Get Mystery Box with random crypto!

AfandishaHarar 🇪🇷🇪🇹🇯🇴🇸🇩🇪🇭🇸🇴

የቴሌግራም ቻናል አርማ afandishaharar — AfandishaHarar 🇪🇷🇪🇹🇯🇴🇸🇩🇪🇭🇸🇴 A
የቴሌግራም ቻናል አርማ afandishaharar — AfandishaHarar 🇪🇷🇪🇹🇯🇴🇸🇩🇪🇭🇸🇴
የሰርጥ አድራሻ: @afandishaharar
ምድቦች: ያልተመደበ
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 12.31K
የሰርጥ መግለጫ

Spreading Ethnographic and Historical Truth.

Ratings & Reviews

3.33

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

1

4 stars

1

3 stars

0

2 stars

0

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 2

2022-08-27 06:11:20 ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው።
ጦርነት ከውድመት በቀር ምንም ትርፍ የለውም
2.6K viewsedited  03:11
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-26 21:04:43 “ላታመልጪኝ፣ አታሩጪኝ”
-----
አፈንዲ ሙተቂ
------
በልጅነታችን ብስኩትና ፓስቲ እየገመጥን ከቦረቅንባቸው ሻይ ቤቶች መካከል ብዙዎቹ አሁንም አሉ፡፡ ይሁንና የድሮ ገጽታቸው ዛሬ የለም፡፡ የቀለም ቅባቸውም ሆነ ውስጣዊ ገጽታቸው ተቀይሯል፡፡ በተለይ በግድግዳዎቻቸው ላይ ሲታዩ የነበሩት ስዕሎች ለቻይና ሰራሽ ማሸብረቂያዎችና ለእግር ኳስ ከዋክብት ፖስተሮች ቦታቸውን ለቀዋል፡፡

ድሮ በነዚህ ሻይ ቤቶች ውስጥ የሚታየው ዝነኛ ስዕል የትኛው እንደነበረ ተውቃላችሁ?… “ላታመልጪኝ አታሩጪኝ” የሚል ርዕስ የነበረው ስዕል ነው፡፡ ይኸውም አያ ነብሮ ሚዳቆን ካባረረ በኋላ “ለቀም” አድርጎ የሚይዝበትን ትዕይንት የሚያሳይ ነው፡፡ ነብሮ አጠገቧ ደርሶ ሁለት እግሮቹን በሽንጧ ላይ ካሳረፈ በኋላ ነው እንደዚያ የሚላት፡፡ ሚዳቆዋ ምን እንደተነፈሰች ስዕሉ አይገልጽም፡፡( ያው እንደፈረደባት “ሜሜሜመሜሜ!!”…. እያለች እንደምትጮህ የታወቀ ነው)፡፡

በደራሲ ጋሽ መስፍን ኃብተማሪያም ላይ ያለኝ ቅሬታ ይህ ነው፡፡ ጋሽ መስፍን “የቡና ቤት ስዕሎች” ብሎ በቡና ቤት ግድግዳ ላይ የሚሳሉ ስዕሎችን አብጠርጥሮ እንዳላወጋን ሁሉ ከቡና ቤቶች ጋር ብዙ ቁርኝት ለሌለን ሰዎች መጽናኛ የምትሆን “የሻይ ቤት ስዕሎች” የተሰኘ ወግ ሳይጽፍልን ሄዷል፡፡ "መቼስ ማል ጎደኒ አለ" የሀረርጌ ሰው!
-----
በገለምሶ ሻይ ቤቶች በራፍ ላይ የተሰቀሉ የሻይ ቤት ስም ማስታወቂያዎች በሌሎች ቦታዎች ከምታውቋቸው ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ይሁንና የአንደኛው ሻይ ቤት ስም የተጻፈበት ሁኔታ በሌሎች አካባቢዎች ከሚታወቁት በጣም ይለያል፡፡ ስያሜው የተጻፈውም በሚከተለው አኳኋን ነው፡

“መስራት የማግኘት ምንጭ መሆኑን ማወቅ መቻል ያስፈልጋል፡፡
የወይዘሮ አሰገደች ኃ/ማሪያም ሻይ ቤት፡፡”

ደስ ይላል አይደል?…. ይህ ሻይ ቤት ዛሬ የለም፡፡ በቦታው የቻይና አልባሳትን የሚቸረችር ቡቲክ ቆሟል፡፡ እንዲያው ይህቺ ቻይና ታሪክ ማበላሸት ብቻ ነው እንዴ ነገረ ስራዋ?… ግድ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲነቃባት ዋጋዋን ይከፍላታል (“ቻይናን የምንመርጠው የሰብዓዊ መብት ምናምን እያለች ስለማታስጨንቀን ነው” አሉ ወዳጆቿ… ቂቂቂቂቂ ... የኛ ጎምቱ ባለቅኔ የሆነው ገሞራው የጻፈባትን አልሰሙም ማለት ነው)፡፡
--------
አፈንዲ ሙተቂ
ሚያዚያ 20/2006
2.8K views18:04
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-25 22:39:44
የሁለት ሙሉጌታዎች ወግ
-------
አፈንዲ ሙተቂ
-------
ድምጻዊ አበበ ተካ በ1988 የኢትዮጵያ ከተሞችን የነቀነቀ አንድ አልበም መልቀቁ ይታወሳል። በዚያ አልበም ከተካተቱት ዘፈኖች መካከል የሙዚቃ አፍቃሪዎችን ከዳር እስከ ዳር ያነጋገረው"ሰው ጥሩ" የሚል ርእስ ያለው ዜማ ነው። አቤ ዘፈኑን በግንቦት ወር 1988 በተካሄደ ሀገር አቀፍ የሙዚቃ ውድድር ላይ አቅርቦት አንደኛ ወጥቶ ተሸልሞበታል።

የዚያን አልበም የሙዚቃ ቅንብር የሰራው ታሪካዊው የጎሃ ምሥራቅ ባንድ ያፈራው ሙሉጌታ አባተ መሆኑን አውቃለሁ። ያ ስራ ለሙሉጌታ ሁለተኛው የአማርኛ አልበም ነው። ከዚያ በፊት ሙሉጌታ የኦሮምኛ አልበሞችን ነው ሲያቀናብር የነበረው።

ታዲያ የአልበሙ አቀናባሪ ሙሉጌታ አባተ መሆኑን ባውቅም ስለዘፈኑ ደራሲ የማውቀው ነገር አልነበረም።
-----
ከትናንት ወዲያ ሙዚቀኛ ሙሉጌታ አባተ "አርሂቡ" ለተሰኘው የኢቴቪ የመዝናኛ ፕሮግራም በታህሳስ ወር 2008 የሰጠውን ቃለ-ምልልስ እያየሁ ነበር። እናም ሙሉጌታ የዘፈኑ ግጥም ደራሲ ባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ እንደሆነ ሲናገር አድናቆትም ንዴትም ያዘኝ።

አድናቆቴ የተነሳብኝ ሙሉጌታ ያንን ዘመን ተሻጋሪ ስራ ስለደረሰ ነው። ንዴቴ የተቀሰቀስው ደግሞ ደራሲው በህይወት እያለ ለዚያ ስራው የሚገባውን እውቅና እና ክብር ያልተሰጠው መሆኑ ነው። ያ ስራ የእርሱ ድርሰት መሆኑን በጭራሽ አላውቅም ነበር። ዛሬም ሙሉጌታ ተስፋዬ በቅኔዎቹ እንጂ በደረሳቸው ብዙ የዘፈን ግጥሞች ትኩረት አላገኘም። ይህ አካሄድ መለወጥ አለበት።
------
ሁለቱ ሙሉጌታዎች በዚህ ወቅት ሁለቱም በሕይወት የሉም። በስራዎቻቸው ግን ዘወትር እናስታውሳቸዋለን።
-----
ፎቶዎቹ:
ሙሉጌታ አባተ (በግራ በኩል)
ሙሉጌታ ተስፋዬ (በቀኝ በኩል)
--------
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 19/2014
2.7K views19:39
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-25 21:42:50 የኒያላ እና የግሥላ ካርቶን ንግድ (1983)
-------
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-------
ወቅቱ የደርግ መንግሥት ፍጻሜ ዋዜማ ነው፡፡ ዕለተ ማክሰኞ፡፡ ገለምሶ እንደ ሁል ጊዜዋ የማክሰኞ ገበያተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ነበረች፡፡ እኔም “አው ሰኢድ” ከሚባለው ሰፈር ካለው የአባቴ መኖሪያ (ድሮ የታወቀ ሱቅ ነበር) ወርጄ ወደ መኖሪያ ቤታችን እየተመለስኩ ነው፡፡ ታዲያ “ኒብራ” በሚባለው የከተማችን አውራ ጎዳና ላይ ያልጠበቅኩት ነገር ገጠመኝ፡፡

“ናሲሮ ሰኢዶ” የሚባለው አብሮ አደግ ጓደኛዬ በየሱቁ እየገባ “የኒያላ ወይም የግሥላ ካርቶን አላችሁ?” እያለ ይጠይቃል፡፡ በእጁ ከሶስት ያላነሱ ካርቶኖችን ይዞ ሌላ ካርቶን መጠየቁ ትንሽ ገረሜታን ፈጠረብኝ፡፡ ምክንያቱም ካርቶን ከአዲስ አበባና ከድሬ ዳዋ የሚመጡ ዕቃዎች ታሽገውበት ወደኛ ከተማ (ገለምሶ) ከመጣ በኋላ አገልግሎቱን እንዳበቃ ነው የሚቆጠረው፡፡ ወደ ሌላ አካባቢ የሚሄድ ጭነት (ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቡና፣ እህል ወዘተ…) የሚታሸገው በጆንያ እንጂ በካርቶን አልነበረም፡፡ ባዶውን ካርቶን የሚፈልጉት “ኩሊ” የሚባሉት የቀን ሰራተኞች አሊያም የቤታቸውን ግማሽ ከፍለው የጥናት ክፍል ሊሰሩበት የሚፈልጉ ተማሪዎች (በተለይ ወደ ሀይስኩል የገቡ)፤ ወይም በካርቶኖ ጊዜያዊ ኮርኒስ ለመስራት የሚፈልጉ አንዳንድ አባወራዎች ናቸው፡፡ “ናሲሮ” ግን ከሶስቱም አልነበረም (ልጁ በወቅቱ ቆንጆ የሆነ የጥናት ቤት ነበረው)፡፡ በዚያ ላይ በእጁ የተመነዘረ ረብጣ ብር ይዟል፡፡ እናም ነገሩን ከርሱ ጠይቄ መረዳት አማረኝና “ለምንድነው ካርቶን የምትገዛው?” አልኩት፡፡
“በጣም ይፈለጋል፤ ወደ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ተወስዶ ይሸጣል”
“ባዶ ካርቶን?”
“አዎን”
“በስንት ነው የምትገዛው?”
“የአንዱ ዋጋ አምስት ብር ነው”
“አምስት ብር ሙሉ?”
“አዎን”
“ሁሉም ዓይነት ካርቶን ይሆናል?”
“አይሆንም፤ የኒያላና የግሥላ ብቻ ነው የሚፈለገው”

ናሲሮ በስራው እንዳግዘው ጠየቀኝ፡፡ “ስንት ትሰጠኛለህ?” አልኩት፡፡ አራት ብር ሊሰጠኝ ቃል ገባልኝ፡፡ እኔም ግብዣውን በደስታ ተቀበልኩት (አራት ብር ዶሮ ከተገዛለት በኋላ እንኳ አንድ ብር ያህል የሚተርፍለት ገንዘብ መሆኑን እያስታወሳችሁ)፡፡
ከናሲሮ ጋር በ“ኒብራ” ጎዳና አንድ ክንፍ ላይ ያሉትን ሱቆች አዳረስን፡፡ አሁን በትክክል የማላስታውሰውን ያህል የኒያላና የግሥላ ካርቶኖችንም ገዛን፡፡ ወደ አስር ሰዓት ገደማም “ፎቶ ማወርዲ” ከሚባለው ፎቶ ቤት አጠገብ ወደሚገኝ መጋዘን ወሰድናቸው፡፡ ከዚያም አራት ብሬን ይዤ ወደ ማክሰኞ ገደማ ላፍ አልኩ፡፡ ዘይቱናና ሸንኮራ እየበላሁ ከናስሮ ጋር የሰራሁትን ገድል ለጓደኞቼ እየቀደድኩላቸው ከቆየሁ በኋላ መሸ፡፡
* * *
በማግስቱ ትምህርት ቤት ሄጄ ስመለስ ከተማው “የኒያላ ካርቶን ያላችሁ….የግሥላ ካርቶን ሽልጡልን” በሚሉ ደላላዎች ተወረሮ አገኘሁት፡፡ “ምን መጣ?” አልኩኝ ለራሴ፡፡ “የሲጋራ ካርቶን ምን ይሰራበታል? ይህንን ያህል ይፈለጋል ማለት ነው?” እያልኩ አሰላሰልኩ፡፡ ነገሩ ይበልጥ የገረመኝ የመግዣ ዋጋው አስር ብር መግባቱን ስሰማ ነው፡፡
“ናሲሮ አታለለኝ ማለት ነው? ለምንድነው የደበቀኝ? እኔ አራት ብሬን ብቻ ከሰጠኝ ከዋጋው ጉዳይ የለኝ! ዋጋውን ለሌላ ሰው እንዳልናገርበት ጠርጥሮኛል ልበል?” እያልኩ በጓደኛዬ አድራጎት ስለፈላሰፍ አንዱ ደላላ ዋጋው በአንድ ቀን ከእጥፍ እንደጨመረ አስረዳኝ፡፡
“እንዴ! ባዶ ካርቶን?”
“አዎን”
“ምን ይሰራበታል ግን?”
“እኔ እንጃ! በጣም ይፈለጋል”

ነገሩ ሀገሬውን በሙሉ ነበር ያስደመመው፡፡ ታዲያ የዕሮብለቱ ሲገርመኝ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዋጋው በእጥፍ ጨመረ፡፡ ባዶ ካርቶን በሀያ ብር! ምክንያቱ ግን ለማንም ግልጽ አልነበረም፡፡

በዚህን ጊዜ ነው ከተሜው በሙሉ ካርቶንን ከያለበት ማሰስ የጀመረው፡፡ “ኩሊዎች” ለንጣፍ የሚጠቀሙበትን አሮጌ ካርቶን ለገበያ አወጡ፡፡ ተማሪዎች ከፍራሽ ስር የሚያነጥፉትን የእርጥበትና የአዋራ መከላከያ ካርቶን እያወጡ የሳምንት በርጫ መግዣ አደረጉት፡፡ ወሬው በየሰፈሩ ተዛመተ፡፡ የጎረምሳና የጎልማሳው የመወያያ ርዕስ “የኒያላ ካርቶን” እና “የግሥላ ካርቶን” ሆነ፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ የካርቶን መግዣ ዋጋው ሀምሳ ብር ደረሰ፡፡ ካርቶንን እንደ ኮርኒስ የሚጠቀመው ቤተሰብ “ኮርኒስ በአፍንጫዬ ይውጣ” እያለ የቤቱን የጣሪያውን መከለያ ፈነቃቀለው፡፡ ዋጋው ወደ ስድሳና ሰባ ብር ሲያሻቅብ የካርቶን ግድግዳዎች ተደረመሱ፡፡ መቶ ብር ሲገባማ በርካታ ነጋዴዎች ቋሚ የካርቶን ገዥዎችና ጫኞች ሆኑ፡፡ ደላሎች እስከ ገጠር እየዘለቁ በየቤቱ የተደበቁትን የኒያላና የግሥላ ካርቶኖች እየገዙ በከፍተኛ ዋጋ ለነጋዴዎች ያቀርቡ ጀመር፡፡

ዋጋው እስከ መቶ ሀያ ብር ደረሰ… ገበያው ጦፈ፡፡ ምድርና ሰው ሁሉ “ካርቶን….ካርቶን” እያለ ቃላት የመላለስ ገባ ይመላለስ ገባ፡፡ የእናቶቸ የቡና ወሬ ካርቶን ሆነ፡፡ ወሬው ከከተማዋ አልፎ በየገጠሩ ተዛመተ፡፡ ጥቂት ነጋዴዎች በካርቶን ንግድ እስከ መቶ ሺህ ብር የሚደርስ ትርፍ እንደዛቁበት ይወራ ጀመር፡፡
* * *
ይህ ኩነት ከሁለት ወራት በላይ የቆየ አይመስለኝም (ምናልባት ሶስት ወር ያህል ቆይቶ ይሆናል)፡፡ ከሚያዚያ ወር መግቢያ በኋላ የከተማችን ነዋሪዎች የመወያያ አጀንዳ ተቀይሮ ከሰሜን ወደ መሀል ሀገር እየገፋ በመጣው የጦርነት ዜና ላይ ሆነ፡፡ የካርቶን ገበያ ሙሉ በሙሉ ባይደርቅም እጅግ በጣም እየቀዘዘ ሄደ፡፡ በሚያዚያ ማብቂያ ገደማ ከነአካቴው ጠፋ፡፡ ከዚያ ወዲህ ስለርሱ ያነሳ ሰው የለም፡፡

“ስንቶች በዚህ ንግድ ከበሩ? ስንቶች በኪሳራ ተሸመደመዱ?” የሚለው እስከ አሁን ድረስ በትክክል የማይታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ ግን “የኒያላ እና የግሥላ ካርቶኖች እስከ መቶ ሀያ ብር በሚደርስ ሂሣብ የተቸበቸቡበት ምክንያት ምንድነው?” የሚለው ነው፡፡
----------
ይህንን ጽሑፍ በፌስቡክ የጻፍኩት የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ገደማ ነበር። በጽሑፉ ላነሳሁት ጥያቄ ትክክለኛ ጥያቄ ያገኘሁት ከዚያ በኋላ ነው።

አዎን! በወቅቱ ካርቶኖቹን የሚሰራው ፋብሪካ ተበላሽቶ ነበር። ፋብሪካው ተጠግኖ ስራ እስኪጀምር ድረስ የሲጋራው አምራች ድርጅት ነጋዴዎች አሮጌ ካርቶኖችን እያመጡ ሲጋራውን እንዲወስዱ መመሪያ ያስተላልፋል። ባዶ ካርቶን ያመጣ ነጋዴ ሲጋራውን ገዝቶ እንዲያከፋፍል ቅድሚያ ይሰጠዋል። ባዶ ካርቶን ያላመጣ ነጋዴ ግን የካርቶን ፋብሪካው እስኪጠገን ድረስ ወረፋ ይይዛል። ለዚህም ነበር የደራው የካርቶን ንግድ ገበያ በመላ ሀገሪቱ የተጀመረው።
------
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 19/2022
2.0K views18:42
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-25 17:20:25 ==የግመሉ ወግ==
ከኢድሪስ ሻህ
(ትርጉም፡ አፈንዲ ሙተቂ)
---------
ሶስት ባልንጀራሞች ወደ ሩቅ ሀገር ጉዞ ጀመሩ፡፡ የመንገዱን አጋማሽ ከሄዱ በኋላ የግመል ፋንዲያ ታያቸው፡፡ አንደኛው ሰውዬ “ይህንን ፋንዲያ የለቀቀው ግመል ጅራተ-ቆራጣ ነው” አለ፡፡ ሰዎቹ እንደገና ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥቂት ከተጓዙ በኋላም ምሳ መብላት አሰኛቸውና ከአንድ ዛፍ ስር አረፉ፡፡ እዚያ ሳሉም የቡድኑ ሁለተኛ ሰው ወደላይ አንጋጦ ካየ በኋላ “ከዚህ ዛፍ የበላው ግመል አንድ ዐይና ነው” በማለት ተናገረ፡፡
ሰዎቹ ምሳቸውን ካጠናቀቁ በኋላ እንደገና መጓዛቸውን ቀጠሉ፡፡ በመንገዳቸው ላይም ግመል የሄደበትን ፋና አዩ፡፡ በዚህን ጊዜም የቡድኑ ሶስተኛ ሰው “ይህንን ዳራ (ፋና) በአሸዋው ላይ ያሳረፈው ግመል ከባድ እቃ ተጭኖበታል” በማለት ተናገረ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላም “ግመሌ ጠፍቶብኛል” ከሚል ሰው ጋር ተገጣጠሙ፡፡
አንደኛው ሰውዬ: “ግመልህ ጅራተ-ቆራጣ ነው?”
ባለ ግመል፡ “አዎን”
ሁለተኛው ሰውዬ፡ “ግመልህ አንድ ዐይና ነው?”
ባለ ግመል፡ “አዎን”
ሶስተኛው ሰው፡ “ግመልህ ከባድ እቃ ተጭኖበታል?”
ባለ ግመል፡ “አዎን”
ሶስቱም በአንድነት፡ “ግመልህን አላየነውም፣ ሂድና ፈልገው ወንድም”
ባለ ግመል፡ “እንዴ ምልክቱን አንድ በአንድ እየነገራችሁኝ ሂድና ፈልገው ስትሉኝ አታፍሩም? ግመሌን ስርቃችሁታልና ቶሎ መልሱልኝ፡፡ አለበለዚያ ከዳኛ ላይ ከስሼ አስቀፈድዳችኋለሁ”
ሶስቱ ሰዎች፡ “በእውነት እኛ አላየነውም”
ሰውዬው በሰዎቹ አድራጎት ተናድዶ ከዳኛ ላይ ከሰሳቸው፡፡

ሶስቱ ሰዎች ከተከሰሱበት ችሎት ፊት ቀረቡ፡፡ ዳኛውም “እናንተ ግመሉን ለምን ሰረቃችሁት አላቸው?”
ሶስቱ ሰዎች፡ “እኛ አልሰረቅነውም፡ ጭራሽ ግመሉን አላየነውም”
ዳኛው፡ “ታዲያ ሰውየው ግመሌን አይተውታል ነው የሚለው?”
ሶስቱ ሰዎች፡ “እኛ ስለግመሉ የተናገርነው በመንገድ ላይ ካየናቸው ምልክቶች ተነስተን ነው”
ዳኛው፤ “እስቲ ያያችኋቸውን ምልክቶች ንገሩን”

አንደኛው ሰውየ፡ “እኔ ግመሉ ጅራተ ቆራጣ ነው ያልኩት በመንገድ ላይ ካየሁት ፋንዲያ ተነስቼ ነው፡፡ በመንገድ ላይ ያየሁት ፋንዲያ በአንድ ቦታ ተከምሯል፡፡ ግመሉ ጅራት ቢኖረው ኖሮ በጅራቱ እየመታው ስለሚበታትነው በአንድ ቦታ አይከመርም ነበር፡፡ ስለዚህ ፋንዲያው በአንድ ቦታ የተከመረው ጅራት ስሌለው መሆን አለበት”

ሁለተኛው ሰውዬ፡ “እኔ “ግመሉ አንድ ዐይና ነው” ያልኩበት ምክንያት በግመሉ የተበላውን ዛፍ አይቼ ነው፡፡ ያየሁት ዛፍ በአንድ ጎኑ ብቻ ተበልቷል፡፡ የዛፉ ሌላኛው ክፍል ግን ምንም አልተነካም፡፡ ግመሉ ሁለት ዐይና ቢሆን ኖሮ ዛፉን በሁለቱም በኩል ይበላለት ነበር፡፡ አንድ ዐይና በመሆኑ ግን የዛፉን ሌላኛውን ክፍል ሳይነካው ሄዷል”

ሶስተኛው ሰውዬ፡ “እኔም ግመሉ ከባድ እቃ ተጭኖበታል ያልኩት የግመሉን ፋና አይቼ ነው፡፡ የግመሉ ፋና ወደ አሸዋው ውስጥ ሰርጉዶ ገብቷል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ግመሉ ከባድ እቃ የተጫነበት በመሆኑ ነው፡፡ ግመሉ ቀላል እቃ የተሸከመ ቢሆን ኖሮ የእግሩ ፋና ከአሸዋው ውስጥ ጠለቅ ብሎ አይገባም ነበር፡፡

ዳኛው በሰዎቹ ብልህነትና አስታዋይነት ተገረመ፡፡ ከዚያም “እጅግ አስገራሚ ሰዎች ናችሁ፡፡ እጅግ በጣም አስገራሚ ትምህርት ነው የሰጣችሁን፡፡ የማስተዋል ችሎታችሁ በጣም ያስደምማል፡፡ ስለዚህ እናንተ ከግመሉ ስርቆት ነጻ ናችሁ” በማለት አሰናበታቸው፡፡
(Idries Shah: Caravan of Dreams; 1973)
2.0K views14:20
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-25 01:13:24 “መወድሰ ሸገር”
-----
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
ወይ አዲስ አበባ አንቺ ሸገር ሸገር
ወይ አንቺ ፊንፊኔ አንቺዋ ሸገር
ባንቺው ይሰተራል አዳሜ ሲቸገር
አንቺው ትበቃለሽ ለከተማነቱ
ባንቺው ነው የፈለቀው ዘመናዊነቱ፡፡
*
ሸገር ሁሉንም ናት፡፡ የኢትዮጵያ ሰው በሙሉ ይወዳታል፤ ይናፍቃታል፤ ያሞግሳታል፤ ይጽፍላታል፡፡ በተለይ የድሮ ከያኒያን ግጥሞቻቸው እንዲጣፍጡላቸው በስንኞቻቸው መሀል የርሷን ስም ጣል ማድረጋቸው በጣም የተለመደ ነገር ነበር፡፡ ለምሳሌ ዓሊ ቢራ በጣፋጭ አንደበቱ ሸገርን እንዲህ ብሎአት ነበር (ከቅንፍ ውጪ ያለው ኦሮምኛ ነው፤ በቅንፍ ውስጥ ያለው ተቀራራቢ የአማርኛ ትርጉም ነው)፡፡

Silaa Shaggarin bahaa, Shaggaritti kooraa fannisanii (ሸገር እወጣ ነበር፤ ግን በሸገር ላይ ኮርቻ ሰቅለዋል)
Silaa sibiran dhufaa, sibratti ijoollee raffisanii (አንቺ ዘንድ ልመጣ ነበር፤ ግን አንቺ ጋ ልጆች አስተኝተዋል)
Ijoolleen hindubbatuu (ልጆቹ ስለማይናገሩ)
Shurrubbaa lash gootee na hindhungattuu? (ሹርባሽን “ለሽ” አድርገኝ ሳሚኝ የኔ ኩሩ)

ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ ደግሞ እንዲህ ብሎላታል፡፡

Silaa Shaggarin bahaa Shaggar hinbahuu xaafiin arama (ወደ ሸገር ልወጣ ነበር፤ ግን አሁን ትቼው ጤፍ ላርም ነው)
Koottutii na haasofsiisi walalaa dammaa (ነይ አጫውቺኝ የኔ ወለላ ናፍቄሻለሁ)

ታዲያ የድሮው ልማድ በኛ ዘመንም ተደጋግሞ ሲከሰት ይታያል፡፡ ለምሳሌ የኔ ትውልድ አባል የሆነው ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የሸገርን ውብ ህዝባዊ መስተጋብር ሲገልጽ እንዲህ ማለቱ አይዘነጋም፡፡

“ሸገር አዲስ አበባ አንቺ ያለሽበት
ራጉኤል አይደል ወይ የአንዋር ጎረቤት?
ቅዳሴና አዛኑን አጥር ቢለያቸው
ፈጣሪ ከሰማይ አንድነት ሰማቸው፡፡
*
“ሸገር” በኑሮና በስራ አጋጣሚ በደንብ ከማውቃቸው ሶስት ከተሞች አንዷ ናት፡፡ እንደርሷ የማውቃቸው ከተሞች ገለምሶ እና ሀረር ብቻ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ከነዋሪቿ ጸባይ 1/3ኛ ያህሉን ወርሼአለሁ (በተቀረው 2/3ኛ ጸባዬ የሀረር ሰው ነኝ)፡፡ ታዲያ አንዳንዶች እንደሚያወሩት ሸገርና ነዋሪዎቿ ዝጋታሞች አይደሉም፡፡ የጨዋታና የሳቅ ድርቀትም አያጠቃቸውም፡፡ ልቡን ከሰጡት የበለጠ ፍቅር ይሰጥና ወደ ውስጣችሁ እንድትመለከቱ ያደርጋችኋል- የሸገር ሰው (የጥቂት ውርጋጦች ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ)፡፡

ከሸገር ልጅ ጋር በደንብ ስትላመዱ እንዳሻችሁት ይሆንላችኋል፡፡ እንዳሻችሁት ይወዳችኋል፡፡ ችግርና ደስታችሁን በቅርበት ይካፈላል፡፡ ይህ በሐሰት የምደርተው መወድስ እንዳይመስላችሁ! በተግባር ያየሁትን ነው በግላጭ የምጽፍላችሁ፡፡ ለምሳሌ በህይወቴ እጅግ በጣም የማምነውና ችግሬን የማዋየው ሰው “ሸገር” የተወለደ የሸገር ልጅ ነው እንጂ የአካባቢዬ ተወላጅ አይደለም፡፡ ደግሞ እንዲህ የምለው ሰው “ሴት” ናት፡፡ እንደርሷ ያስገረመኝን ሰው የተዋወቅኩባቸው አጋጣሚዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡

"ክርስቲያኗ ፍቅረኛዬ" ያልኳትን ታስታውሳላችሁ አይደል? አዎን! ወደ አሜሪካ ከመብረሯ በፊት የኔ ምርጥ ጓደኛ እርሷ ነበረች። እኔ ሙስሊም የሀረር ልጅ፣ እርሷ ክርስቲያን የሸገር ልጅ መሆናችን ልብ ለልብ እንዳንገናኝ አላደረገንም፡፡ ሁለታችን እንደ ወንድምና እህት ሆነን በጣም እየተዋደድን ያሳለፍነውን ጊዜ የሚያውቁ ሰዎች እስከ አሁን ድረስ ይጠይቁናል ፡፡
*
ሸገርን ኖረንባታል፡፡ ተምረንባታል፡፡ በርካታ አስደሳችና አሳዛኝ አጋጣሚዎችን አሳልፈንባታል፡፡ ዛሬ “አደገች!… ፎቅ በፎቅ ሆነች” እየተባለ የሚጎሰምላት ነጋሪት ዳር ዳርታው “እወቁኝ!…እኔኑ ደግፉኝ!”..” የሚል ቅኝት ያለው ቢሆንም የርሷ እድገት የሁላችንም እድገት ነውና “እንኳን ተመነደገች” እንላለን፡፡ ሆኖም ከፎቅና ከመንገዱ ማማር በላይ የዘወትር ጭንቃችን ሰብዓዊ እድገቷ ነው፡፡ ከነዋሪዎቿ መካከል ግማሽ ያህሉ በቂ ምግብና የጤና አገልግሎት የማያገኙ መሆናቸው እየታወቀ፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ያዘለች መሆኗ እየተመዘገበ፣ በልመና የሚተዳደሩትም ቁጥራቸው እየጨመረ መሄዱ እየተነገረ፣ በነዋሪዎቿ መካከል “ታማኝ” እና “ተጋፊ” የሚል የማበላለጫ ድንበር ስለመሰመሩ እየተጻፈ ወዘተ … የህንጻና የፎቅ ጋጋታ መቁጠር የሸገርን ጤናማ እድገት ከሚመኝ ግለሰብም ሆነ ቡድን አይጠበቅም፡፡ የሁላችንም መገናኛና መኩሪያ ለሆነችው መዲናችን ክብርና ዘላቂ ድምቀት የምናስብ ከሆነ ለሰብዓዊ እድገቷ ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ሌላ ሌላው ከዚያ በኋላ ይደረስበታል፡፡
*
ስለ ሸገርና ትዝታዎቼ ብዙ በጻፍኩላችሁ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ምሽት ያለሁበት ሁኔታ ለዚያ ብቁ አላደረገኝም፡፡ ወደፊት መላልሰን ስለርሷ እናወጋ ይሆናል፡፡ ለአሁኑ ግን በዚህ የሸገር ውዳሴ ልሰናበታችሁ፡፡

“ወይ አንቺ ሸገር ሀገረ ገነት
ያሸተው ሲበላ ያላሸተው ሲሸት”
*
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 18/2014
2.1K views22:13
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-23 19:36:55 (ከላይ ከቀረበው ጽሑፍ የቀጠለ)

ሶስቱ የኦሮሞ ማህበረሰቦች የሚኖሩበትን ስፍራዎች አብዛኛው ህዝብ በሚያውቃቸው ስያሜዎች መጥራት ያስቸግራል፡፡ ሆኖም ኢቱ የሚኖርበት ክልል በጥንቱ አጠራር “ጨርጨር” ይባል እንደነበር ሽማግሌዎች ያወጋሉ፡፡ የአኒያ ኦሮሞ መኖሪያ ክልል ደግሞ “ቡርቃ ቲርቲራ” ይባላል፡፡ የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ በበኩሉ መኖሪያ ክልሉን “ጎሮ ፉጉግ” (የፉጉግ ጉብታ) በማለት ይጠራዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ስያሜ ሶስቱም የኦሮሞ ማህበረሰቦች የሚኖሩበት ክልል የወል መጠሪያ በመሆንም ያገለግላል፡፡

ከፉጉግ ተራሮች መካከል ለኔ አሰልቺ የሚሆንብኝ ክፍል ከጭሮ (አሰበ ተፈሪ) ተነስቼ ወደ ገለምሶ ስጓዝ የግዴታ ማቋረጥ ስላለብኝ ብቻ የምተላለፍበት ክፍል ነው፡፡ ከጭሮ ተነስታችሁ ቁኒ እስክትደርሱ አሰልቺ ዳገት! ከቁኒ እስከ በዴሳ አስጨናቂ ቁልቁለት!

እጅግ በጣም የተዋበው የፉጉግ ክፍል ደግሞ ቁንድዶ ነው፡፡ ሁኔታው በሙሉ በሰማይ ጠቀስ ህንጻ ላይ የተዘረጋ ሰፊ ሰገነት ይመስላችኋል፡፡ አየሩ፣ አራዊቱ፤ ጫካው፤ አዕዋፉ፣ ምንጩ ወዘተ ሁሉም ማራኪ ነው፡፡ ብቻ ምን ልበላችሁ! ተራራውን መውጣት ከቻላችሁ ወደ ምድራዊ ገነት ደረሳችሁ ማለት ነው፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
ሰኔ 20/2001 አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የወጣ ጽሑፍ
-----
Afendi Muteki, August 22/2022
------
ትክክለኛዎቹ የሶሻል ሚዲያ አድራሻዎቼ የሚከተሉት ናቸው።

= የፌስቡክ ፔጅ (My New Facebook Page)

https://www.facebook.com/AfendiEthno2018

=> የቴሌግራም ቻነል (My Telegram Channel)

https://t.me/afandishaHarar
2.1K viewsedited  16:36
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-23 19:36:55 “ፉጉግ” እና የሀረርጌ ኦሮሞ
------
ጸሐፊ፡- አፈንዲ ሙተቂ
------
በማለዳ ወይም ቀትር ላይ “የቻልኩትን ያህል ልመልከት” ብላችሁ ዓይናችሁን በነጻነት ብትለቁት ከአንድ የተፈጥሮ ግድግዳ ጥግ ትደርሳላችሁ፡፡ ከዚያ ወዲያ ላማትር ብትሉ በጭራሽ አይሆንላችሁም፡፡ ይህም በአማርኛ “አድማስ” የሚባለው ጠርዝ ነው፡፡ ፈረንጆቹ “horizon” ይሉታል፡፡ በኦሮምኛስ (Afaan Oromoo) ምን እንደሚባል ታውቃላችሁ?

ኦሮምኛ ብዙ ዘዬዎች ያሉት በመሆኑ ስያሜው እንደ የአካባቢው ይለያያል፡፡ እኔ አፍ በፈታሁበት የሀረር ኦሮምኛ አድማስ ማለት ከፈለጋችሁ ግን “ፉጉግ” ትላላችሁ፡፡

በሀረርጌ ገጠሮች ውስጥ ስትዘዋወሩ ከፊት ለፊቱ የተዘረጋውን ሰፊ አድማስ አየት አድርጎ “Ar’a Fugug Rooba Hima” የሚል የሀረርጌ ገበሬ በየአፍታው ያጋጥማችኋል፡፡ የሀረርጌ ገበሬ እንዲህ ሲል “ዛሬ ፉጉግ ስለዝናብ ይናገራል” ማለቱ ነው፡፡ መልእክቱ ግን “ዝናብ እየመጣ ነው” የሚል ነው፡፡ በሀረር ኦሮምኛ “ከአድማስ ባሻገር” ለማለት ካሻችሁ ደግሞ “ፉጉጊን ገመ”(Fugugiin Gama) ነው የምትሉት፡፡

በጥንቱ የኦሮሞ ባህላዊ አስተዳደር ዘመናት ከሞት ፍርድ ቀጥሎ በወንጀለኞች ላይ የሚጣለው ትልቁ ቅጣት ከሀገር መባረር ነበር ይላሉ- የሀረርጌ ሽማግሌዎች፡፡ ይህ ቅጣት በበርካታ ማህበረሰቦች ዘንድ የሚታወቅ በመሆኑ አስገራሚ ላይሆን ይችላል፡፡ እኔ ጨዋታውን ያመጣሁት የሀረርጌ ኦሮሞ ለዚህ ቅጣት የሰጠው ስያሜ ስለሚደንቀኝ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ቅጣት የወሰኑ ሽማግሌዎች “ፉጉጊን ገመ ጌሳ ደርባ” በማለት ለፍርድ አስፈጻሚዎች ትእዛዝ ይሰጣሉ፡፡ በአማርኛ “ከፉጉግ ወዲያ ውሰዱትና ጣሉት” ማለት እንደማለት ነው፡፡

የሀረርጌ ኦሮሞ ከአዋሽ እስከ ጅጅጋ ድረስ በተዘረጋ ሰፊ መሬት ላይ የሚኖር ቢሆንም በአንድ ቀበሌ ለሚኖር ሰው ከ“ፉጉግ ወዲያ” ያለው መሬት በርሱ ሀሳብ ሌላ ክልል ነው፡፡ “ፉጉግ” ለጥቅላላው የሀረርጌ ህዝብ ደግሞ ሌላ ውስጣዊ “ማዕና” (ፍቺ) አለው፡፡ ለመሆኑ “ፉጉግ” የሚለው ቃል ምንጩ ከየት ነው? የፉጉግ ውስጣዊ “ማዕና”ስ ምንድነው?
-----------------
=የፉጉግ ተራሮች=

የጂኦግራፊ ካርታዎችን ከፊታችሁ ዘርግታችሁ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ዓይናችሁን ጣል ካደረጋችሁ “Ahmar Mountains” በሚል ስያሜ የሚጠራ የተራራ ሰንሰለት ትመለከታላችሁ፡፡ ይህም ከአርባ ጉጉ (አርሲ) እስከ ፋፈም ሸለቆ (ጉርሱም) ድረስ ለተዘረጉ ሰንሰለታማ ተራሮች መጠሪያ የሆነ የጋራ ስም ነው፡፡ ስያሜው ለተራሮቹ ለምን እንደተሰጠ በትክክል አላውቅም፡፡ “አሕመር” በዐረብኛ “ቀይ” ማለት በመሆኑ በተራሮቹ ላይ ፈጠው ከሚታዩ ቀያይ ዐለቶች ጋር የተያያዘ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ሆኖም የሀረርጌ ኦሮሞ ሰንሰለቱን ሲጠራ “አህመር” አይልም፡፡ ይህንን የተግተለተለ የተፈጥሮ ስሪት “ፉጉግ” ይለዋል፡፡

ፉጉግን በየትኛውም የሀረርጌ ክፍል ሆናችሁ ለማየት ትችላላችሁ፡፡ የ“ፉጉግ” መነሻ ግን በምስራቃዊ የአርሲ ክፍለ ሀገር ያለው የአርባ ጉጉ ተራራ (በኦሮሞ ህዝብ አጠራር “ጋረ ጉጉ”) ነው፡፡

“ፉጉግ” ከመነሻው ላይ ቀለል ያለ ነው፡፡ ወደ ገለምሶ፣ ዋጩ እና በዴሳ አካባቢ ሲደርስ መወሳሰብ ይጀምራል፡፡ ወደ ቁኒ፣ አርበ ረከቴ፣ ደበሶ እና ሂርና ሲደርስ ግን መላ ቅጡ የጠፋ ትብታብ ጠፍር ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ የሚያካልለው መሬት ስፋትም በጣም ይጨምራል፡፡ እንዲህ ውስብስብ እንደሆነ ወደ በሮዳ፣ ቆቦ፣ ጨለንቆና ቀርሳ አካባቢዎች ይደርሳል፡፡ ወደ ሀረማያ እና ሀረር ሲመጣ መቃለል ይጀምራል፡፡ ጅጅጋ ከመድረሱ በፊት ግን ይጠፋል፡፡

ከላይ እንደጠቀስኩት በየትኛውም የሀረርጌ ክፍል የሚኖር ሰው “ፉጉግ”ን ለማየት ይቻለዋል፡፡ ስለዚህ ሩቅ የሆነ ነገር ሁሉ ለርሱ “ከፉጉግ” ወዲያ ያለ ነው፡፡ የፉጉግ ተራሮች አግራሞትን የሚያጭሩት ግን ውስብስብ ሆነው በመፈጠራቸው ብቻ አይደለም፡፡ የተራሮቹ አስደማሚ ምእራፍ በቋንቋ፣ በስነልቦና እና በእምነት አንድ የሆነውን የሀረርጌ ኦሮሞ በባህላዊ አወቃቀር፣ በአሰፋፈር እና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ረገድ በሶስት ቦታ ስለሚከፍሉት ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ሊገነዘብ የሚችለውም ሁኔታዎችን በአንክሮ የተመለከተ ወይንም ጠለቅ ያሉ የምርምር ጽሁፎችን ያነበበ ሰው ብቻ ነው፡፡ የፉጉግ አስፈላጊነትና ትንግርተኛነት ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡

አዎን! ፉጉግ በግላጩ (reality) አንድ የሆነውን የሀረርጌ ኦሮሞ በሶስት ትላልቅ ማህበረሰቦች ይከፍለዋል፡፡ እነርሱ እነማን ናቸው?
**
ፉጉግ እጅግ በጣም በተወሳሰበት ምእራባዊ ክፍሉ “ቡርቃ” የሚባል ትልቅ ጅረት ይፈሳል፡፡ “ቡርቃ” ከበሮዳ ከተማ አቅራቢያ ተነስቶ የደቡብ አቅጣጫን ይዞ ይፈስና የዋቤ ወንዝ (ዋቤ ሸበሌ) ዋነኛ ገባር ከሆነው “ራሚስ” ጋር ይቀላቀላል፡፡ ከ“ቡርቃ” በስተምእራብ በኩል የሰፈረው የሀረርጌ ኦሮሞ “ኢቱ” ተብሎ ይጠራል፡፡
ቡርቃ በፉጉግ ተራሮች ላይ በተሸነቆረ ሸለቆ ውስጥ ሌት ተቀን ይፈሳል፡፡ እርሱን ተሻግራችሁ እስከ ፋፈም (ጅጅጋ) ድረስ በተዘረጋው መሬት ውስጥ መጓዝ ካሰኛችሁ በሌላኛው የሀረርጌ ኦሮሞ ቅርንጫፍ ውስጥ መግባታችሁ ነው፡፡ በዚህኛው ክፍል የሰፈረው የሀረርጌ ኦሮሞ “አፍረን ቀሎ” ይሰኛል፡፡

ፉጉግ ወደ ቀድሞው የጋረ ሙለታ አውራጃ ሲደርስ የሰማይ ጣራ ይነካል፡፡ የፉጉግ ከፍተኛ ቦታ የሚገኘውም እዚህ አካባቢ ነው፡፡ እንዲያውም የትክክለኛው ፉጉግ መገኛ እዚህ ሳይሆን አይቀርም! በርካታ የተራራ ጫፎች አንደኛ ለመሆን የሚፎካከሩት በዚህኛው የተራራው ሰንሰለታማ ክፍል ነውና፡፡ ሆኖም ከነዚህ ተራሮች መካከልም በቁመቱ አንደኛ የሆነው “ጋረ ሙለታ” እንደሆነ ማንም ይነግራችኋል፡፡ “ጋረ ሙለታ” የሚለው ስያሜ ራሱ ተራራው ከሁሉም ቦታ ተሁኖ የሚታይ መሆኑን ያመለክታል፡፡

“ጋረ ሙለታ” በሚገኝበት አካባቢ ምእራባዊ ክፍል ደግሞ “ደባል” የሚባል የተራራ ጫፍ አለ፡፡ “ደባል” በሳንሳዊ ልኬት የፉጉግ አንደኛ ተራራ አለመሆኑ ቢረጋገጥም በትውፊት “ጋረ ሞቲ” (የተራራ ንጉስ) የሚባለው እርሱ ነው፡፡ “ጋረ ሙለታ” እና “ደባል” ባሉበት ስፍራ የሚኖረው ከላይ የጠቀስኩት “አፍረን ቀሎ” ነው፡፡ እነዚህን ተራሮች ተሻግራችሁ በስተደቡብ አቅጣጫ ቁልቁል ስትወርዱ ደግሞ የሀረርጌ ኦሮሞ ሶስተኛ ቅርንጫፍ ከሆነው የ“አኒያ” አሮሞ መሬት ትገባላችሁ፡፡

ፉጉግ የሀረርጌን ኦሮሞ እንዲህ ይከፋፍለዋል፡፡ ከሶስቱ ማህበረሰቦች መካከል በፉጉግ ላይ የማይኖረው አርብቶ አደሩ “አኒያ” ነው፡፡ ሆኖም እርሱም ራቅ ብሎ ስለ ፉጉግ ይጠበባል፡፡ ስለፉጉግ ብትጠይቁት እስኪበቃችሁ ድረስ ይነግራችኋል፡፡

ከ“አኒያ” ቀጥሎ ሰፊ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ የምታገኙት በኢቱ ኦሮሞ ዘንድ ነው፡፡ ከአዋሽ ፈንታሌ እስከ ሚኤሶና አፍደም ድረስ የሰፈረው የኢቱ ኦሮሞ ሙሉ በሙሉ አርብቶ አደር ነው፡፡ በዚህ አካባቢ አራሽ ገበሬ የምታገኙት የአሰቦት ከተማን በሚያካልለው ሜዳማ ስፍራ ላይ ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከዋቤ ሸበሌ ወንዝ ጋር በሚዋሰኑት የዳሮለቡና ቦኬ ወረዳዎች ከሚኖረው ህዝብ ግማሹ አርብቶ አደር ነው፡፡

የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ ግን በአብዛኛው አራሽ ነው-ከያዘው ስፍራ አንጻር ሲታይ፡፡ ሆኖም በዚህም ክፍል ያለው አርብቶ አደር በቁጥር ሲቀመጥ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ በጃርሶና ጭናክሰን ወረዳዎች የሰፈረው የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ በአብዛኛው አርብቶ አደር ነው፡፡
1.9K views16:36
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-22 23:15:50
"ተባለ...ተባለ እንዴ"
------
ፀሐዬ ዮሐንስ፣ ተመስገን ተካ እና ሮሃ ባንድ አስገራሚ ጥምረት ያሳዩበት አልበም።
----
አወይ ሰሞኑን ምን ነካህ
ጸባይህ ተቀይሯል።
(እስቲ እኔን ለቀቅ አርጉኝ)
አወይ ሰሞኑን ስላንተ መክሳትህ
መጥቆርህ ብዙ ይወራል።
(እንዲህም ተባለ እንዴ?)
ተባለ (ተባለ እንዴ?)
ተባለ (ተባለ እንዴ?)
----
"ተባለ...ተባለ እንዴ?" ከዚህ አልበም መውጣት በፊት ተደጋግሞ የማይነገር ሐረግ ነበር። ይህ አልበም እንደወጣ ግን ወጣቶችና ጎልማሶች እንደ ፋሽን የሚናገሩት የመግባቢያ ቋንቋ ሆኗል።

ይህ አልበም በ1982 ነው የወጣው። በዚህ አልበም የተነሳ የፀሐዬ ዮሐንስ ዝና በጣም ነው የጨመረው። ታዋቂው ሮሃ ባንድም የሙዚቃ እጀባውን በልዩ ቀለም በመወጣቱ በጣም የተደነቀው። ከማንም በላይ በዚህ ስራ ልዩ ብቃቱን ያሳየው ግን ወጣቱ ገጣሚ ተመስገን ተካ ነው።

ተመስገን ተካ በዚያ ወቅት ገና የ24/25 ዓመት ወጣት ነበር። ከዚህ ስራ በፊት ለተለያዩ አርቲስቶች የዘፈን ግጥሞችን ሰጥቷል። በተለይ ለኬኔዲ መንገሻ በሚጽፋቸው ግጥሞች መደነቅ ጀምሯል። ለሙሉ አልበም ግጥም መጻፍ የጀመረው ግን በዚህ የፀሐዬ ዮሐንስ ካሴት ላይ ነው።
-----
ተመስገን ተካ ለረጅም ጊዜ በሕይወት መቆየት ካልቻሉትና ቦግ ብለው ከጠፉብን የጥበብ ከዋክብቶች አንዱ ነው። በ1993 ገና በለጋ ዕድሜው ተቀጭቷል።
RIP Temesgen Teka.
ተባለ....ተባለ እንዴ?
ተባለ...ተባለ እንዴ?
2.0K views20:15
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-07-15 11:02:59 .ከኢህአፓ ውድቀት እንማር
-----
ኢህአፓ ደርግን በማጨናነቅ መጣል ይቻላል ብሎ አመነ። እናም "ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት አሁኑኑ" የሚል የከረረ አቋም ይዞ ደርግን መወጠር ጀመረ። ይባስ ብሎም ታንክና መድፍ የገጠመውን አደገኛ ቡድን በከተማ ውጊያ ገጠመ። በውጤቱ መቶ ሺዎችን የወለደው ቀይ ሽብር ተወለደ። ኢህአፓም ብትንትኑ ወጣ።
-----
አክራሪነት ዋጋ ቢስ ነው። የተሰራውን መልካም ስራ ከማጥፋት በስተቀር አንድም ፋይዳ የለውም። ሁላችንም ወደ ልቦናችን እንመለስ። በእብሪት ላበደው ሁሉ ዱላ አቀባይ አንሁን።
350 views08:02
ክፈት / አስተያየት ይስጡ