2022-06-27 15:07:01
ሕንጸተ ቤተ ክርስቲያን( ሰኔ 20 እና 21 )
በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ ተመዘገበልን ሰኔ ፳ (20) ቀን በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ ሀገር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ያለ እንጨት፣ ያለ ጭቃና ያለ ውሃ በሦስት ድንጋዮች በተወደደ ልጇ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የታነጸበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከሚከብሩ ከእመቤታችን 33 በዓላት አንደኛው ነው፡፡ ጌታችን በዐረገ በስምንተኛው ዓመት ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስ ወደ ፊልጵስዩስ ገብተው በክርስቶስ ስም አሳምነው ብዙ አሕዛብን ካጠመቁ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሊሠሩላቸው ወደዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ርዕሰ ሐዋርያት እያለ እኛ መሥራት አይገባንም ብለው ለሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት ላኩበት፡፡ እርሱም ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር መጥቶ ከቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ በርናባስ ጋር በኢየሩሳሌም ተገናኙ፡፡
በዚያም በአንድነት ሱባዔ ይዘው ከቆዩ በኋላ ጌታችን የሞቱትን አስነሥቶ፣ ያሉትንም ጠርቶ ቅዱሳን ሐዋርያትን በፊልጵስዩስ አገር ሰብስቦ ‹‹በእናቴ በድንግል ማርያም ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚሠራዉን የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ ላሳያችሁ ፤ ሥርዓቱንም ላስተምራችሁ ሰብስቤአችኋለሁ›› ብሎ ወደ ምሥራቅ ይዟቸው ወጣ፡፡ በዚያ ሥፍራ የነበሩትን ሦስት ድንጋዮችንም የተራራቁትን አቀራርቦ ፣ ጥቃቅኑን ታላላቅ አድርጎ ቁመቱን በ፳፬፤ ወርዱን በ፲፪ ክንድ ለክቶ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሰጣቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት ሰም እሳት ሲያገኘው እንዲለመልም፣ ድንጋዩ በእጃቸው ላይ እየተሳበላቸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሠርተው ፈጽመዉታል፡፡ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራዉም ጌታችን በዐረገ በ፲፱ኛው፤ እመቤታችን በዐረገች በ፬ኛው ዓመት ሰኔ ፳ ቀን ሲኾን፣ በ፳፩ኛው ቀን (በማግሥቱ) ኅብስት ሰማያዊ፣ ጽዋዕ ሰማያዊ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወረደ፡፡
ከእመቤታችን 33 ቱ በዓላት አንዱ ነው፤ ህንጸተ ቤተክርስቲያን ይባላል። የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የታነጸችው በዛሬዋ ቀን ነው አናጺውም እራሱ ባለቤቱ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ቦታው ፊልጰስዩስ ነው፤ ቤተክርስቲያኗ የተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው። ጴጥሮስ፤ ዮሐንስ በርናባስና ሌሎችም ሐዋርያት በፊልጰስዩስ ተሰብስበው ሳለ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል እመቤታችን በቀኙ ነበረች፤ 3 ድንጋዮችን አንስቶ ጎተታቸው እንደ ሰም ተለጠጡ እንደ ግድግዳም ሆኑ ዳግመኛም የብርሃን ምሰሶ ወረደ በሰማያዊቷ እየሩሳሌም አምሳያ አድረጎ አነጻት ሁለንተናዋም ተጠናቀቀ፤ ዳግመኛ በበነጋው ሰኔ 21 ቀን እመቤታችንን እና ቅዱሳን መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል ቅዳሴ ቀድሶ ለሐዋርያቱ አቆረባቸው ፍጹም ደስታም ሆነ።
ከዚህ በኃላ ሐዋርያት ከጌታ እንዳዩት በዓለም ዞረው ቤተክርስቲያን አንጸዋል። ከዚያ በፊት የነበረው የንጉሥ ሰሎሞን ቤተመቅደስ የአይሁድ ምኩራብ የአይሁድ ስርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እንጂ የአዲስ ኪዳን የቁርባንም ሆነ የጥምቀት ስርዓት መፈጸሚያ አልነበረም፤ ታዲያ ሐዋርያት የት ነበር ህዝቡን የሚያጠምቁት የሚያቆርቡት ካሉ በየሰው ቤት ነበር። ቤተክርስቲያናችን ዕለቱንም ህንጸተ ቤተክርስቲያን በማለት ታከብረዋለች።
ጌታችንም ከእመቤታችን ጋር ከሰማየ ሰማያት መጥቶ እመቤታችንን ታቦት፤ ሐዋርያትን ልዑካን አድርጎ፣ እርሱ ሠራዒ ካህን ኾኖ ቀድሶ ካቈረባቸው በኋላ ‹‹እምይእዜሰ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ፤ ከዛሬ ጀምሮ እናንተም እንደዚህ አድርጉ›› ብሎ አዝዟቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡
ይህ ታሪክ ብዙ ምሳሌዎች አሉት፡፡ ይኸውም፡- የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ቁመት በነገሥታት ዘመን የነበሩ የ፳፬ቱ ነቢያት፤ አንድም የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ አምሳል ሲኾን፣ ወርዱ ደግሞ የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፡፡ ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴ አምሳል ሲኾኑ፣ ከታች አቀማመጣቸው ሦስት፤ ከላይ ሕንጻቸው አንድ መኾኑ የሥላሴን ሦስትነትና አንድነት ያመለክታል፡፡ የሠሩትም ሦስት ክፍል አድርገው ሲኾን፣ ይህም የመጀመሪያው የታቦተ አዳም፤ ሁለተኛው የታቦተ ሙሴ፤ ሦስተኛው የታቦተ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዳግመኛም የሦስቱ ዓለማት ማለትም የመጀመሪያው የጽርሐ አርያም፣ ሁለተኛው የኢዮር፣ ሦስተኛው የጠፈር ምሳሌ ነው፡፡
አንድም መጀመሪያው የኤረር፣ ሁለተኛው የራማ፣ ሦስተኛው የኢዮር አምሳል ነው፡፡
በኤረር፡- መላእክት፣ መኳንንት፣ ሊቃናት፤
በራማ፡- ሥልጣናት፣ መናብርት፣
አርባብ፤ በኢዮር፡- ኃይላት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌል ይኖራሉ፡፡
እነዚህ ዘጠኙ ነገደ መላእክት የዘጠኙ መዓርጋተ ቤተ ክርስቲያን (መዓርጋተ ክህነት) አምሳል ሲኾኑ፣ ይኸውም መላእክት – የመዘምራን፤ መኳንንት – የአናጕንስጢሳውያን፤ ሊቃናት – የንፍቀ ዲያቆናት፤ ሥልጣናት – የዲያቆናት፤ መናብርት – የቀሳውስት፤ አርባብ – የቆሞሳት፤ ኃይላት – የኤጲስ ቆጶሳት፤ ሱራፌል – የጳጳሳት፤ ኪሩቤል – የሊቃነ ጳጳሳት አምሳሎች ናቸው፡፡
ይህም በታች (በምድር) የሚኖሩ ደቂቀ አዳም ከቅዱሳን በቀር ወደ ላይ (ወደ ሰማይ) መውጣት እንደማይቻላቸው፣ ከመዘምራን እስከ ጳጳሳት ድረስ ያሉ ካህናትም ከእነርሱ በላይ ያሉትን መዓርግ መሥራት (መፈጸም) እንደማይቻላቸው ያጠይቃል፡፡ እንደዚሁም በላይ የሚኖሩ መላእክት ወደ ታች መውረድ እንደሚቻላቸው ሊቃነ ጳጳሳትም ከእነርሱ በታች ያሉ ካህናትን ተልእኮ መፈጸም (መሥራት) እንደሚቻላቸው ያስረዳል፡፡
በጽርሐ አርያም መንበረ ብርሃን (የብርሃን መንበር)፤ ታቦተ ብርሃን (የብርሃን ታቦት)፤ መንጦላዕተ ብርሃን (የብርሃን መጋረጃ)፤ እንደዚሁም ፬ ፀወርተ መንበር (መንበሩን የሚሸከሙ)፤ ፳፬ አጠንተ መንበር (መንበሩን የሚያጥኑ) መላእክት አሉ፡፡
ጽርሐ አርያም – የመቅደስ፤ መንበረ ብርሃን – የመንበር፤ መንጦላዕተ ብርሃን – የቤተ መቅደሱ መጋረጃ፤ ፬ቱ ፀወርተ መንበር – የ፬ቱ ሊቃነ ጳጳሳት ወይም የመንበሩ እግሮች፤ ፳፬ቱ አጠንተ መንበር – የጳጳሳት (የኤጲስ ቆጶሳት) አምሳሎች ናቸው፡፡
#ሰኔ_ጎልጎታ፦ በሌላ በኩል ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም በዚህ ቀን (ሰኔ 21) ልጇን ወዳጇን ጐልጐታ ላይ ለኃጥአን ምሕረትን ለምናዋለች:: ጌታችንም ‹‹ስምሽን የጠራውን፤ በቃል ኪዳንሽ ያመነውን ሁሉ እምርልሻለሁ፡፡›› ብሏታል::
የድንግል እመቤታችን ልመናዋ ክብሯ፣ ጣዕመ ፍቅሯና በረከቷ በሁላችን ላይ ይደርብን:: !!! ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን !!! በዘመናችን የመጣብንን ወረርሽኝ በቸርነቱ ያስታግስልን አሜን!!!!
#ሼር
https://t.me/joinchat/AAAAAFSJ49GBC3YRZoSNHQ
16.6K views12:07