2022-07-28 21:00:11
ቴዎድሮስ እስኪነግሥ ከተሰኘው መጽሐፍ ከገጽ 204-206 ካለው የተወሰደ።
የምትሰማውን ሳይሆን የሚሰማህን ተከተል,!
ኢትዮጵያ የጀብድና መስዋዕትነት እንዲሁም የአሸናፊነት ምልክት እንጂ በምርኮ የምትበዘበዝ የተሸናፊዎች መገለጫ አይደለችም፡፡ ጀግኖቿ በህይወት እያሉም ሆነ በሞታቸው ውድቀትና ባርነትን ድል ነስተው፣ ሀገርና ህዝብን በነጻነት ያቆዩ ናቸው፡፡ በዘመን መፈራረቅ ውስጥ እነዚህ ታላላቅ ሰዎች ለሚወዱት ሀገርና ህዝብ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ከፍ አድርገው ህይወታቸውን ያለስስት ገብረዋል፡፡ እኒህ ከሀገርና ከህዝብ በፊት ራስን መስዋዕት ማድረግ የሚቀድማቸው ቀደምት አባቶቻችን እንዳለመታደል ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እሳት አመድን ወለደ እንደሚባለው ከላይ እስከ ታች የተሰገሰጉ ባለጊዜ ሹመኞች ባላጠለቁት ሱሪ፣ ባልነበሩበት የጦር ግንባር፣ የድል አጥቢያ ሽለላና ፉከራቸውን እያቀለጡ ሀገርን ለባንዳ፣ ህዝባቸውን ለባርነት አሳልፈው ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመረማመጃ ምንጣፋቸውን አንስተው በባዶ እግር ጉዞ እሾህ ተጎዝጉዞ የሚኖሩ ኢትዮጵያ ከኔ ጀመረች ባይ ተራማጆችን መመልከት የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል፡፡ በሰላም ተኝቶ ለማደር ቀርቶ ቆሞ ለመራመድ እንኳን ከእግር በፊት ዋስትና የሆናቸውን የቀደሙት አባቶቻችንን ደምና አጥንት እየከሰሱና እያንኳሰሱ የተያይዞ ገደል ጉዟቸውን ተያይዘውታል፡፡ ይህ ጊዜ የሰጠው ባለ ጠባብ ቅል አዕምሮ የሰፊዋንና ታላቋን ሀገር ነባር ርስት ሸንሽኖ ህዝብን ለመበታተን በመጣደፍ ለሰይጣን ወዶ ገብነቱን በመፍቀድ ሽምጥ የሚጋለብ ፈረስነቱን ተያይዞታል፡፡ ልዩነት እየዘራ የሰው አንገት ያጭዳል፤ ጎተራና ገበታውም የአቤል ስጋና ደም ከሆነ ሰንብቷል፡፡
በዚህ መርህ አልባ የህይወት አዙሪት ቅኝት ብዙኀኑ የውሸት ገናናዎች በእውነት ተፈትነው ይወድቃሉ፡፡ ባለራዕዩ የጥበብ ሰው በአባቶች ቅን አመለካከትና በመንፈሳዊ ጸጋ ከዘመነ መሳፍንት አዙሪት ወጥታ እያበበች የነበረችውን ሀገር ትንሽዬ መንደር ያደረጓትን ሹማምንት በአደባባይ መታገሉ ከሞት በታች የሆነ ብዙ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ ይሁን እንጂ ከራሱ ዝና የቀደምት ሀገሩን ክብርና የህዝብ ነጻነት ለማስከበር ሞትም ቢመጣ ጽዋውን ሊጋተው ወስኖ ጉዞውን በመጀመሩ ምንም ዓይነት ፈተና ከጉዞው ሊያስቆመው አልቻለም፡፡
በጥቂት የሚቆጠር እድሜ ውስጥ ዋጋው ተለክቶ የማይታወቅ ዕልፍ ዘርፈ-ብዙ ስራ የሰራው ጥበበኛ የወገኖቹ የጸብ ጠብመንጃ ላይ በፍቅር ቁሞ የፈሰሰውን ደም ለማድረቅ፣ የተደፋውን ለማቅናት፣ የደረቀውን ለማለምለም ደፋ ቀና እያለ ሲታትር ውቡን የወጣትነት እድሜውን ለሀገሩ ገብሯል፡፡ ቴዲ ከብዙዎቹ የሚለየው የሚሰማውን ውስጡ የሚለውን፣ የሚሰሙትን፣ ጆሯቸውን የሰጡትን እንጂ በየመንገዱ የሚሰማውን አልተከተለም፡፡ ጥላቻን ጆሮው ሲሰማ ውስጡን ፍቅር ገባው፤ መከፋፈልን ጆሮው ሲሰማ አንድ መሆን ውስጡን ገዛው፤ የወደፊቱን ጭንቅ በጆሮው ሲሰማ ልቡ የወደፊቱ ብርሃን አየው፤ ያንንም ሲከተልና ሲያቀነቅን የኖረ የመልካም መሆን አርአያ ጀግና አርቲስት ነው፡፡
መጽሐፉን ከዚህ በታች በተጠቀሱት መደብሮች ማግኘት ይችላሉ።
ስታዲየም ነጃ መጽሐፍ መደብር 0910990259
ለገሀር በጋሻው መጽሐፍ መደብር 0911656729
ለገሀር ማድያ ያሬድ መጽሐፍ መደብር 0913094097
መሳለሚያ ሆናልያት ህንፃ ቢሮ ቁጥር 156 ተኬ ማን ፕሮሞሽን 0911518012 ወይም 0921935862
አራት ኪሎ 0901197837
ፒያሳ አምፒር ታረቀኝ መጽሐፍ መደብር 0983294565
ለበለጠ መረጃ 0975550865 ይደውሉልን።
6.1K views18:00