Get Mystery Box with random crypto!

ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ)

የቴሌግራም ቻናል አርማ sigewe — ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ)
የቴሌግራም ቻናል አርማ sigewe — ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ)
የሰርጥ አድራሻ: @sigewe
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 7.53K
የሰርጥ መግለጫ

❤ በየቀኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስንክሳር የሚታሰቡ የቅዱሳን ታሪክ፣ የኢትዮጵያኑ ቅዱሳን በየበዐላቸው ቀን አስደናቂ፣ አስገራሚ ገድላቸው፣ ቃል ኪዳናቸው፣ የቅዱሳን ሰላምታ፣ የየቀኑ የቅዳሴ መልዕክታ፣ የሐዋርያት ሥራ፣ የወንጌል ጥቅስ እና ምስባክ ይቀርብበታል።
❤ የፌስቡክ አድራሻዬ ሊንክ https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886

Ratings & Reviews

2.33

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

1

4 stars

0

3 stars

0

2 stars

0

1 stars

2


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 2

2022-08-29 12:41:16 በዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ከሆነው በኋላ ሐይቅ በሚባል ቦታ ወደሚኖር ወደ ኢየሱስ ሞዓ የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው ሔዶ ከእርሱም የምንኲስና ልብስ ቀሚስና ቅናትን ተቀበለ። ከዚያም ወደ ደብረ ዳሞ ሔዶ ለአቡነ አረጋዊ አራተኛ ከሆነ ከአባ ዮሐኒ ዘንድ ቆብንና አስኬማን ተቀበለ። ሁለተኛም ወደ ኢየሩሳሌም ሒዶ ከከበሩ ቦታዎችና ከሊቀ ጳጳሳቱ ቡራኬን ተቀበለ።

በዚያም ወደ ሸዋ ምድር ተመልሶ የአባቱ ወንድም ልጅ የሆነ አባ ዜና ማርቆስን አገኘው በወግዳ በረሀም በአንድነት ኖሩ ከዚያም ግራርያ ወደ ሚባል አገር ሒዶ በኰረብታ መካከል ዋሻ አዘጋጅቶ ተቀመጠ በቀንም በሌሊትም ከዚያ አይወጣም ነበረ ከጥቂት ቅጠልም በቀር እህልን አይቀምስም መጠጡም ጥቂት ውኃ ነው። ብዙ ወንዶችና ሴቶች ወደርሱ መጥተው መነኲሳቶች ሆኑ በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ መኝታ ላይ ተኝተው ያድራሉ እርስበርሳቸውም አይተዋወቁም እነርሱም እንደ ሕፃናት ናቸው በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜም በአንድነት ይቆማሉ በዘመኑ ሰይጣን ስለ ታሠረ ወንዱ ሴቷን ሴት እነደሆነች አያውቅም እንዲሁም ሴቷ ወንዱን ወንድ እንደሆነ አታውቅም።

በዚህም በኋላ መጠጊያ ሠርቶ በፊቱ በኋላው በቀኙ በግራው የተሳሉ ፍላጻዎችን ተከለ ይህንም ማድረጉ በመደገፍና በመተኛት እንዳያርፍ ነው በዚያም እግሩ ከቅልጥሙ እስቲሰበር ሰባት ዓመት ቆመ። በዚያም ወራት ምንም የዕንጨት ፍሬ ወይም ቅጠል ሳይቀምስ ውኃም ሳይጠጣ ኖረ።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርቶስ ወደርሱ መጣ ከእርሱም ጋራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የከበሩ ነቢያትና ሐዋርያት ሁሉም ሰማዕታትና ጻድቃን የጳጳሳት አለቆች የመላእክት አለቆችም ከሠራዊቶቻቸው ጋራ አሉ።

መድኃኒታችንም እንዲህ አለው "ወዳጄ ሆይ አንተ በመከራዬ መሰልከኝ እኔም በመንግሥቴ ከእኔ ጋራ እንድትመስለኝ አደርግሃለሁ። እነሆ የዚህ ዓለም ድካምህ ተፈጸመልህ በእኔ ዘንድም የምቀበለው ሆነ ከእንግዲህስ መንግሥተ ሰማያትን ትወርስ ዘንድ ና። እነሆ ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ገድልህን ለሚጽፍ ለሚያነበውና ለሚሰማውም ቤተ ክርስቲያንህን ለሚሠራ በስምህ መባ ለሚሠጥ ለድኆችም በስምህ ለሚመጸውት በመታሰቢያህም ቀን ለሚቆርብ ስለ አንተ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሉ እኔ እስከ ዐሥር ትውልድ እምርልሃለሁ"። አባታችንም እጅግ ደስ አለው ለጌታችንም ሰገደ ጌታችንም ከእርሱ ዘንድ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ።

ከዚህም በኋላ አባታችን በንዳድ በሽታ ታመመ ዕድሜውም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀን ሆኖት በለመለመ ዕርጅና ነሐሴ 24 ቀን ዐረፈ። በመዘመርና በማመስገን አክብረው ገንዘው በዋሻው ውስጥ ቀበሩት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን ተክለ ሃይማኖት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

+ + +
አቡነ ቶማስ ዘመርዓስ፦ የዚህንም አባት ትሩፋቱንና ገድሉን ሰው ተናግሮ ሊፈጽመው አይችልም እርሱ አስቀድሞ በጾም በጸሎት በሰጊድ ቀንና ሌሊትም በመራራት ተጠምዶ የሚኖር ነው ። ከዚህም በኃላ መርዓስ ለሚባል አገር ኤጲስቆጶስ ይሆን ዘንድ የክብር ባለቤት ጌታችን መረጠው መንጋውንም እንደ ሐዋርያት ጠበቀ ። ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስም በነገሠ ጊዜ ክርስቲያኖችን ያሠቃያቸው ዘንድ ከመኳንቶቹ አንዱ ወደዚያች አገር ደረሰ እርሱም ቅዱስ ቶማስን ወደርሱ ያቀርቡት ዘንድ ጭፍሪቹን ላከ እነርሱም እየደበደቡ በምድር ላይ እየጎተቱ ወሰዱት ደሙም እንደውኃ ፈሰሰ።

ከዚህም በኃላ መኰንኑ ቅዱስ ቶማስን "ለአማልክት ስገድ" አለው ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት "እኔ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለረከሱ ጣዖታት የሚሰግድ ሁሉ የተረገመ ነውና"። መኰንኑም ተቆጥቶ እጅግ የበዛና ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃየው የነዳጅ ድፍድፍና አፍልተው በላዩ በአፉና በአፍንጫው ውስጥ ጨመሩ እንዲህም እያደረጉበት እስከ ብዙ ዘመናት ኖረ።

የእሊህ ከሀዲያን ልባቸው እንደ ድንጊያ የጸና ስለሆነ ቅዱስ ቶማስ ቶሎ እንዲሞት አልፈለጉም። ሌሎች ብዙዎች ሰዎችን ያሰፈሩአቸው ዘንድ የክብር ባለቤት ክርስቶስንም ይክዱት ዘንድ የሥቃዩን ዘመን አስረዘሙ እንጂ። እርሱ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የጸና ነውና ማሠቃየቱን ከሀድያን በተቸነፉ ጊዜ ስለ ስሕተታቸውም ይዘልፋቸው ስለነበር ስለዚህ በጨለማ ቦታ ጣሉት በዚያም ሃያ ሁለት ዓመት ኖረ።

ከሀድያንም በየዓመቱ ወደርሱ ገብተው ከሕዋሳቱ አንዱን ይቆርጣሉ። በዚያም ቦታ አፍንጫውን ከንፈሮቹን ጆሮዎቹን እጆቹንና እግሮቹን ቆረጡ መንጋዎቹም ያረፈ መስሏቸው በየዓመቱ መታሰቢያውን ሲያደርጉ ኖሩ። ነገር ግን አንዲት ክርስቲያናዊት ሴት በጣሉት ጊዜ ስለአየችው ቦታውን ታውቅ ነበር እርሷ በሌሊት ወደርሱ ተሠውራ በመሔድ ትመግበዋለች ። ጻድቅ ቁስጠንጢኖስም እስከ ነገሠና የቀናች የክርስቶስን ሃይማኖት ክብር እስከ ገለጠ ድረስ እንዲህ ሲሠቃይ ኖረ። ይህም ንጉሥ ክርስቶስን በመታመን የታሠሩ እሥረኞችን ሁሉ በሀገሮች ሁሉ በወህኒ ቤት ያሉትን ይፈቷቸው ዘንድ አዘዘ።

ይችም ሴት ሒዳ ስለ ቅዱስ ቶማስ ከእርሱ የሆነውን ሃያ ሁለት ዓመት ተጥሎ እንደኖረ ለካህናቱ ነገረቻቸው በውስጡ ወደሚኖርበትም ቦታ መራቻቸው። እነርሱም አንሥተው ተሸከሙት እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አደረሱት በቤተ መቅደሱም ፊት ለፊት በወንበሩ ላይ አስቀመጡት ምእመናንም ሁሉ ወደርሱ እየመጡ ከእርሱ ይባረኩና የተቆረጡ ሕዋሳቱን ይሳለሙ ነበር።

ንጉሥ ቂስጠንጢኖስም የከበሩ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳትን የአንድነት ጉባኤን በኒቅያ አገር በሰበሰበ ጊዜ ይህ የከበረ ቶማስ ከእሳቸው አንዱ ነው። ንጉሡም ወደ እነርሱ ገብቶ ሰላምታ ሰጣቸውና ከእርሳቸውም ቡራኬ ተቀበለ። የዚህ የቅዱስ ቶማስን ተጋድሎውን በነገሩት ጊዜ ወደርሱ ቀርቦ ሰገደለት ሕዋሰቱም ከተቆረጡበት ላይ ተሳለመው አዝኖና እጅግም አድንቆ ሕዋሳቱን ዳሠሠው ፊቱንና ዐይኖቹን አሻሸው።

ከሀዲ አርዮስንም ተከራክረው ከረቱ በኃላ አውግዘው ለይተው ከወገኖቹ ጋር ከቤተ ክርስቲያን አሳደዱት። ከዚህም በኃላ መንፈስ ቅዱስ እንደ አስተማራቸውና እንደመራቸው የሃይማኖትን ትምህርት በአንደበታቸው ተናገሩ ሕግና ሥርዓትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍርድንም ሠሩ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቶማስ ወደ መንበረ ሢመቱ ሔደ ካህናቱንና መንጋዎቹን ሁሉ ሰብስቦ አነበበላቸው እርሱንም እንዲአስተውሉት እንዲጠብቁትም በመጠበቅም እንዲጸኑ አዘዛቸው። ጥቂት ዘመናትም ከኖረ በኃላ በሰላም በፍቅር ነሐሴ 24 ቀን ዐረፈ የሹመቱም ዘመን አርባ ዓመት ነው በዚህም እግዚአብሔርን አገለገለው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በተጋዳይ በአቡነ ቶማስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 24 ስንክሳር።

+ + +
600 viewsAschalew Kassaye, 09:41
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-29 12:41:15 "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

ነሐሴ ፳፬ (24) ቀን።

እንኳን ለኢትዮጽያውያን ጻድቃን ለታላቁ አባት ለከበረ ሐዲስ ሐዋርያ ለትሩፋትም መምህር ለሆነ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት በዓለ ለዕረፍትና ለታላቁ አባት ለክርስቶስ ምስክር ለሐዋርያው ለመርዓስ አገር ኤጲስ ቆጶስ ለተጋዳይ ለቅዱስ አባት ቶማስ በዓለ ለዐረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

+ + +
የዕለቱ አንገሪጋሪ ግእዝ ዜማ፦ "አባ አቡነ አቡነ መምህርነ እምአእላፍ ኅሩይ ሐውፅ እምሰማይ ብርሃነከ ከመ ንርአይ አማን ተክል ሃይማኖት ፀሐይ"፡፡ትርጉም፦ አባ አባታችን አባታችን መምህራችን ከብዙዎች የተመረጥህ ከሰማይ ጎብኝ ብርሃንን እንድናይ በእውነት ተክለሃይማኖት ፀሐይ።

+ + +
የዕለቱ ዓራራይ ዜማ፦ "ተክለ ሃይማኖት ጸመወ እምገድለ ቅዱሳን ምክዕቢተ ከመ ይፍረይ ፍሬ ህየንተ አሐዱ ሠላሳ ወስሳ ወምዕተ ኢያጽነነ ትልሞ ወኢገብአ ድኅሪተ እመንፈስ ቅዱስ ነሢኦ አሦተ"፡፡ ትርጉም፦ ተክለ ሃይማኖት ደከመ ከቅዱሳን ገድል እጥፍ ድርብ ስለ አንድ ፈንታ ሠላሳ ስልሳ እና መቶ ፍሬ ያፈራ ዘንድ ባዪን አላጓደለም ወደ ኋላም አልተመለሰም ከመንፈስ ቅዱስ ዋጋውን ተቀብሎ ወስዶ። ከሊቁ ቅዱስ ያሬድ ድጓ።
+ + +
ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፦ የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ጸጋ ዘአብ የእናቱ ስም እግዚእ ኀረያ ነው እሊህም ቅዱሳን ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ብርሃንን ላበሩ ካህናት ከወገኖቻቸው የሆኑ ናቸው። እግዚእ ኀረያም መካን ስለሆነች ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እያዘኑ ሲጸልዩ ኖሩ። በዚህም ነገር እያሉ የዳሞት ገዥ ሞተለሚን ሰይጣን አነሣሣው የሸዋን አውራጃዎች እስከ ጅማ እስከ ገዛ ድረስ። የሀገር መኳንንቶችም በየተራቸው ሚስቶቻቸውን ይሰጡታል። ከማረከውም ደምግባት ያላቸውን ሴቶች ያገኘ እንደሆነ ቁባቶች ያደርጋቸዋል።

በዚያም ወራት ወደ ጽላልሽ ደርሶ ብዙ ክርስቲያኖችን ገደለ ከእርሳቸውም የሚበዙትን ማረከ ጸጋ ዘአብም ከግድያ ፍርሃት የተነሳ ሸሸ አንድ ወታደርም ተከተለው እርሱም ወደ ባሕር ተወርውሮ ገባ በእግዚአብሔርም ፈቃድ በባሕሩ ውስጥ ተሸሸገ። ሚስቱን እግዚእ ኀረያንም ወታደሮቹ ማረኳት ወደ ሞተለሚም አደረሷት ባያትም ጊዜ ውበቷንና ላህይዋን አደነቀ በልቡም እጅግ ደስ ብሎት ብዙ ሽልማትን ጌጥን ሰጥቷት በሽልማትና በጌጥ ሁሉ ሸለማት አስጌጣትም የጋብቻ ሥርዓትንም ማዘጋጀት ጀመረ ለሠርጉም እንዲሰበሰቡ ወደመኳንንቶቹ ሁሉ ላከ።

እግዚእ ኀረያም ይህን በሰማች ጊዜ ከአረማዊ ጋር አንድ ከመሆን ያድናት ዘንድ በብዙ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር ጸሎትን አደረገች። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በብርሃናዊ ክንፉ ተሸክሞ ከዳሞት አገር ወደ ምድረ ዞራሬ አድርሶ ወዲያውኑ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ በሴቶች መቆሚያ አቆማት። ባሏ ጸጋ ዘአብም ከማዕጠንት ጋራ በወጣ ጊዜ እንደተሸለመች ቁማ አያት አድንቆ በልቡ "ይቺ ሴት ምንድን ናት ወደዚህስ ማን አመጣት" አለ። የማዕጠንቱንም ሥራ ጨርሶ ወጣ በጠየቃትና በመረመራት ጊዜ እርሷ ሚስቱ እግዚእ ኀረያ እንደሆነች አገኛት እርሷም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እግዚአብሔር ያደረገላትን ነገረችው።

ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በአንዲት ሌሊት ተገለጠላቸው የዜናው መሰማት በዓለሙ ሁሉ የሚደርስ የተባረከ ልጅ ይወልዱ ዘንድ እንዳላቸው ነገራቸው አበሠራቸው። ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ይህ ቅዱሱ ተፀንሶ በታኀሣሦ ወር በሃያ አራት ተወለደ በጸጋ ዘአብና በእግዚእ ኀረያ ቤታቸው ታላቅ ደስታ ሆነ ከዘመዶቻቸውና ከጐረቤቶቻቸው ጋራ ደስ አላቸው።
ለክርስትና ጥምቀትም በአስገቡት ጊዜ ፍሥሓ ጽዮን ብለው ሰየሙት። ሕፃኑም አደገ ድንቅ ተአምራትንም እያደረገ ዕውቀትንና ኃይልንም ተመልቶ በመንፈስ ቅዱስ ጸና።

ከዚህም በኋላ ዲቁና ይሾመው ዘንድ አባ ጌርሎስ ወደ ተባለ ጳጳስ ወሰዱት በዚያንም ዘመን በዛጔ መንግሥት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን ነበር። ወደ ጳጳሱም በአደረሱት ጊዜ "ይህ ልጅ የተመረጠ ዕቃ ይሆናል" ብሎ ትንቢት ተናገረለት። የዲቁና ሹመትንም ተቀብሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።

ጐልማሳ በሆነ ጊዜ አራዊትን ሊያድን ወደ ዱር ሔደ። ቀትር ሲሆንም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልኩ የሚያምር ጐልማሳ አምሳል በቅዱስ ሚካኤል ክነፍ ላይ ተገለጠለትና እንዲህ አለው "ወዳጄ አትፍራ እንግዲህ የኃጢአተኞችን ነፍስ ወደ ሕይወት የምታጠምድ ትሆናለህ እንጂ አራዊትን የምታድን አትሆንም ስምህም ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንደ ኤርምያስና እንደ አጥማቂው ዮሐንስ እኔ ከእናትህ ማኀፀን መርጬ አከብሬሃለሁና እነሆ በሽተኞችን ትፈውስ ዘንድ ሙታንንም ታሥነሣ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠሁህ ርኩሳን አጋንንትንም ከሁሉ ቦታ ታሳድዳቸዋለህ"። ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ገንዘብን ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በተነ "ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል" እያለ ቤቱን እንደ ተከፈተ ትቶ ምርኩዙን ይዞ በሌሊት ወጣ።

ከዚህም በኋላ ወደ ጳጳስ ሔዶ የቅስና ሹመት ተቀብሎ ለሸዋ አገር ሁሉ ወንጌልን መስበክ ጀመረ። ዐሥራ ሁለት ሽህ ሦስት መቶ ነፍስ ያህል አጠመቀ ለጣፆት የሚሠውበትን ሁሉ ሻረ በውስጡ የሚኖሩ አጋንንት እስከሸሹ ድረስ ዐፀዶቻቸውን ሁሉ ቆረጠ።

ሁለተኛም ወደ ዳሞት ምድር ሔዶ ብዙ ሟርተኞችንና አስማተኞችን ጠንቋዮችን አሳመነ ከሀዲ ሞተለሚም ብዙ ወራት ተቃወመው በጉማሬ ማጥመጃ ውስጥ በመጨመር ብዙ ጊዜ ወደ ገደል ወረወረው እርሱ ግን በደኀና ይመለሳል ደግሞ ሊወጋው ጦር ወረወረ ጦሩም ተመልሶ እጁን ወግቶ ተጠመጠመበት በተሠቃየም ጊዜ አባታችንን ለመነው እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሳምኖ አዳነው የተጠመጠመበትንም ጦር ፈታለት ቀናውን መንገድ የሚያጣምሙ ሟርተኞችንም አጠፋቸው።

ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት ጌታችን ስም ያደረገውን ድንቅ ተአምራቱን አይተው የአገር ሰዎች ሁሉም ከንጉሣቸው ጋራ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶላቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት አስተማራቸው በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው ከዚህም ሁሉ ጋራ በጾም በጸሎት በስግደት ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ ተጠምዶ ይጋደል ነበር። ዜናውንም ሰምተው ወደርሱ የሚመጡትን የነፍሳቸውን ድኀነት ያስተምራቸዋል የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስን በማመን ያጸናቸዋል።

ከዚህ በኋላ በኤልያስ ሠረገላ ተቀምጦ ወደ አምሐራ ሀገር ሔደ በገድል ተጸምዶ ወደሚኖር መነኰስ ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል በአንዲት ቀን ደርሶ በዚያ እንደባሪያ ሲያገለግል ኖረ በአንድነት የሚኖሩ መነኰሳትንም ያገለግላቸው ነበር የሞተውንም እስከማንሳት ድረስ ከደዌያቸው ይፈውሳቸው ነበር።
637 viewsAschalew Kassaye, 09:41
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-29 11:02:50
874 viewsAschalew Kassaye, 08:02
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-29 11:02:36 ከዚህ በኋላ ጌታ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራን እናቴ ማርያምን ወደ ምትኖርበት ውሰዳት" አለው። ቅዱስ ሚካኤልም "ጌታ ወደ አዘዘልሽ ቦታ እንሒድ" አላት። ቅዱስ ሚካኤልም ይዟት ሲሔድ እጅግ የሚያስደነግጥና ከፀሐይ ከጨረቃ ከዋክብት ብሃርን ይልቅ ብርሃኑ የሚያበራ መንበር አየች። ይህን መንበር በአየችውም ጊዜ በጣም አድርጋ ወደደችው።

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም "ክርስቶስ ሠምራ ምን ትመለከቻለሽ" አላት። "ያን ቡሩህ የሆነ መንበር እመለከታለሁ" አለችው። "ይህ መንበር ለአንቺ ቢሆን ትወጃለሽን" አላት። "አዎን ጌታዬ ለእኔ ቢሆን እወዳለሁ" አለችው። "እንግዲያውስ ለአንቺ የተዘጋጀ ነው" አላት። በዚያ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል "ጌታዬ መኖርያሽ እናቴ ከማርያም ጋር ነው ብሎኝ አልነበረምን"። ታዲያ እንዴት ይህ መንበር ለአንቺ የተዘጋጀ ነው ትለኛለህ" አለችው። መላአኩም "ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ለምን ቸኮልሽ" አላት። ይህን ካአለ በኋላ ወደ እመቤታችን ወደ ድንግል ማርያም መኖርያ ወስዶ አደረሳትና። "ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እግዲህ ተመልከች" አላት። በተመለከተቻት ወይም ባየቻት ጊዜም ማርያም ወይም ሰው አልነበረችም ነገር ግን ከፍታዋ ወይም ቁመቷ የላቀ ተራራ ነበረች እንጂ።

ቅዱስ ሚካኤልም "ማርያም ነች ብኸኝ አልበረምን ታዲያ እንዴት ተራራ ልትሆን ቻለች" አለችው። ያን ጊዜ ምሥጢሯ እስኪገለጽልሽ ድረስ ትንሽ ታገሽ" አላት። ከዚያም ቀና ብላ ብትመለከት እመቤታችን ድንግል ማርያምን አየቻትና እንደአሞራ በራ አንገቷን አቅፋ ሳመቻት። እመቤታችንም "ክርስቶስ ሠምራ ሆይ አንቺ የተባረክሽ ነሽ አንቺንም የሚያፈቅር የገድልሽን ዜና የሚሰሙ ሁሉ የተባርኩ የተመሰገኑ ናቸው" በማለት ሳመቻት። ይህንም ከአለቻት በኋላ በቀኟ አስቀመጠቻት...።

ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ አባ ይስሐቅ የሚባል መነኵሴ ከእናታችን ከክርስቶስ ሠምራ ዘንድ ቢሄድ ሥጋዋ ብቻ ወይም አስከሬኗ በጉድጎድ ውስጥ እንደተተከለ ምሰሶ ወይም ዓምድ ቆሞ አገኘው። ነፍስዋ ከሥጋዋ ያልተለየች ወይም በሕይወት ያለች መስሎት ነበርና "እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ባርኪኝ" አላት። የሚመልስለት ቢያጣ ወደ ወደርስዋ ቀረበና ሥጋዋን ዳሰሰው። እንደ ዐረፈችም በአወቀ ጊዜ ፈጽሞ ደነገጠ ከመሬት ላይ እየወደቀ እየተነሣ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።

መነኰሳቱን ሁሉ ያለቅሱላት ዘንድ ጠራቸው። መነኰሳቱም እየተሽቀዳደሙና እየተሯሯጡ መጥተው አርፋ አገኙአት። በዚህ ጊዜ "አንቺን የተሸከመች ማኅፀን የተባለገች ነች አንቺንም ያጠቡ ጡቶች የተመሰገኑ ናቸው" እያሉ ጽዕኑና መራራ ልቅሶን አለቀሱ።

ከዚህ በኋላ አባ ይስሐቅ ሥጋዋን ወይም አስከሬኗን በንጹሕ በፍታ ገንዞ በሳጥን አድርጎ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቀበራት። መነኰስ ይስሐቅም ወደ በዓቱ መመለሱ ቀርቶ በዚያው ቤተ ክርስቲያኖ በስተ ምሥራቅ በኩል በቁመቱ ልክ ጎድጎድ አስቆፍሮ በውስጧ ገባ።

ከዚያም ከጎድጎዱ ውስጥ ገብቶ "ከእንግዲህ እስክሞት ድረስ እንደ እናቴ ክርስቶስ ሠምራ ከዚህ ጎድጎድ አልወጣም" በማለት ወሰነ። ይህንንም ካአለ በኋላ መሪር እንባ እያለቀሰ እህል ሳይቀምስ እስከ 40 ቀን ተቀመጠ። ከ 40 ቀን በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየችና በእናታችን በክርስቶስ ሠምራ አማላጅነትና ልመና ፍጹም መንግሥተ ሰማያትን ወረሰ።

እናታችን ክርስቶስ ሠምራ በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ የኖረችው ሦስት መቶ ሰባ አምስት (375) ነው። ከእናታችን ከቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቷም ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ።

+ + +
አቡነ ጊዮርጊስ ዘግሽ፦ ሀገራቸው ጎጃም ግሽ ዓባይ ሲሆን የታላቁ ጻድቅ አባት የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የአክስት ልጅ ናቸው። የተፀነሱትም ሆነ የተወለዱት በመልአክ ብሥራት ነው፡፡ ሰማዕትነት ለመቀበል ወደ ፋርስ በመሄድ ለ9 ሺህ ሰማዕታት መሪ ሆነው ጣዖትን ካጠፋ በኋላ በሰይፍ ተሰይፈው ሰማዕት የሆኑ ታላቅ አባት ናቸው። እመቤታችን ለዐፄ ካሌብ ተገልጻ የጻድቁን ዐፅም ወደ ሀገራችን እንዲመጣው ስላዘዘችው ዐፄ ካሌብም ዐፅማቸውን አስመጥቶ በጣና ቂርቆስ አስቀምጦታል። ከአባታችን አቡነ ጊዮርጊስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸም ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳንና ቅዱሳን በዓላት።

በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።

@sigewe

https://t.me/joinchat/AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA
729 viewsAschalew Kassaye, 08:02
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-29 11:02:36 ነው" አላት። ይህንንም በአላት ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ሁሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔርንም ፈጽማ አመሰገነች።

+ + +
ስለ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ዕረፍት፦ ከዚህ በኋላ በአዲስ ተጋድሎ ጀመረች። ደናግሉን ልጆቿን ሰበሰበችና "ከእግዲህ እርስ በራሳችሁ በመፈቃቀር ኖሩ እግዚአብሔርም በመፍራት ተቀመጡ" አለቻቸው። ይህንንም ከአለች በኋላ በ1079 ደናግል ወይም መነኰሳት አስተዳዳሪ እመ ምኔት ሾመችላቸው። "ከወሰንኩላችሁ ሕግ ወይም ከሰራሁላች ሥርዓት አትተላለፉ ከእግዲህ ከዛሬ በስተቀር በመንፈስ እንጂ በሥጋ አንገናኝም እና" አለቻቸው። ይህንንም ተናግራ ከእነርሱ ስትለይ አንዲት መነኵሲት ወይም መበለት ጠርታ ሹል የሆኑ ብረቶች አምጭልኝ" ብላ አዘዘቻትና አመጣችላት።

ከዚያም በእናታችን ክርስቶስ ሠምራ በቁመቷ ልክ ጎድጎድ አስቆፈረችና በውስጡ ዕፀ ከርካዕ ወይም የሎሚ እንጨት አስተከለችበት። ዳግመኛ "ከእግዲህ እግዚአብሔር ይቅር እስከ አለኝ ድረስ ከዚህ አልወጣም" ብላ ከጎድጎዱ ውስጥ ገባች። ሦስት የተሳሉ ጦርች በፊቷ ሦስት ጦር በኋላዋ፣ ሦስት ጦር በቀኝ ጎና፣ ሦስት ጦር በግራዋ ጎን ተከለች። መበለቲቱም የፊጢኝ ወይም የኋሊት በገመድ አሰረቻት። ከዚህም በኋላ ስለ ዓለሙ ሁሉ ሕዝብ ይልቁንም ለኢትዮጵያ ሰዎች አጥብቃ ትጸልይና ታዝን ጀመር።

በዚህ አይነት ተጋድሎ ሰውነቷን ወይም ሥጋዋን በልዩ ልዩ ፀዋትወ መከራ ስትፈትና ኖረች። ፈጥና በክንፈ ረድኤት ወደ በዓቷ የምትመለስበት ጊዜ አለ። በዚህ አይነት ግብር ለብዙ ዘመን ኖረች። በምትሰግድበት ጊዜ ወደፊት ስትል ደረቷን ወደኋላ ስትል ጀርባዋን ወደቀኝ ስትል ቀን ጎኗን ወደግራ ስተል ግራ ጎኗን ጦሩ እየወጋት ከቊስሉ የተነሣ ጦሩ የወጋት ገመዱ የከረከራት መላ ሰውነቷ ሸቶ ተልቶ ለዐሥራ ሁለት ዓመት ተጋድሎ አደረገች።

እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ግን እግዚአብሔር ኃይል ጸንታለችና ከጉድጉዳ ወጥታ በጣና ባሕር ውስጥ ገብታ እንድትጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ አዘዛት ከዚያም በባሕሩ ውስጥ እየጸለየች ሦስት ዓመት ተቀመጠች።

ከሦስት ዓመት በኋላ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በጣና ባሕር ውስጥ ሳለች ለጌትነቱ ክብር መሰገድ የሚገባው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደእስዋ መጣ። ከሱም ጋር ቅዱሳን ሚካኤል፣ ገብርኤልና ሩፋኤል እናቱ ማርያም መጡ። ዐሥራ አምስቱ ነቢያት ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሰባ ሁለቱ አርድእት ጻድቃን ሰማዕታት ደናግልና መነኰሳት ሌሎች ሁሉም በየሥርዓታቸውና በየማዕረጋቸው በየነገዳቸው መጡ። ኄሮድስ ያስፈጃቸው ሕፃናት አለቃቸው ሕፃኑ ቂርቆስን ተከትለው እደዚሁም ዘጠና ዠጠኙ ነገደ መላእክት በየነገዳቸውና በየወገናቸው መጡ።

ከነዚህ ሁሉ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት መጥቶ "ልጄ ሆይ ስሚ ጆሮሽን አዘንብይ ወገንሽንና ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ውበትሽን ይወዳል እርሱ ጌታሽ ነውና" እያለ በገናውን ይደረድር ነበር። እንዲህም እያለ በሚዘምርበት ጊዜ በዚያ ያሉ ቅዱሳኖች በሙሉ "የእግዚአብሔር ባለሟል ወይም ወዳጅ ይህች ክርስቶስ ሠምራ በእውነት ብፅዕት ነች" እያሉ ዘመሩ።

በዚያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዛሬ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ላስተላልፍሽ መጥቻለሁ" አላት። "ድካምሽ ወደዕረፍት ኃዘንሽ ወደ ደስታ ችግርሽ ወደ ብልጽግና ተለውጦልሻል። እውነት በእውነት እልሻለሁ ወይም እነግርሻለሁ በፍጹም ደስታ መታሰቢያሽን ያደረገ በመንግሥተ ሰማያት አስደስተዋለሁ። በችግሩ ወይም በጭንቁ ጊዜ በመታመን ስምሺን ቢጠራ እኔ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ አድነዋለሁ።

የገድልሽን ዜና የሚናገረውን መጽሐፍ የጻፈ ወይም ያጻፈ እኔ ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ እጽፍላቸዋለሁ። ቤተ ክርስቲያንሽን የሠራ ወይም ያሠራ ያሣነፀ ወይም ያነፀ እኔ በመንግሥተ ሰማያት ንጹሕ አዳራሽ አዘጋጅለታለሁ። በስምሽ ለተራበ ያበላ እኔ በዕለተ አርብ ከተቆረሰው ሥጋየ አበላዋለሁ። በስምሽ ለተጠማው እፍኝ ውሃ ያጠጣ እኔ በዕለተ አርብ ከጎኔ በሰሰው ደሜ አረካዋለሁ። በዓልሽ በሚከበርበት ዕለት ጧፍ፣ ዕጣን፣ ወይም ዘይት ንጹሕ ስንዴ የመሰለውንም ሁሉ መባ ያገባ መሥዋዕቱን እንደ አብርሃምና እንደ መልከ ጼዴቅ መሥዋዕት አድርጌ እቀበልለታለሁ" አላት

በዚህ ጊዜ "አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ባርያህ ባለሟልነትን በፊትህ ካገኘሁስ አንድ ጊዜ እናገር ዘንድ ፍቀድልኝ" አለችው። እርሱም "ትናገሪ ዘንድ ፈቅጄልሻለሁ" አላት። " አቤቱ ሥጋዬ የሚቀበርበትን ወይም የሚያርፍበት ቦታ ወዴት ታዝዛለህ" አለችው። መቃብርሽ በዚች ጓንጒት በምትባል ደሴት ውስጥ ነው" አላት። "ነገር ግን ሥጋሽ በመሬት ውስጥ ይቀበራል ስላልኩሽ ኀዘን አይግባሽ በኋለኛው ዕለት እኔ አስነሣዋለሁና" አላት።

"አቤቱ እንዲህ ከሆነ መታሰቢያየን እያደረገ ስሜን እየጠራ በስሜ በታነጸው ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ የሚቀበረውን እስከ ስንት ትውልድ ድረስ ትምርልኛለሁ" አለችው። "እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እምርልሻለሁ" አላት። ይህንም ቃል ኪዳን በሰጣት ጊዜ ፈጽማ ተደሰተች።

ዳግመኛም "ይህች ደሴት እንደ ደብረ ታቦርና ደብረ ዘይት ስሟ የተጠራ ይሁን" አላት። "እንደዚሁ ይህችን ሥጋሽ የምታርፍበትን ቦታ ቀደስኳት አከበርኳት። መጽሐፍ የተናገረውን አልሰማሽምን ቦታ ሰውን የሚያከብረው አይደለም ሰው ቦታን ያስከብረዋል እንጂ። ስለዚህ ነገር ስላንቺ ይቺን መካነ መቃብርሽን ቀደስኳት አከበርኳት። ስሟም ደብረ ፍቅር ደብረ ምሕረት ተብሎ ይሰየም ወይም ይጠራል። እውነት እውነት እልሻለሁ ሥጋሽ ከተቀበረበት ሄዶ መካነ መቃብርሽን የተሳለመ የእናቴን የማርያምን መካነ መቃብር እንደተሣለመ ይቆጠርልታል። እውነት እውነት እልሻለሁ አንቺን ያከበረ ሁሉ እኔ በሰማያዊ መንግሥቴ አከብረዋለሁ። አንቺን የወደደ ወይም ያፈቀረሽን እኔ አፈቅረዋለሉ።

ዳግመኛም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ይህ የዛሬው በዓልሽ የደስታና የተድላ ቀን ነው" አላት። ይህንንም ብሎ በብዙ ወገን ወይም ሠራዊት ላይ ሾማት። "ክብሮሽ ከአሮንና ከሙሴ፣ ከጴጥሮስና ከጳውሎስ፣ ሰይጣን ድል ከአደረገው ከሕፃኑ ቂርቆስ፣ ከእንጦንስና ከመቃርስ፣ ከፀሐየ ልዳ እየተባለ ከሚጠራ ከጊዮርጊስ ጋር ክብር ጋር ትክክል ነው" አላት።

በደብረ ጽዮን ከሊቀ ዲያቆናት እስጢፋኖስ ጋር ትዘምሪ ዘንድ በክብር ተካከልሽ። በእውነት አንቺን የሚያፈቅሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው" አላት። ነቢዩ ዳዊት "አቤቱ እግዚአብሔርን ከሚያከብሩ ወይም ከሚፈሩ በስተቀር በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል በተቀደሰውስ ተራራ ላይ ማን ይኖራል" ብሎ ተናግሯልና። ስለዚህም አንቺን የሚያከብሩ ሁሉ አንቺን ከአለሽበት ቦታ ገብተው ከአንቺ ጋር ይደሰታሉ"።

ከዚህም አምላካዊ ቃል ጋራ በነሐሴ 24 ቀን የአባታች ተክለ ሃይማኖት በዓል የሚከበርበት ዕለት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለየች። በዚህ ጊዜ የነጎድጎድ ብልጭልጭታ ሆነ ነቢዩ ዳዊት "በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ" ብሎ እንደተናገረ የመላእክት ሠራዊትና ጻድቃን ሰማዕታትም ሁሉ እልል እያሉ አመሰገኑ። እርሷም ከነርሱ ጋር እየተደሰተች አመሰገነች። ከዚያም መላእክት ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አድርሰዋት ወይም አሳርገዋት በሸናፊው በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሰገደች።
601 viewsAschalew Kassaye, 08:02
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-29 11:02:35 ፀጒራን ይዛው በነበረ ምላጭ ላጨች ልብሷንም አውልቃ ለነዳያን አከፋፈለች የያዘችውንም ገንዘብ በመንገድ ላይ ላገኘችው ሁሉ መፅውታ ጨረሰች። ከዚያም አስቀድማ ያዘጋጀችውን ልብስ ምንኵስና ማለት ቀሚስዋን አጥልቃ አጽፋን ተጐናጽፋ ቆቧን ደፍታ ደብረ ሊባኖስ ከሴቶች ገዳም ደረሰች። የገዳሙ መነኰሳትም በታላቅ ክብር ተቀብለው ወደበዓታቸው አስገቧት ...

እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ለሳጥናኤል ምሕረት እንደለመነች፦ ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ጓንጉት በምትባል ደሴት ውስጥ ዓርብ ዕለት ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ስለሰው ልጆች ስትጸልይ ሣለ። ዓለሙ ሁሉ ከንቱ እንደሆነና የሰውም ልጅ ሕይወት እንደጥላ ኃላፊ ጠፊ መሆኑን ፈጽማ ተመለከተች። ነቢዩ ዳዊት "ሰው ከንቱ ነገርን ይመስላል ዘመኑ ወይም ሕይወቱ እንደጥላ ያልፋል" ሲል ተናግሯልና። ዳግመኛም "ሰው ክብር እንኳ ቢሆን ሊኖር አይችልም እንደሚጠፋ ወይም ማስተዋል እንደሌለው እንስሶች መሰለ... አለ ክቡር ዳዊት። ስለዚህም ሁሉ ነገር አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው መፃተኛዋ ባሪያህንም ኃጢአቷን አታስብባት እያለች ወደፈጣሪዋ መሪር ዕንባን አለቀሰች። ያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ግርማ ወደስዋ መጣ። በታላቅ ግርማ ሆኖ ባየችውም ጊዜ ደነገፀች ከእግሩ ሥርም ወደቀች። ከዚህ በኋላ ነውር በሌለባቸው ንዑዳት ክቡራንና ንጹሐን በሆነ እጆቹ አነሣት። ቀጥሎም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ አትደንግጭ ነገር ግን የልብሽን ሃሳብ ንገሪኝ" አላት። እስዋም "አቤቱ ባሪያህንስ በባለሟልነት ካሠለጠንካት አባታችን አዳምን በአርአያህና በአምሣልህ ስለምን ፈጠርከርው። በእንጨት መስቀልስ ላይ ለምን ተሰቀልክ ስለአዳምና ስለልጆቹ አይደለምን?" አለችው። "አዋን ስለነሱ ስል ተሰቅያለሁ" አላት። "እግዲያውስ መሰቀልህ ወይም የተሰቀልከው ስለነሱ ከሆነ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዛሬ የሞቱን ከዛሬም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚሞቱትን አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው" አለችው። "አንተ ቸር ይቅር ባይ መዓትህ የራቀ ምሕረትህ የበዛ ነህና ከአንተ ሌላ አምላክ የሌለ እውነተኛ አምላክ ነህ ሁሉ ይቻልሃልና የሚሣንህ ነገር ከቶ የለምና ዓለም በጠቅላላዋ በእፍኝህ አትሞላም" በማለት እያለቀሰች ለመነችው። በዚያ ጊዜ ጌታ መልሶ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ አንቺ ራስሽ ፍረጅ አዳም ከነልጆቹ ከሠራው ኃጢአት እና እኔ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን በቀያፋና በሐና አደባባይ በዕለተ ዓርብ ከተቀበልኩት ሕማማተ መስቀል ቢመዘን የትኛው ይመዝን ይመስልሻል?" አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ደነገጠችና ከመሬት ላይ ወደቀች። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት በሆኑ እጆቹ ከወደቀችበት አነሣትና "እንግዲህ ይህን ሁሉ መከራ የተቀበልኩ ለማን ወይም በማን ምክንያት ይመስልሻል" አላት።...

ጌታም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ የልብሽን ሃሳብ ወይም ፍላጐትሽን ንገሪኝ" አላት። በዚህን ጊዜ "አቤቱ ፈጣሪየ ፈቃድህስ ቢሆን የአዳም ልጆች ከሥቃይ ከኵነኔ ይድኑ ዘንድ ዲያብሎስን ይቅር ትለው ወይም ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ። የኃጥእን መመለሱን እንጂ ጥፋቱን አትወድምና" አለችው። "የምለምንህ ወይም ማረው የምልህ ዲያብሎስን ወድጄው አይደለም ነገር ግን እርሱ ከተማረ በአዳም ልጆች ላይ ሥቃይና ኵነኔ ሊኖር አይችልም ብየ በመገመት እንጂ። የነሱ ሥጋ ሥጋየ እንደሆመኑ መጠን የኔም ሥጋ ሥጋህ ነውና" አለችው። ይህንም ባለችው ጊዜ ጌታ ፍግግ ብሎ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ሌሎች ካንቺ በፊት የነበሩ ካንቺም በኋላ የሚነሱ የማያስቡትን እጅግ የሚያስደንቅ ልመና አቀረብሽ" አላት። ይህንም ካለ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ዲያብሎስን ማርልኝ ስትል ልመና አቅርባለችና እሺ ካላት ታወጣው በንድ ወደሲዖል ይዘሃት ሂድ" ብሎ አዘዘው። በዚህ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እሺ ብሎ ሰግዶ እጅ ነሥቶ ወደሲዖል ይዞአት ሄደ። አብረው በሚጓዙበትም ጊዜ "እንግዲህ ዲያብሎስ ከታረቀ ወይም ከተማረ የሰው ልጆች ሁሉ ያርፋሉ" እያለች ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል ታሳስበው ነበር። ይህን አምላክነትን ሲሻ ከክብሩ የተዋረደ ዲያብሎስ ምሕረት ለማግኘት ይሻ መስሏት ነበርና።

ከሲዖል አፋፍ በደረሱም ጊዜ የተመለከተችው ሥቃይ ተነግሮ የማያልቅ ነው ሰዎች ከሰዎች ጋር እንደውሻ ይናከሱ ነበር። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል "ምሕረት የሚፈልግ ከሆነ እስኪ በይ ዲያብሎስ ብለሽ ጥሪው" አላት። በዚህ ጊዜ በመላእክት ቋንቋ ሦስት ጊዜ "ሣጥናኤል ሣጥናኤል ሣጥናኤል" በማለት ጠራችው። ዲያብሎስም "ከዚህ በብዙ ሠራዊት ላይ ነግሼ ከምኖርበት አገር ማን ነው እሱ የሚጠራኝ" እያለ በታላቅ ቃል አሰምቶ ተናገረ። ከዚህም በኋላ "ለብዙ ዘመን ስፈልግሽ ወይም ሳድንሽ ቆይቼ ነበር ዛሬ ግን ከምኖርበት ቤቴ ድረስ መጣሽን" አላት። እርሷም "ጌታ ይቅርታ አድርጓልሃልና ከዚህ ከሥቃይና ከመከራ ቦታ ከወገኖችህ ጋራ ና ፈጥነህ ውጣ" አለችው። ይህንም በለችው ጊዜ ልቡ እንደ እሳት ነደደ አፈፍ ብሎ ተረማምዶ በግራ እጁዋን ይዞ ከሲዖል ረግረግ ውስጥ ወረወራት። በዚያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የእሳት ሰይፍ ይዞ ከኋላ ከኋላዋ ይከተላት ነበርና ይህን ምሕረት የሌለው ዕቡይ ዲያብሎስ በያዘው ሰይፍ ቢቀጣው የሲዖል ደጃፍ ተከፈተች። በዚህ ሰዓት ታላቅ ጨኸትና ውካታ ወይም መደበላለቅ ሆነ በሲዖል ያሉ የሰዎች ነፍሳት እንደንብ ከበቧት ወይም ሠፈሩባት። በዚያን ጊዜ በቅዱስ ሚካኤል ክንፍና በስዋም በተሰጣት ክንፈ ረድኤት ከሲዖል የወጡት ነፍሳት ቁጥር ዓሥር ሺህ ያህል ነበር። እነዚህ ከመከራ ያመለጡ ከሥቃይ የወጡ ነፍሳትን ባየች ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል እምቦሳ ጥጃ በመካከላቸው ትዘል ነበር።

ከዚህም በኋላ ወደ ፈጣሪዋ ሄዳ "አቤቱ ፍርድህ ከቶ እንደዚህ ነውን?" እያለች አደነቀች። ጌታም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዲያብሎስን ድል አድርገሽ ጥቂት ምርኮን አገኘሽን" አላት። እስዋም "አዋ ጌታዬ በኃይልህና በቸርነትህ አገኘሁ" አለችው። ከዚህ በኋላ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ "እሊህን ነፍሳት ዓለም ሳይፈጠር ወደ አዘጋጀሁላት ወደ ክርስቶስ ሠምራ መኖሪያ ቦታ ውሰዳቸው" አለው። በዚህ ጊዜ "አቤቱ ፈጣሪየ የእኔ መኖሪያየ ወዴት ነው?" አለችው። ጌታም "መኖሪያሽ ከእናቴ ከድንግል ማርያም ጋራ ነው እነሆ በትረ ማርያም ብየ ሰየምኩሽ መቀመጫሽን ወይም ደረጃሽን ከእርስዋ ቀጥሎ ሁለተኛ አደረግሁልሽ የባለሟልነት ግርማ አጐናጸፍኩሽ አንቺን የሚወዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው" አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ፈጽማ ደስ ተሰኘች ወደ ኋላዋም መለስ ብላ ብትመለከት ለዓይን የሚያንፀባርቁ ዓሥር አክሊላት አየች። በየአንዳንዳቸው አክሉል ላይ ዐራት ከዋክብት አሉ ባቸው የእሊህ ከዋክብት ቊጥራቸው ሲደመር አርባ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ከስዋ ጋራ የነበረውን መልአክ "እሊህ በላያቸው ብርሃናውያን ከዋክብት ያሉባቸው አክሊላት ለማን የተዘጋጁ ናቸው ሰውነቴ እጅግ አድርጋ ወዳቸዋለችና" አለችው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም "ላንቺ ቢሆን ደስ አይልሽምን?" አላት። እርስዋም "አዎን ጌታየ ለኔ ቢሆን እወዳለሁ" አለችው። "እንግዲያስ ላንቺ የተዘጋጁ ናቸው" አላት። "በምን ሥራዬ ለኔ ተሰጡኝ" አለችው። "ዐሠርቱ ቃላት ኦሪትን ስድስቱን ቃላተ ወንጌል ጠብቀሽ ቤትሽን ጥለሽ ይህን ዓለም ንቀሽ አጥቅተሽ የክርስቶስን ቀምበር ተሸክመሽ ፈጣሪሽን ስለተከተልሽው
591 viewsAschalew Kassaye, 08:02
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-28 22:03:07 Watch "LIVE እንኳን ለመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳቹ" on YouTube


304 viewsAschalew Kassaye, 19:03
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-28 13:33:45
735 viewsAschalew Kassaye, 10:33
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-28 13:33:31 "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

ነሐሴ ፳፫ (23) ቀን።

እንኳን በእስክድርያ (በግብጽ) በልዮናውያን ምክንያት በሰማዕትነት ለዐረፋ ለክርስቲያን ለወንዶች ለሴቶች ለሕፃናት ለሠላሳ ሺህ ሰዎችና ለዕረፍታቸው በዓልና ለቅዱስ ድምያኖስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን።

+ + +
በዚች ቀን በእስክንድርያ አገር ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ሠላሳ ሺህ ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ። ይህም እንዲህ ነው ንጉሥ መርትያኖስ አባታችን ዲዮስቆሮስን ወደ ደሴተ ጋግራ በአጋዘው ጊዜ ብዙ ዘመናት በእስክንድርያ አገር ሁከትና ብጥብጥ ሆነ።

መርትያኖስም በሞተ ጊዜ በርሱ ፈንታ ልዮን ነገሠ እርሱም አብሩታርዮስ የተባለውን መለካዊ ከሮማውያን ወገን ለእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ሾመ ይህም መለካዊ በኬልቄዶን ጉባዔ የሚያምን ነው ስለዚህም ከጥቂት ግብዞች ሰዎች በቀር የእስክንድርያ ሰዎች አልተቀበሉትም። ያልተቀበሉትም ሰዎች አስቀድሞ አባታችን ዲዮስቆሮስ ከሾማቸው ቀሳውስት ሥጋውንና ደሙን የሚቀበሉ ሆኑ። ከዚህም በኋላ በቃሉ ለሚያምኑ ባልንጀሮቹ ጉባኤ አደረገላቸውና የክርስቶስ መለኮቱ ከትስብእቱ ተቀላቀለ የሚል አውጣኪን አወገዘው ።

አብሩታርዮስም ይህን ማድረጉ የእስክንድርያን ሰዎች ሸንግሎ ወደ ከፋች እምነቱ ሊስባቸው ወዶ ነው እንጂ ስለዚህ ነገር አባ ዲዮስቆሮስ አውጣኪን አስቀድሞ አውግዞታል። የአባታችን የዲዮስቆሮስ ሃይማኖት እንደ ባስልዮስና ጎርጎርዮስ እንደ ቅዱስ ቄርሎስ ቃል ከሥጋ ጋር ከተዋሐደ በኋላ አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ ብለው እንደሚያምኑ የሚያምን ነውና።

ከጉባኤውም በኋላ የሰበሰባቸው የአብሩታርዮስ ተባባሪዎቹ ወደየቦታቸው ተመለሱ። እርሱም ራሱ አብሩታርዮስ በቤቱ ውስጥ ተገድሎ ተገኘ ለባልንጀሮቹም የአባታችን ዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት ወይም የአውጣኪ ባልንጀሮች ወይም ሌቦች ገንዘቡን ለመውሰድ የገደሉት መሰላቸው ይህም እውነት ይመስላል።

የአብሩታርዮስም ባልንጀሮች ወደ ንጉሥ እንዲህ ብለው መልእክትን ላኩ "እነሆ የዲዮስቆሮስ ወገኖች የንጉሥን ትእዛዝ በማቃለል ደፍረው የሾምከውን ሊቀ ጳጳሳት ገደሉት። በዚያንም ጊዜ ወንድሞቻችን የእስክንድርያ ሰዎች በላያቸው ጢሞቴዎስን ሊቀ ጵጵስና ሾሙት"። እሊህ መናፍቃንም ከዚህ በኋላ ሁለተኛ እንዲህ ብለው ወደ ንጉሥ መልእክትን ላኩ። "እነሆ አብሩታርዮስን የገደሉት ሰዎች አሁንም ያለ ንጉሥ ፈቃድ ደፍረው ሊቀ ጳጳሳት ሾሙ"።

ንጉሡም በሰማ ጊዜ ከሁለቱ መልእክቶች የተነሣ እጅግ ተቆጣ። ሰይጣንም በልቡ አድሮ ጭፍሮቹን ልኮ ሃይማኖታቸው ከቀና ወንድሞቻችን ክርስቲያኖች ታላላቆችና ታናናሾች ሠላሳ ሺህ ሰዎች ተገደሉ ጢሞቴዎስንም ወደ ደሴተ ጋግራ አጋዘው በዚያም ሰባት ዓመት ኖረ።

ከአባታችን ዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት አንዱ የገደለውስ ቢሆን ስለ አንድ ሰው ፈንታ ሠላሳ ሺህ ሰው መግደል ይገባልን ስለዚህ ከሰይጣን ሥራ እንደሆነ ይታወቃል።

ከዚህ ከከፋ ዕልቂት በኋላም ወንድሞቻችን የሆኑ የዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት አብሩታርዮስን እንዳልገደሉት ንጉሡ ተረዳ እጅግም አዘነ ጢሞቴዎስንም ከተሰደደበት መልሶ በመንበረ ሢመቱ አኖረው ታላቅ ክብርንም አከበረው። መንጋውንም እያበረታ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በ 30 ሺህ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

+ + +
ሰማዕቱ ቅዱስ ድምያኖስ፦ ይህንንም ቅዱስ የአንጾኪያ አገር መኰንን ይዞ ብዙ አሠቃየው፡፡
በኋላ ቅዱስ ድምያኖስ በእምነቱ መጽናቱን ሲያውቅና ማሠቃየትም በሰለቸው ጊዜ አንገቱን በሰይፍ ቆረጠውና ሰማዕትነት ፍጻሜው ሆነ፡፡ የክብር አክሊንም ተቀዳጀ፡፡ የቅዱስ ድምያኖስ በረከቱ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 23 ስንክሳር።

+ + +
"ሰላም ለክሙ በቃለ ብዙኅ ብፅዓን። ሠለስቱ እልፍ ምእመናን። ዘተቀተልክሙ በእደ አርዮሳውያን። ኦ አብያዝ ጽዱላን ስን። ደዩ ውስተ ሥጋየ እምቅብዕክሙ ርጢን። ማኅቶቱ ኢይጥፋእ ዘተብህለ ዐይን"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የነሐሴ23።

+ + +
የዕለቱ ምስባክ፦ "ወለእመኒ ፈለሱ አድባር ውስተ ልበ ባሕር። ደምፁ ወተሐምጉ ማያቲሆሙ። ወአድለቅለቁ አድባር እምኃይሉ"። መዝ 45፥2-3። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 13፥1-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 5፥6-12 እና የሐዋ ሥራ 12፥18-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 21፥18-23። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን ማርያም ወይም የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችን ይሁንልን።


በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።

@sigewe

https://t.me/joinchat/AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA
759 viewsAschalew Kassaye, 10:33
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-27 21:54:17
817 viewsAschalew Kassaye, 18:54
ክፈት / አስተያየት ይስጡ