Get Mystery Box with random crypto!

'የዓለም ሁሉ እመቤት ተወለደች' እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የልደት | ትምህርተ አበው

"የዓለም ሁሉ እመቤት ተወለደች"

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል አደረሳችሁ።የድንግል ማርያም ልደት የሁላችን ልደት ነውና እርሷን የሰጠን አምላክ ክብር ምስጋና ይግባው።



(ሊቁ አባ ሕርያቆስ) በድርሰቱ"ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ"አ
እየለ የልደቷን ነገር ያደንቃል።

የተባረኩ ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሃና ግንቦት ፩ ቀን ይህችን ብርክት ልጅ ወለዱ ስሟንም ማርያም አሏት።

ማርያም ማለት:- ጸጋ ወሀብት ማለት ነው ለጊዜው ለወላጇቿ ለፍፃሜው ለሁላችን ጸጋና ሀብት ሆና ተሰታለችና።
ማርያም ማለት:- ፍጽምት ማለት ነው መልክ ከደምግባት አሟልታ ይዛለችና በኋላም በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ጸንታ ኖራለች።
ማርያም ማለት:- መርሕ ለመንግስተ ሰማያት ማለት ነው በምልጃዋ ሁላችንን ከልጇ አማልዳ መርታ መንግስተ ሰማያት ታስገባናለችና።
ማርያም ማለት:- ከሁለት ቃላት የተገኘ ነው እርሷም ሁለቱን መስተፃርራን አስተባብራ ይዛለችና እናትነትን ከድንግልና። ማር:- በምድር ያለ ጣፋጭ ያም:- በገነት ያለ ጣፋጭ ምግብ ነው ማርያም በምድር በደቂቀ አዳም በሰማይ በመላእክት ስሟ ጣፋጭ ነውና።

የከበረች ቅድስት ሃና የብጽአት ልጇን ነሃሴ 7 ቀን ጸንሳ በፈቃደ እግዚኣብሔር ግንቦት ፩ ቀን በሊባኖስ ተራራ
ወልዳታለች።

የመወለድዋ ደስታ ለቤተሰቦቿ ብቻ አይደለምና የዓለም ደስታ ድንግል ማርያም ከቤት ውጭ በተራራ ስር ተወለደች በቤት ወልደዋት ቢሆን ደስታው በእነርሱ በቀር ነበር የልደቷ ደስታ ግን ለሁላችን ነው በተለይ ለኦርቶዶክሳውያን።

ቅድስት ሃና ሆይ "እንኳን ልጅሽ ማረችሽ" ለሌሎች ሴቶች በወለዱ ግዜ እንኳን ማርያም ማረችሽ እንላለን አንቺ ግን የምትምርሽን ወልደሻታልና።

(ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዲህ እያለ ያመሰግናል) "የእግዚአብሔር ልጆች እንግዲህ ይህችን ንጽህይት ሙሽራ የወለዱልንን ኢያቄምንና ሐናን እናድንቃቸው፤የማትነቀፍ የእስራኤል ድንግል የተባረከችይቱም ፍሬ የፈራችባት የሩካቤያቸው ንጽህይት ቀን እንደምን ያለች ናት? ከይሁዳ ወገን የምትሆኝ ንጽህይት ርግብ ለመጸነስሽ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሆነባት የመገናኘታቸው ቀን እንደ ምን ቅድስት ናት?የንጉሥ አዳራሽ የምትሆን የእርሷ መሠረት የተመሰረተባት ዕለት እንደምን ደስ ያለች ናት? (አርጋኖን ዘሐሙስ)


አደራ በዓሉን ከፍፁም ክርስቲያናዊ ሥርዓት ሳንወጣ በአግባብ እናክብር ቅድስት ሃና እና ዘመዶቿ በዓሉን ለ15 ቀን በውጭ እንዳከበሩት አንድም ድንግል ማርያም ከቤት ውጭ እንደተወለደች አብነት በማድረግ ከቤታችን ውጭ በተለያየ ሥርዓት እንደየአቅማችን እናከብራለን የበዓሉ አከባበር ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ቅርጽ እየቀየረ ወደ ባዕድ አምልኮ እየዞረ መቷል ኦርቶዶክሳውያን በዓሉን ድንግል ማርያም ባለ ልደቷ በምትደሰትበት መልኩ ብቻ ማክበር ይገባናል።

እመቤቴ ሆይ እኔን ኋጥኡን ባርያሽን በምልጃሽ አስቢኝ።

የግንቦት ልደታ ዋዜማ/2014
ዲ/ን ፍቃዱ ጎንፋ (ዘፍቁረእግዚእ)