድ ይህ መጽሐፍ ቤተክርስቲያን ለአስተምህሮዋ መጽሐፍ ቅዱስን ቅዱስ ትውፊትን ቅዱሳን ሊቃውንት አበውን...እንደምትጠቀም ሁሉ ይህ ድርሳንም መጽሐፍ ቅዱስን በምንጭነት ይጠቀማል መነሻውን ከመዝሙር ፵፭(45) አድርጎ ይነሳል እያንዳንዱን ክፍል ከመረመርን በመጽሐፍ ቅዱስ ውኃነት የለመለመ ተክል ሁኖ እናገኘዋለን እንዲሁም መጽሐፈ ቀሌምንጦስን አበው ስለ ድንግል ማርያም ስብዕና እና የቅድስና ሕይወቷ ከጻፉት ድርሳናት ምንጭ አድርጓል(በዚህም ከProtovangelium of james ቅዱስ አትናቴዎስ ቅዱስ አምብሮስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሊቁ አርጌንስ እና ሌሎች አበው ሊቃውንት ስለ እርሷ ስብዕና ጽፈዋል) እናም የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ከእነዚህ አበው ድርሳናት ተጠቅሟል እንዲሁም ሌሎች አበው ሌሎች ስለ እመቤታችን እና ነገረ መለኮት የተነገሩ የተጻፉ ትውፊቶችን ተጠቅሟል።
#ይዘቱ
ቅዳሴ አንዱ የቤተክርስቲያን የአስተምህሮ ምንጭ ነውና እንዲሁም ቤተክርስቲያን የምታምነውን ትጸልያለችና ቤተክርስቲያን ስለ ድንግል ማርያም ያላትኔ ክብር (Veneration of the virgin mary) እና አስተምህሮ እንዲሁም አጠቃላይ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮዎች ስለ ነገረሥላሴ ስለ ነገረሥጋዌ ስለ ሚስጢራተ ቤተክርስቲያን ልቡናን ንፁህ ስለማድረግ እና ስለሌሎች ጉዳዮች ያለውን የቤተክርስቲያን አቋም እና ዶግማ ቅዳሴ ሕያው ወንጌል ነውና ስለእነዚህ ሁሉ ይህ ድርሳን ያስተምራል ይመሰክራል።
በረከተ ማርያም ድንግል ይደርብን
በረከተ አባ ሕርያቆስ ይደርብን !
ማጣቀሻዎች
፩ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ገፅ፩ -፲(1-10
፪ ዝኒ ከማሁ
፫ ድርሳነ ዑራኤል ዘጥር
፬ ቀሲስ ዶክተር መብራቱ ኪሮስ አኮቴተ ቁርባን ገፅ ፫፻፴፯ (237)
፭ገድለ አቡነ ዳንኤል ዘገርዓልታ ዘወርኃ ሐምሌ
4.0K views09:55