2022-08-27 00:05:16
† ስንክሳር ነሐሴ 21 †
እንኳን ለቅዱሳት አንስት ኄራኒ ሰማዕት: ንግሥተ ሳባ እና ንግሥት ዕሌኒ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †
†ቅድስት ኄራኒ ሐዋርያዊት ሰማዕት †
† ይህቺ ቅድስት ወጣት መልክ ከደም ግባት: ምግባር ከሃይማኖት: ስም ከመልካምነት የተባበረላት ሰማዕት ናት:: #ኄራኒ ማለት "ሰላማዊት: የተወደደች" ማለት ነው:: አንድም በጥሬው "ሰላምና ፍቅር" ማለት ነው::
ቅድስት ኄራኒ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን በታናሽ እስያ የንጉሥ #ሉክያኖስ ልጅ ናት:: ከተወለደች ጀምሮ ስለ ክርስትና ሰምታ አታውቅም:: ምክንያቱም አባቷ ጣዖት አምላኪ ከመሆኑ ባለፈ ክርስቲያኖችን ይቀጣ ስለ ነበር ነው::
ልጁን ማንም እንዳያገኛት ሲል ንጉሡ ለቅድስት ኄራኒ ቤተ መንግስት ሠራላት:: ማንም እንዳይገባ በዙሪያው 12 አጥር አጠረበት:: ጣዖቶቹን እንድታጥን አገልጋዮችንም ሾመላት::
ምናልባት አጥር ሰውን ሊከለክለው ይችላል:: #እግዚአብሔር ግን እግዚአብሔር ነውና ምንም አይከለክለውም:: ጌታ ደግሞ ይህቺን ወጣት ለወንጌል አገልግሎት ይፈልጋታል:: አንድ ቀን አባቷ: ልጁ ምሑር እንድትሆንለት አለ የተባለ ሽማግሌ ፈላስፋ ቀጠረላት::
ጥበበ እግዚአብሔር ማለት ይሔ ነው:: አባቷ ይሕ ሽማግሌ ማንን እንደሚያመልክ አልተረዳም:: አረጋዊው እጅግ የተዋጣለት ክርስቲያን ነው:: ግን ማንም አያውቅበትም:: አረጋዊው ቅድስት ኄራኒን ዝም ብሎ ሊሰብካት አልወደደም::
መጀመሪያ በስነ ምግባር አነጻት:: ቀጥሎ ግን "ጌታ ሆይ! ጐዳናህን ምራት" እያለ ይጸልይላት ገባ:: ጌታችን ልመናውን ሰምቶታልና ቅድስቷ አንድ ቀን ግሩም ራዕይን አየች::
እርሷ ለማዕድ ተቀምጣ ሳለ: የምሥራቅና የምዕራብ መስኮቶቿም ተከፍተው ሳሉ: በምሥራቁ መስኮት ነጭ ርግብ በአፏ የወይራ ዝንጣፊ (ቆጽለ ዘይት) ይዛ ገባችና ማዕዷ ላይ አኑራው ሔደች:: እርሷን ተከትሎ ደግሞ ንስር በአፉ አክሊል ይዞ ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ሔደ::
በ3ኛው ግን ቁራ: እባብ በአፉ ይዞ በምዕራቡ መስኮት ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ወጣ:: ቅድስት ኄራኒ ያየችው ራዕይ ቢጨንቃት ሽማግሌ መምሕሯን "ተርጉምልኝ" አለችው::
እርሱም "ልጄ ሆይ! ለዘመናት ስጠብቀው የነበረ ምኞቴን ነው ጌታ ያሳየሽ:: የሕልምሽ ትርጉም እንዲህ ነው:- ነጭ ርግብ የመንፈስ ቅዱስ (የሃይማኖት) ምሳሌ ናት:: የወይራ ዝንጣፊው ደግሞ #ማሕተመ_ጥምቀት( #ሜሮን) ነው:: ቁራ የክፉ ነገሥታት ምሳሌ ሲሆን እባብ የመከራ ምሳሌ ነው::
ንስር ድል የመንሳት ምልክት ሲሆን አክሊል ደግሞ የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው:: ልጄ! ክርስቲያን ሆነሽ የሚደርስብሽን ሁሉ ጌታ አሳይቶሻል" ብሎ ተርጉሞላት ተሰናበታት::
እርሷም ወደ ምሥራቅ ዙራ ጸለየች:- "የማላውቅህ አምላክ ሆይ! ወደ እውነትህ ምራኝ" ስትል ለመነች:: በዚያች ሰዓት የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ አጽናናት:: የሚያጠምቃትም እንደሚልክላት ነገራት::
በዚያን ጊዜ አባቷ ገብቶ "ልጄ! ከመሣፍንቱ ላንዱ ልድርሽ ስለሆነ ምን ትያለሽ?" አላት:: "3 ቀን ስጠኝ" አለችውና ሰጣት:: ወደ ጣዖቶቹ ዕለቱኑ ወርዳ "ላግባ ወይስ ይቅርብኝ?" አለቻቸው:: ከቀድሞም በወርቅ የተለበጡ ድንጋዮች ናቸውና ዝም አሉ:: በሙሉ ቀጥቅጣ ሰባብራቸው ተመለሰች::
በዘመኑ #ቅዱሳን_ሐዋርያት(በተለይ እነ #ቅዱስ_ዻውሎስ) በሕይወተ ሥጋ ነበሩና ከቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቤቷ እንደ ተዘጋ ገባ:: ክርስትናን ከጥንቱ እስከ ተፍጻሜቱ አስተምሮ አጠመቃት::
በ3ኛው ቀን አባቷ "ምን መከርሽ?" ቢላት "የእኔ ምክር #መርዓተ_ክርስቶስ(ሰማያዊ ሙሽራ) መሆን ነው" አለችው:: አባቷ ደነገጠ:: እጅግ ስለ ተናደደ ወደ አደባባይ አውጥቶ: አስሮ መሬት ላይ ጣላትና በመቶ የሚቆጠሩ ፈረሶች እንዲረግጧት አደረገ::
በወቅቱ ሰው የሚጠብቀው የአካሏን ቁርጥራጭ ነበር:: ነገር ግን ጌታ ከእርሷ ጋር ነበርና ልብሷ እንኩዋ ጭቃ አልነካም:: አባቷ ንጉሥ ሉክያኖስና ሠራዊቱ ያዩትን ማመን አልቻሉም:: ሁሉም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው "ከክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም" አሉ:: ቅድስት ኄራኒ ምንም ሳትናገር ይህንን ሁሉ ሰው ማረከች::
ወዲያውም ንጉሡ መልእክተኛ ልኮ: የቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዝሙርን አስጠርቶ: ከነ ቤተሰቦቹ ተጠመቀ:: የዚህን ዓለም ክብር ንቆም ንግሥናውን ተወ:: የጸሎት ሰውም ሆነ:: የቅድስት ኄራኒ ተጋድሎ ግን ቀጠለ::
በአካባቢው የነበረ ንጉሥ መጥቶ የአባቷን መንግስት ቀማ:: እርሷንም እጅግ አሰቃያት:: እርሱ አልፎ አርማንዮስ የሚባል ንጉሥ እንዲሁ አሰቃያት:: እርሱም አለፈ:: ከእርሱ ቀጥሎ የመጣው ንጉሥ ብዙ መከራዎችን በእርሷ ላይ አደረሰ:: በጦርም ጐኗን ወግቶ ገደላት::
ከጥቂት ሰዓታት በሁዋላ ግን ልክ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ተነስታ ጠራችው:: በጣም ደንግጦ "አምላክሽ አምላኬ ነው" ሲል አመነ:: ከ30,000 በላይ ሠራዊቱን ይዞም ተጠመቀ::
ቅድስት ኄራኒ በቀረ ሕይወቷ በስብከተ ወንጌል እስያን አድርሳለች:: ጌታ አብርቶላት: እርሷም አብርታ: እልፍ ፍሬን አፍርታ: በዚህች ቀን ዐርፋለች:: የሐዋርያትንም: የሰማዕታትንም አክሊል ተቀዳጅታለች::
ንግሥተ ሳባ
† ይሕቺ ኢትዮዽያዊት ከ3 ሺ ዘመናት በፊት የነበረች ደግ እናት ናት:: በሥጋዊ ደረጃ ከታንዛንያ እስከ #የመን ያስተዳደረች ስመ ጥር ንግሥት ስትሆን በመንፈሳዊው ደረጃ ደግሞ እግዚአብሔር የቀባውን ሰው ፍለጋ ወደ #ኢየሩሳሌም ተጉዛለች::
ከዚያውም አምልኮተ እግዚአብሔርን ከሥርዓተ ኦሪት ጋር አምጥታለች:: ድንግልናዋን ለታላቁ #ንጉሥ_ሰሎሞን ሰጥታ #ምኒልክን ወልዳለች:: ይህቺ ንግሥት በጌታችን (በፈጣሪ) አንደበትም ተመስግናለች:: (ማቴ. 12:42) በስምም " #ሳባ: #አዜብና #ማክዳ ተብላ ትታወቃለች:: ዛሬ ዕለተ ልደቷ ነው::
† ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት †
† ይሕቺ ቅድስት የቅዱስ #ቆስጠንጢኖስ እናቱ: የመስቀሉ ወዳጅ: የቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የሆነች ክብርት እናት ናት:: ይህቺም ቅድስት የተወለደቺው በዚሁ ዕለት ነው::
† የቅዱሳት እናቶቻችን አምላክ እህት እናቶቻችንን ከክፋትም: ከጥፋትም: ይሠውርልን:: ለሃገርም: ለሃይማኖትም የሚጠቅሙ ሴቶችንም ጌታ አይንሳን:: በረከታቸውም ይደርብን::
† ነሐሴ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (6ኛ ቀን)
2.ቅድስት ኄራኒ ሐዋርያዊት (ሰማዕት)
3.ቡርክት ንግሥተ ሳባ (ልደቷ)
4.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት (ልደቷ)
† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ
2.አበው ጎርጎርዮሳት
3.አቡነ ምዕመነ ድንግል
4.አቡነ አምደ ሥላሴ
5.አባ አሮን ሶርያዊ
6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ
††† " #ንግሥተ_አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስታ ትፈርድበታለች:: የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና:: እነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ::" †††
(ማቴ. 12:42)
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
ቤተሰብ ይሁኑ
https://t.me/Sinksar
https://t.me/Sinksar
https://t.me/Sinksar
179 views21:05