2022-06-22 06:58:29
"ሰዕድ ኢብኑ አቢ ወቃስ
(ረዲየላሁ ዐንሁ) ክፍል "
<< ረሱል ﷺ እንዲህ አሉ፦ "ፊዳከ አቢ ወ ኡሚ ያ ሰዕድ (ሰዕድ ቀስስት! አባቴና እናቴ መስዋት ይሁኑልህ።>>]
•••✿❒ ❒✿•••
ሰውንም በወላጆቹ (በጎ እንዲያደርግ) በጥብቅ አዘዝነው፡፡ እናቱ ከድካም በላይ በሆነ ድካም አረገዘችው ጡት መጣያውም በሁለት ዓመት ውስጥ ነው። ለኔም ለወላጆችህም አመስግን በማለት (አዘዝነው)፣ መመለሻው ወደኔ ነው። ፨ ለአንተ በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህም አትታዘዛቸው፡፡ በቅርቢቱም ዓለም፤ በመልካም ሥራ ተወዳጃቸው፡፡ ወደእኔም የተመለሰን ሰው መንገድ ተከተል፡፡ ከዚያም መመለሻችሁ ወደእኔ ነው፡፡ ትሠሩት የነበራችሁትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ (አልነው)፡፡ [ሉቅማን፥14-15]
•••✿❒ ❒✿•••
ከዚህ የቁርአን አንቀፅ ጋር የተያያዘ ብርቅዬ ታሪክ ያለው ግለሰብ ነው። ሰዕድ ኢብን አቢ ወቃስ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) ይባላል። ይህ ሶሐባ በጎ ነገር በተንኮል ላይ እምነት (ኢማን) በክህደት (ኩፍር) ላይ ድል ሲመቱ ያሳየናል። ሰዕድ ኢብን አቢ ወቃስ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) የዘር ሀረጋቸው ከልዑላን ጎራ ከሚያስፈርጃቸው ከመካ ወጣቶች አንዱ ነው። ነቢያዊ ብርሀን በመካ በፈነጠቀበት ወቅት ሰዕድ ገና አፍላ ወጣት ነበር። ርህሩህ አዛኝ ወላጆቹን ከመጠን በላይ ያፈቅርና ያገለግላቸው ነበር። በተለይ ከእናቱ ጋር ልዩ ትስስር ነበራቸው።
ሰዕድ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) ገና የ17 አመት ወጣት ቢሆንም አለባበሱ ግን የአዋቂወችና የትልቅ ሰወች ነበር። የዕድሜ አቻወቹ የሚያማልላቸው ነገሮች አያማልሉትም የዘወትር ትኩረቱ የጦር መሳሪያወችን መንከባከብ እና ኢልማ በመምታት ወታደራዊ ብቃቱን ማዳበር ነበር። ራሱን ለአንድ ከፍተኛ ተልዕኮ የሚያዘጋጅ ይመስላል። በአንፃሩ ሰዕድ ህዝቡ ያለበትን የእምነት ክስረትና የሞራል ድቀት ተቀብሎ ለመቆየት ህሊናው አልፈቀደለትም። አንድ ጠንካራ ሰው መጥቶ ህዝቡን ከጨለማ ህይወት ነፃ ማውጣት እንዳለበት ይሰማው ነበር። የመካና የመላው አለም ተጨባጭ ሁኔታ ከፍተኛ ዝቅጠትና ውድቀት ላይ ባለበት ወቅት ነበር...
•••✿❒ ❒✿•••
አላህ (ሱብሃነሁ ወተዓላ) ለሰው ልጅ እዝነትና ክብር ሲል ታላቅ ሰው የላከለት። የፍጡራን ሁሉ የበላይ የሆኑትን ሙሐመድ ኢብን ዐብደሏህ ﷺ እንዲነሱ ያደረገ። ለዚህ ቅንና የሐቅ ጥሪ ሰዕድ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) አስቸኳይ ምላሽ ነበር የሰጠው። ኢስላምን ከእርሱ በፊት የተቀበሉ ሰወች አስራ ሁለት ወይም አስራ ሶስት ሰወች ነበሩ። በከፍተኛ ኩራትም እንዲህ ይል ነበር፦ "ኢስላም ከፈነጠቀ በኋላ በክህደት የቆየሁት ለሰባት ቀናት ብቻ ነው። እኔ የኢስላም ሲሶ ነኝ።" ሰዕድ ሲሰልም ነብዩ ሙሀመድ ﷺ እጅግ በጣም ተደስተዋል። ምክንያቱም ግለሰቡ ከፍተኛ ተስፋ የሚጣልበትና ጀግና ሰው እንደሚሆን ከፊቱ ይነበብ ነበር።
•••✿❒ ❒✿•••
ይህ ጮርቃ ነገ ሙሉ ጨረቃ እንደሚሆን ታምኗል። ሰዕድ ልዑላን የሚባሉ ሰወች ውስጥ የሚመደብ በመሆኑም ወጣቶች የርሱን ተምሳሌት ሊከተሉ እንደሚችሉ እውን ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ሰዕድ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) የነቢዩ ﷺ ዘመድም ነው በእናታቸው በአሚና በኩል። የሰዕድ ኢስላምን በቀበል ግን በቀላሉ የሚያልፍ አልሆነም። ብርቱ ፈተናና ውሳኔን ለመለወጥ የሚዳዳ ሙከራ ገጥሞታል። በዚህ ሳቢያም አላህ ተባረከ ወተዓላ የቁርኣንን አንቀፅ አውርዶለታል። ሰዕድ ረዲየሏሁ ዐንሁ ታሪኩን እንዲህ ሲል ራሱ ይገልፅልናል፦
በዚህ ሳቢያም አላህ ተባረከ ወተዓላ የቁርኣንን አንቀፅ አውርዶለታል። ሰዕድ ረዲየሏሁ ዐንሁ ታሪኩን እንዲህ ሲል ራሱ ይገልፅልናል፦ ከመስልሜ ሶስት ቀን በፊት በህልሜ አየሁ። በድቅድቅ ጨለማ በውሀማ አካል ውስጥ ያለሁ ይመስለኛል። ጥልቅ ወደሆነው ውሀ ስደርስ የጨረቃ ብርሃን ታየኝ። ብርሃን ወዳለበት ቦታ ከፊት ለፊት ቀድመው የሚጓዙ ሰወች ተመለከትኩ። ዘይድ ኢብን ሐሪስን፤ ዓሊይ ኢብን አቡ ጧሊብን እና አቡበክር ሲዲቅን (ረዲየሏሁ ዐንሁም አጅማኢን) አየኋቸው መቸ ነው እዚህ ቦታ የደረሳችሁት አልኳቸው? በቅርብ አሉኝ። በማግስቱ ሙሐመድ ﷺ የሚስጥር ዳእዋ እንደጀመሩ ሰማሁ።
•••✿❒ ❒✿•••
አላህ ለኔ በጎ ነገር እንደሻልኝ አወቅኩ ። በርሳቸው አማካኝነትም ከጨለማ ወደ ብርሃን ሊያወጣኝ መሆኑን ተረዳሁ። በፍጥነት ወደ እርሳቸው ሄድኩ። በአንድ የመካ ሸለቆ ስር ባለ ቤት ውስጥ አገኘኋቸው። ሶላት ሰግደው ጨርሰዋል። ኢስላምን ተቀበልኩ። በህልሜ ካየኋቸው ግለሰቦች ውጭ የቀደመኝ አልነበረም። ሰዕድ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) ኢስላምን ከተቀበለ በኋላ የገጠመውን ፈተናም እንዲህ በማለት ይገልፀዋል። "እናቴ መስለሜን ስትሰማ እጅግ በጣም ተበሳጨች። እናቴን ታዛዥና አፍቃሪ ወጣት ነበርኩ። ወደኔ በመምጣትም፦ 'ሰዕድ ሆይ! ...
የአባትህና የእናትህን ሃይማኖት በመተው ያቀፍከው ዲን (ሃይማኖት) ምንድን ነው? በፈጣሪ ስም እምላለሁ አዲሱን ሃይማኖትህን መተው አለብህ። አሊያ ግን እስከምሞት ድረስ አልበላም፥ አልጠጣም። ልብህም በእኔ ሀዘን እንደተቆራመተ ይኖራል። በሰራኸው ተግባር ፀፀት ይወርስሀል። ሰወችም ዝንተ ዓለም በአድራጎትህ ሲያነውሩህ ይኖራሉ። አለችው። "እሱም እናቴ ሆይ!፥ ይህንን ነገር አትፈፅሚ። እኔ ሃይማኖቴን ለምንም ነገር ስል አልለውጥም" አልኳት። እርሷ ግን በዛቻ ብቻ አልተወሰነችም። መብላትና መጠጣቷን አቆመች። ለተወሰኑ ቀናትም በዚሁ ሁኔታ ቀጠለች። አካሏ ተዳከመ። አጥንቷ ተዝለፈለፈ፥ ኃይሏ ሟሸሸ።
•••✿❒ ❒✿•••
በተደጋጋሚ በመመላለስ ጥቂት ህይወቷን ሊያቆይ የሚችል ምግብና መጠጥ እንድትወስድ አቀረብኩላት። እምቢታዋ ግን ከፍተኛ ነበር። እኔ ሃይማኖቴን እስካልተውኩ ድረስም እስትንፋሷ እስኪቋረጥ ድረስ እንደማትበላና እንደማትጠጣ በመሀላዋ አረጋገጠችልኝ። በዚህ ወቅት እንዲህ አልኳት፦ "እናቴ ሆይ! እኔ በጣም እወድሻለሁ። ነገር ግን ላንች ያለኝ ውዴታ ለአላህና ለመልእክተኛው ﷺ ካለኝ ፍቅር የሚበልጥ አይደለም። በአላህ ስም እምላለሁ! ለአንች አንድ ሺህ ነፍስ ቢኖሩሽና አንዱ ነፍስ ወጥቶ ሌላው እየተተካ ቢትቆይ እንኳን ይህንን ሃይማኖት አልተውም።"
•••✿❒ ❒✿•••
ፅናቴን ስትመለከት በከፍተኛ ጥላቻ መብላትና መጠጣት ጀመረች። በዚህ ሳቢያ ነበር አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ይህን አንቀፅ ያወረደው፦
وَإِن جَٰهَدَاكَ عَلَىٰٓ أَن تُشْرِكَ بِى مَا لَيْسَ لَكَ بِهِۦ عِلْمٌۭ فَلَا تُطِعْهُمَا ۖ وَصَاحِبْهُمَا فِى ٱلدُّنْيَا مَعْرُوفًۭا ۖ
ለአንተ በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህም አትታዘዛቸው፡፡ በቅርቢቱም ዓለም፤ በመልካም ሥራ ተወዳጃቸው፡፡ [ሉቅማን፥15]
የተለያዩ ጣፋጭ አስተማሪና ኢስላማዊ
ታሪኮች የሚቀርቡበት ምርጥ ቻናል ነው።
•════••• •••════•
ሼር JoiN & Share
https://t.me/AAASELEFYA
https://t.me/AAASELEFYA
94 views03:58