2022-07-09 07:57:46
የዝምታ ጊዜ አስፈላጊነት
ለአንድ አማኝ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር መቀመጡና ከእርሱ ጋር ህብረት መፍጠሩ እንደ ምን ያለ የተባረከ ልዩ መብት ነው! እንዲህ ያለው ሁኔታ ነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን "ስትጸልይ ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገርህ አይደለምን? ይህ እንደ ምን ያለ ልዩ መብት ነው!" በማለት በአድናቆት እንዲናገር ያደረገው። በአጠቃላይ የዝምታ ጊዜ ማለት ይህ ነው። አንተ በዚህ ልዩ መብትህ ሐሴት ማድረግ ትፈልጋለህ?
ምስጋና ይግባውና የዝምታ ጊዜን ጥቅም በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ውስጥ መገንዘብ ትችላላችሁ ፤ እርሱ ፍለጋውን እንከተለው ዘንድ ምሳሌ ትቶልን ሄዶአልና ፤1ኛ ጴጥ 2:21። አምላካችን በየዕለቱ ማልዶ በመነሣት ገለልተኛ ወደ ሆነ ቦታ እየሄደ ይጸልይ ነበር ፤ ማር 1:35። ሌሊቱንም ሙሉ ሲጸልይ ያድር ነበር ፤ ሉቃ 6:12። አብዝቶ ይጸልይ የነበረውም ወደ ምድረ በዳ በመሄድ ነበር ፤ ሉቃ 5:16።
በእርግጥ ለክርስቶስ ጸሎት አስፈልጎት ነበር እንዴ?
በሥላሴ መካከል ያለው አንድነት የማይለያይ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። በዚህ ምክንያት ወልድ ለአብ እንዲህ በማለት ተናግሮአል ፦ ". . አባት ሆይ ፤ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፤. . " ዮሐ 17። መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ያደረገው የእርሱን ፈለግ ለሚከተሉ ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ለሚኖራቸው ቁርኝት ማስረጃ እንዲሆን ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሕይወት ስንመለከት ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው የበጀውን የዝምታ ጊዜ ጥቅም መገንዘብ እንችላለን። በመቀጠል ጥቂት ምሳሌዎች ቀርበውልናል፦
ሀ/ ነቢዩ ዳዊት።
እንደ ንጉሥነቱ ፣ እንደ መሪነቱና እንደ ፈራጅነቱ ባተሌ ሰው ቢሆንም እንኳ ዘወትር በማለዳ ከእግዚአብሔር ጋር ብቻውን የሚሆንበት ጊዜ ነበረው። "በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ ፤ በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ ፤ እጠብቃለሁም።" መዝ 5:3።
ለ/ ዳንኤል
ነብዩ ዳንኤል ብቻውን ከእግዚአብሔር ጋር ሆኖ በመጸለይ ጊዜውን ማሳለፍን ልማድ አድርጎት ነበር። ንጉሡ ይህን እንዳያደርግ በጽሑፍ ቢከለክለውም እንኳ ግድ አልሰጠውም። ይልቁንም እንዲህ ነበር ያደረገው ፦ "ዳንኤልም ጽሕፈቱ እንደ ተጻፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፤ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር ፤ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ፣ አመሰገነም።" ዳን 6:10።
እስቲ ለዚህ ድንቅ ዓረፍተ ነገር ትኩረታችሁን ስጡት ፣ "ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ. . " ለሚለው። የዝምታን ጊዜ ማሳለፍ በእርሱ ሕይወት ውስጥ የማያቋርጥ ልማድ ነበረ።
ሐ/ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ
ቅዱስ ጴጥሮስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በህብረት በሚካሄደው ጸሎት ላይ ከነበረው ተሣትፎ በተጨማሪ በየዕለቱ በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ሲሰበሰቡ አብሮ ይገኝ ነበር። እርሱ ጊዜውን ለጸሎት ያውል ነበር። ስለ ቅዱስ ጼጥሮስ መጽሐፍ ቅዱስ " . . . ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ጣራው ወጣ።" (ሐዋ 10:9) የሚል ቃል ዘግቦ እናነባለን።
እነዚህንና ሌሎች ብዙ ተጨማሪ ምሳሌዎችን መሠረት አድርጋችሁ ስትመለከቱ ከእግዚአብሔር ጋር የሚሆን የጸሎትና የዝምታ ጊዜ ያለውን ጥቅም መገንዘብ ትችላላችሁ። ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ የቅርብ ግንኙነት በመንፈስ ለተሞላ ሕይወት ሀይል መሣሪያ ነው።
የግብጽ ኦሮቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባት ዘካርያስ ቡትሮስ እንደ ጻፋት
@yeemariyaam21
@yeemariyaam21
@yeemariyaam21
4.0K viewsedited 04:57