2022-05-01 07:42:59
#####ቶማሶች እመኑ #######
እንኳን ለዳግማ ትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ። አደረሰን።
የዳግም ትንሳኤ ነገር እንዴት ነው ቢሉ:- አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ቀን ሦስት ሊሌት(33 ሰዓት) በከርሰ መቃብር ከቆየ በኋላ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ሙስና መቃብር(በስጋ መፍረስ መበስበስን) ሳያገኘው ሞትና መቃብርን ድል አድርጎ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ለትንሣኤያችን በኩር ሆኖ ተነስቷል።
የክርስቶስን መነሳት አስቀድሞ የተገለፀው #ለሴቶች ነበር ሰው የመሆኑ ነገር ቀድሞ ለሴት(#ለድንግል _ማርያም) እንደተነገረ ሁሉ ከሙታን መነሳቱም አስቀድሞ ለሴት(ለመቅደላዊትማርያም)ተገልፆአል(ዮሐ 20፥16)።
እርሷም ለሐዋርያት ሄዳ ነግራቸው ነበር ከዚህ በኋላ ለቅዱስ ጴጥሮስ(ሉቃ 24፥34)፣
ወደ ኤማሁስ ተስፋ ቆርጠው ለተመለሱት አርድእት ከተገለፀ በኋላ(ሉቃ 24፥15)
ለሐዋርያት ሁሉ በተዘጋ ማህፀን አድሮ ሰው የሆነ አምላክ በተዘጋ በር ገብቶ ሰላምን ሰብኮላቸዋል(ሉቃ 24፥36)።
ትንሣኤውን ክርስቶስ ለሐዋርያት ሲገልፅ ከእነርሱ መሃል ቶማስ አልነበረም ነበርና (ዮሐ 20፥24) እንዴት እኔ ትንሣኤውን ሳላይ ቢል ክርስቶስ ደግሞ #በ8ተኛው ቀን ትንሣኤውን ለሐዋርያት ገለፀ ዳግም ትንሣኤ ይህ ነው።
#የቶማስ _አለማመን
ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን የቶማስን አለማመን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ሐሳብ ነው ብለው ይፈቱታል። ባይጠራጠር ባላየው አይቶትም እጁን ከቶ ባልዳሰሰው ባይዳስሰው የክርስቶስን አምላክነት ባልመሰከረ በመመስከሩ ደግሞ የሁሉን እምነት ጨምሯል።(ዮሐ 20፥31)ደግሞስ ይላሉ መተርጉማን ሐዋርያት ክርስቶስ ከሞት ተነሳ ብለው ሲያስተምሩ። #ቶማስ መነሳቱን ሐዋርያት ነገሩኝ ቢል ማን ትምህርቱን ይቀበለው ነበር???
የቶማስ አለማመን ለ8 ቀን የቆየ ነው የተወጋ ጎኑን ዳሶ ትንሳኤውን አይቶ "#ጌታዬ _አምላኬም" ብሎ መስክሯል(ዮሐ 20፥28)።
ቶማስ ጌታዬ አምላኬም በማለት የመሰከረው እግዚኣብሔር ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑን(ምስጢረ ሥጋዌን) ነው።ቶማስ ክርስቶስን ከዳሰሰ በኋላ ጌታዬ አለ አምላኩን ሥጋን ተዋሕዶ በሰው አካል ዳሶታልና ጌታዬ አለ።የዳሰሰው አካል ሩቅ ብእሲ ያልሆነ መለኮትን የተዋሐደ ነውና አምላኬም አለ።ቶማስ ጌታዬ አምላኬም ብሎ የመሰከረው ሌሎች እንዳሉት ሲዳስ ደንግጦ የደነገጠ የሚለውን እንደማያውቅ ሆኖ አልነበረም በፍፁም አምኖ እንጂ ለዚህም ማስረጃችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ቃል ነው
"ኢየሱስም ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው" ዮሐ 20፥29
ተመልከቱ ስለ አየኸኝ አምነሃል አለው እንጂ ስለ ደነገጥክ መስክረሃል አላለውም።ቶማስስ አይቶ ዳስሶ አመነ በሐዋርያት ስብከት የምናምን እንደ አባ ህርያቆስ "ከርሱም ጋር በላን ጠጣን..." ስለምንል ስለ እኛም ብፅዕና ተመስክሮልናል።እስከ አሁን የክርስቶስን አምላክነት ያላመኑ ያልመሰከሩ ቶማሶች ግን ብዙ ናቸው(ልብ ይስጥልን) ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች እንዲህ ይላቸዋል:-
"የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?" ገላ 3፥1
እኔም እንዲህ እላለሁ የማታስተውሉ መናፍቃን ሆይ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚኣብሔር መሆኑን እንዳታስተውሉ ማን አዚም አደረገባችሁ፤የማታስተውሉ መናፍቃን ሆይ ቶማስ አምላክነቱን የመሰከረለትን ክርስቶስን አምላክ ብላችሁ እንዳትቀበሉ አዚም ያደረገባችሁ ማነው???
እኛስ አባቶቻችን በተረዳ ነገር እንዳስተማሩን ወልደ አብ ወልደ ማርያም ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው ብለን እናምናለን።
መልካም የትንሣኤ በዓል።
አጽራረ ቤተክርስቲያንን ያስታግስልን።
ዲ/ን ፈቃዱ ጎንፋ (ዘፍቁረእግዚእ)
200 viewsፍቅር በ ኢትዮጵያ, 04:42