Get Mystery Box with random crypto!

'ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ' ሉቃ 22 | ትምህርተ አበው

"ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ"
ሉቃ 22፥19

በስመ አብ ወወልድ መንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን።
የተከበራችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች እንደምን ከርማችኋል እንኳን ለጸሎተ ሐሙስ አደረሳችሁ።
በዚህች ቀን ከተፈፀሙ ምስጢራት መካከል አንዱ ምስጢረ ቁርባን ነውና ስለ ቅዱስ ቁርባን ጥቂት እንነጋገር።ከላይ መግቢያ ያደረግነውን ጥቅስ በመያዝ ከእኛ እምነት በአፋ ያሉ ሰዋች(መናፍቃን) ለመታሰብያ አድርጉ ብሏቸዋልና መታሰብያ ነው እንጂ አማናዊ አይደለም ብለው ይሞግቱናል የእኛ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ምን ይላሉ:-

++++++++እውን መታሰብያ ነውን++++++

መናፍቃኑ መታሰብያ ለማለት የሚጠቅሱት ጥቅስ ይህ ነው" ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው ይህን ለመታሰብያዬ አድርጉት" ሉቃ22፥19 ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ቃል የተናገረው እነርሱ መስሏቸው በተረዱበት "በተረጎሙበት" አግባብ አይደለም ይልቁኑ ይህ ቃል እንዴት ይታያል ካላችሁ ተከተሉኝ:-

ይህንን ቃል ከሉቃስ ወንጌል በተጨማሪ በማቴዋስ ወንጌልም እናገኘዋለን "ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና። እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና። እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው" ማቴ 26፥26-28 በዚህ ቃል አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ህብስቱ አማናዊ ሥጋው ወይኑ አማናዊ ደሙ እንደሆነ ገለጠ እንጂ መታሰብያ አድርጉት አላለም።

የጌታ ሥጋና ደም መታሰብያ ሳይሆን አማናዊ ነው ይህንንም ንዋየ ህሩይ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይገልጸዋል "ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት" 1ቆሮ 11፥27 አስተውሉ መታሰብያውን ሳያስብ ቢቀር አላለም ይልቁኑ ሳይገባው የተቀበለ አለ እንጂ ስለዚህ የተገባቸው ብቻ ከርሱ ሊቀበሉት የሚገባ አማናዊ እንጂ መታሰብያ አይደለም ይህንንም እራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ በትእዛዝ አስቀመጠው "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ" ዮሐ 6፥54 ተመልከቱ ሥጋዬንና ደሜን የሚቀበል አለ እንጂ መታሰብያ የሚያደርገው አላለም ስለዚህ አማናዊ እንጂ መታሰብያ አይደለም።

ሊቁ አባ ሕርያቆስ እንዲህ ይላል"በበግ በጊደር በላህም ደም እንደነበረው እንደ ቀደሙት አባቶች መስዋዕት አይደለም እሳት ነው እንጂ፤ ፈቃዱን ለሚፈፅሙ ልብናቸውን ላቀኑ ሰዋች የሚያድን እሳት ነው ስሙን ለሚክዱ ለአመፀኞች ሰዎች የሚባላ እሳት ነው፤ እሳታውያን የሚሆኑ ሱራፌልና ኪሩቤል ሊነኩት የማይቻላቸው በእውነት እሳት ነው"(ቅዳሴ ማርያም)

ስለዚህ እንደሚሉን መታሰብያ ሳይሆን ሊቁ እንዳስተማረን በንፅህና ብንቀበለው ሕይወት የሚሰጠን አማናዊ ነው።

++ታድያ ለምን ለመታሰብያዬ አድርጉት አለ++

ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ያስረዳናል
" እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ። ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና" 1ቆሮ 11፥25
ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን አማናዊ የክርስቶስን ሥጋ እና ደም ስንቀበል ሞቱን ማሰብ ህማማተ መስቀልን መዘከር ይገባል ለዚህ ነው በቅዳሴያችን "ንዜኑ ሞተከ..." እያልን ሊቁ አፈ በረከት ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በቅዳሴው "የምትወዱት አልቅሱለት" እንዳለ የምንወደው ዋጋ የተከፈለልን እኛ አማናዊውን የክርስቶስን ሥጋ እና ደም ስንቀበል ሞቱን ሕማሙን ለእኛ ሲል የተቀበለውን መከራ ሁሉ መታሰብያ (ምሳሌ) አድርገን ልንቀበል ይገባል እንጂ ሥጋ ወደሙ አማናዊ ነው። ሲሰጠንም እንዲህ ብሎናል "ይህ ህብስት ሥጋዬ ነው ይህ ወይን ደሜ ነው" ማር 14፥22 መታሰብያ ሳይሆን ዘላለማዊ ሕይወት የምናገኝበት አማናዊ ነው።ንሰሐ ገብተን ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን የስሙ ቀዳሽ የክብሩ ወራሽ ያደርገን ዘንድ የድንግል ማርያም ምልጃ የቅዱሳን ጥባቆት አይለየን።
አሜን።

እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ጻማ ወድካም ዓመ ከመ ዮም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በፍስሐ ወበሰላም።

ዲ/ን ፍቃዱ ጎንፋ (ዘፍቁረእግዚእ)
ጸሎተ ሐሙስ(2014)