Get Mystery Box with random crypto!

ፀጒራን ይዛው በነበረ ምላጭ ላጨች ልብሷንም አውልቃ ለነዳያን አከፋፈለች የያዘችውንም ገንዘብ በመን | ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ)

ፀጒራን ይዛው በነበረ ምላጭ ላጨች ልብሷንም አውልቃ ለነዳያን አከፋፈለች የያዘችውንም ገንዘብ በመንገድ ላይ ላገኘችው ሁሉ መፅውታ ጨረሰች። ከዚያም አስቀድማ ያዘጋጀችውን ልብስ ምንኵስና ማለት ቀሚስዋን አጥልቃ አጽፋን ተጐናጽፋ ቆቧን ደፍታ ደብረ ሊባኖስ ከሴቶች ገዳም ደረሰች። የገዳሙ መነኰሳትም በታላቅ ክብር ተቀብለው ወደበዓታቸው አስገቧት ...

እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ለሳጥናኤል ምሕረት እንደለመነች፦ ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ጓንጉት በምትባል ደሴት ውስጥ ዓርብ ዕለት ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ስለሰው ልጆች ስትጸልይ ሣለ። ዓለሙ ሁሉ ከንቱ እንደሆነና የሰውም ልጅ ሕይወት እንደጥላ ኃላፊ ጠፊ መሆኑን ፈጽማ ተመለከተች። ነቢዩ ዳዊት "ሰው ከንቱ ነገርን ይመስላል ዘመኑ ወይም ሕይወቱ እንደጥላ ያልፋል" ሲል ተናግሯልና። ዳግመኛም "ሰው ክብር እንኳ ቢሆን ሊኖር አይችልም እንደሚጠፋ ወይም ማስተዋል እንደሌለው እንስሶች መሰለ... አለ ክቡር ዳዊት። ስለዚህም ሁሉ ነገር አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው መፃተኛዋ ባሪያህንም ኃጢአቷን አታስብባት እያለች ወደፈጣሪዋ መሪር ዕንባን አለቀሰች። ያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ግርማ ወደስዋ መጣ። በታላቅ ግርማ ሆኖ ባየችውም ጊዜ ደነገፀች ከእግሩ ሥርም ወደቀች። ከዚህ በኋላ ነውር በሌለባቸው ንዑዳት ክቡራንና ንጹሐን በሆነ እጆቹ አነሣት። ቀጥሎም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ አትደንግጭ ነገር ግን የልብሽን ሃሳብ ንገሪኝ" አላት። እስዋም "አቤቱ ባሪያህንስ በባለሟልነት ካሠለጠንካት አባታችን አዳምን በአርአያህና በአምሣልህ ስለምን ፈጠርከርው። በእንጨት መስቀልስ ላይ ለምን ተሰቀልክ ስለአዳምና ስለልጆቹ አይደለምን?" አለችው። "አዋን ስለነሱ ስል ተሰቅያለሁ" አላት። "እግዲያውስ መሰቀልህ ወይም የተሰቀልከው ስለነሱ ከሆነ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዛሬ የሞቱን ከዛሬም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚሞቱትን አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው" አለችው። "አንተ ቸር ይቅር ባይ መዓትህ የራቀ ምሕረትህ የበዛ ነህና ከአንተ ሌላ አምላክ የሌለ እውነተኛ አምላክ ነህ ሁሉ ይቻልሃልና የሚሣንህ ነገር ከቶ የለምና ዓለም በጠቅላላዋ በእፍኝህ አትሞላም" በማለት እያለቀሰች ለመነችው። በዚያ ጊዜ ጌታ መልሶ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ አንቺ ራስሽ ፍረጅ አዳም ከነልጆቹ ከሠራው ኃጢአት እና እኔ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን በቀያፋና በሐና አደባባይ በዕለተ ዓርብ ከተቀበልኩት ሕማማተ መስቀል ቢመዘን የትኛው ይመዝን ይመስልሻል?" አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ደነገጠችና ከመሬት ላይ ወደቀች። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት በሆኑ እጆቹ ከወደቀችበት አነሣትና "እንግዲህ ይህን ሁሉ መከራ የተቀበልኩ ለማን ወይም በማን ምክንያት ይመስልሻል" አላት።...

ጌታም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ የልብሽን ሃሳብ ወይም ፍላጐትሽን ንገሪኝ" አላት። በዚህን ጊዜ "አቤቱ ፈጣሪየ ፈቃድህስ ቢሆን የአዳም ልጆች ከሥቃይ ከኵነኔ ይድኑ ዘንድ ዲያብሎስን ይቅር ትለው ወይም ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ። የኃጥእን መመለሱን እንጂ ጥፋቱን አትወድምና" አለችው። "የምለምንህ ወይም ማረው የምልህ ዲያብሎስን ወድጄው አይደለም ነገር ግን እርሱ ከተማረ በአዳም ልጆች ላይ ሥቃይና ኵነኔ ሊኖር አይችልም ብየ በመገመት እንጂ። የነሱ ሥጋ ሥጋየ እንደሆመኑ መጠን የኔም ሥጋ ሥጋህ ነውና" አለችው። ይህንም ባለችው ጊዜ ጌታ ፍግግ ብሎ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ሌሎች ካንቺ በፊት የነበሩ ካንቺም በኋላ የሚነሱ የማያስቡትን እጅግ የሚያስደንቅ ልመና አቀረብሽ" አላት። ይህንም ካለ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ዲያብሎስን ማርልኝ ስትል ልመና አቅርባለችና እሺ ካላት ታወጣው በንድ ወደሲዖል ይዘሃት ሂድ" ብሎ አዘዘው። በዚህ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እሺ ብሎ ሰግዶ እጅ ነሥቶ ወደሲዖል ይዞአት ሄደ። አብረው በሚጓዙበትም ጊዜ "እንግዲህ ዲያብሎስ ከታረቀ ወይም ከተማረ የሰው ልጆች ሁሉ ያርፋሉ" እያለች ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል ታሳስበው ነበር። ይህን አምላክነትን ሲሻ ከክብሩ የተዋረደ ዲያብሎስ ምሕረት ለማግኘት ይሻ መስሏት ነበርና።

ከሲዖል አፋፍ በደረሱም ጊዜ የተመለከተችው ሥቃይ ተነግሮ የማያልቅ ነው ሰዎች ከሰዎች ጋር እንደውሻ ይናከሱ ነበር። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል "ምሕረት የሚፈልግ ከሆነ እስኪ በይ ዲያብሎስ ብለሽ ጥሪው" አላት። በዚህ ጊዜ በመላእክት ቋንቋ ሦስት ጊዜ "ሣጥናኤል ሣጥናኤል ሣጥናኤል" በማለት ጠራችው። ዲያብሎስም "ከዚህ በብዙ ሠራዊት ላይ ነግሼ ከምኖርበት አገር ማን ነው እሱ የሚጠራኝ" እያለ በታላቅ ቃል አሰምቶ ተናገረ። ከዚህም በኋላ "ለብዙ ዘመን ስፈልግሽ ወይም ሳድንሽ ቆይቼ ነበር ዛሬ ግን ከምኖርበት ቤቴ ድረስ መጣሽን" አላት። እርሷም "ጌታ ይቅርታ አድርጓልሃልና ከዚህ ከሥቃይና ከመከራ ቦታ ከወገኖችህ ጋራ ና ፈጥነህ ውጣ" አለችው። ይህንም በለችው ጊዜ ልቡ እንደ እሳት ነደደ አፈፍ ብሎ ተረማምዶ በግራ እጁዋን ይዞ ከሲዖል ረግረግ ውስጥ ወረወራት። በዚያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የእሳት ሰይፍ ይዞ ከኋላ ከኋላዋ ይከተላት ነበርና ይህን ምሕረት የሌለው ዕቡይ ዲያብሎስ በያዘው ሰይፍ ቢቀጣው የሲዖል ደጃፍ ተከፈተች። በዚህ ሰዓት ታላቅ ጨኸትና ውካታ ወይም መደበላለቅ ሆነ በሲዖል ያሉ የሰዎች ነፍሳት እንደንብ ከበቧት ወይም ሠፈሩባት። በዚያን ጊዜ በቅዱስ ሚካኤል ክንፍና በስዋም በተሰጣት ክንፈ ረድኤት ከሲዖል የወጡት ነፍሳት ቁጥር ዓሥር ሺህ ያህል ነበር። እነዚህ ከመከራ ያመለጡ ከሥቃይ የወጡ ነፍሳትን ባየች ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል እምቦሳ ጥጃ በመካከላቸው ትዘል ነበር።

ከዚህም በኋላ ወደ ፈጣሪዋ ሄዳ "አቤቱ ፍርድህ ከቶ እንደዚህ ነውን?" እያለች አደነቀች። ጌታም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዲያብሎስን ድል አድርገሽ ጥቂት ምርኮን አገኘሽን" አላት። እስዋም "አዋ ጌታዬ በኃይልህና በቸርነትህ አገኘሁ" አለችው። ከዚህ በኋላ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ "እሊህን ነፍሳት ዓለም ሳይፈጠር ወደ አዘጋጀሁላት ወደ ክርስቶስ ሠምራ መኖሪያ ቦታ ውሰዳቸው" አለው። በዚህ ጊዜ "አቤቱ ፈጣሪየ የእኔ መኖሪያየ ወዴት ነው?" አለችው። ጌታም "መኖሪያሽ ከእናቴ ከድንግል ማርያም ጋራ ነው እነሆ በትረ ማርያም ብየ ሰየምኩሽ መቀመጫሽን ወይም ደረጃሽን ከእርስዋ ቀጥሎ ሁለተኛ አደረግሁልሽ የባለሟልነት ግርማ አጐናጸፍኩሽ አንቺን የሚወዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው" አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ፈጽማ ደስ ተሰኘች ወደ ኋላዋም መለስ ብላ ብትመለከት ለዓይን የሚያንፀባርቁ ዓሥር አክሊላት አየች። በየአንዳንዳቸው አክሉል ላይ ዐራት ከዋክብት አሉ ባቸው የእሊህ ከዋክብት ቊጥራቸው ሲደመር አርባ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ከስዋ ጋራ የነበረውን መልአክ "እሊህ በላያቸው ብርሃናውያን ከዋክብት ያሉባቸው አክሊላት ለማን የተዘጋጁ ናቸው ሰውነቴ እጅግ አድርጋ ወዳቸዋለችና" አለችው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም "ላንቺ ቢሆን ደስ አይልሽምን?" አላት። እርስዋም "አዎን ጌታየ ለኔ ቢሆን እወዳለሁ" አለችው። "እንግዲያስ ላንቺ የተዘጋጁ ናቸው" አላት። "በምን ሥራዬ ለኔ ተሰጡኝ" አለችው። "ዐሠርቱ ቃላት ኦሪትን ስድስቱን ቃላተ ወንጌል ጠብቀሽ ቤትሽን ጥለሽ ይህን ዓለም ንቀሽ አጥቅተሽ የክርስቶስን ቀምበር ተሸክመሽ ፈጣሪሽን ስለተከተልሽው