2022-06-30 20:25:49
ደንብ መተላለፍ በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ #መግቢያ
በኢትዮጵያ ህግ ቅጣት ሊያስከትሉ የሚችሉ ድርጊቶችን ከክብደታቸው እና ከሚያስከትሉት ሀላፊነት አንፃር በወንጀል ህግ የሚያስቀጡ እና በደንብ መተላለፍ ህግ የሚያስቀጡ ብለን ልንከፍል እንችላለን፡፡ በደንብ መተላለፍ የሚያስቀጡ ድርጊቶች በኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ህግ ሰባተኛ መፅሀፍ እና ስምንተኛ የተደነገጉ ሲሆን ቅጣትን የሚመለከቱ ደንቦች እና የህጉ ተፈጻሚነት ወሰን በወንጀል ህጉ ተካቶ ይገኛል፡፡ በዚህ አጭር ፅሁፍ የደንብ መተላለፍ ምንነት እና ከወንጀል ሀላፊት በምን እንደሚለይ ፣ የደንብ መተላለፎች የሚያስከትሉት ቅጣት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ይዳሰሳሉ፡፡
የደንብ መተላለፍ ምንነት አንድ ሰው ደንብ ተላልፏል የሚባለው ሥልጣን ያለው አካል ባወጣው ህግ የተመለከተውንና አንድ ነገር እንዳይፈፀም የሚያዘውን ወይም የሚከለክለውን ድንጋጌ የተላለፈ ወይም በወንጀል የማያስቀጣ ቀላል ጥፋት የፈፀመ ሲሆንና የዚህ ዓይነቱ ህግ መጣስ ወይም ቀላል ጥፋት በወንጀል ህጉ ከአንቀፅ 746 እስከ 775 በተመለከቱት ድንጋጌዎች የሚያስቀጣ ሲሆን ነው፡፡ በዚሁ መሰረት በወንጀል ህጉ የደንብ መተላለፍ ህግ ላይ በተለየ ሁኔታ ካልተደነገገ በቀር የነገሩን ዓይነት እንዲሁም የህጉን መንፈስና ግብ በመመልከት የወንጀል ህጉ ጠቅላላ ክፍል መሰረታዊ መርሆችና ደንቦች በደንብ መተላለፍ ላይ ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡
የደንብ መተላለፍ አይነቶችየደንብ መተላለፍ ህጉ በውስጡ የተለያዩ አይነት የደንብ መተላለፎችን የያዘ ሲሆን እነዚህ መተላለፎች በስራቸው ዝርዝር የጥፋት አይነቶችን ከሚያስከትሉት ቅጣት ጋር አካተው ይገኛሉ፡፡ የደንብ መተላለፍ አይነቶቹም በመንግስትና ህዝብ ጥቅም ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ተግባሮች( ለምሳሌ ህጋዊ ገንዘብን አለመቀበል)፤ ወታደራዊ ግዴታዎችን መጣስ እና በመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም በፖሊስ ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች፤ በመንግስት የስራ ግዴታዎች እና በመንግስት መስሪያ ቤት/ባለስልጣን/ ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች(ለምሳሌ ሀቀኝነትን ማጓደል)፤ በሕዝብ ደኅንነት፣ሰላምና ተረጋግቶ መኖር ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች(ለምሳሌ ሐሰተኛ የአደጋ ምልክት መስጠት)፤ በሕዝብ ጤና እና በፅዳት ጥበቃ ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች( ለምሳሌ መርዛማና አደንዛዥ ንጥረ ነገሮችና መድሀኒቶች ለመቆጣጠር የወጣ ደንብ) እና በሰዎችና በንብረቶች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ናቸው፡፡
ደንብ መተላለፍ ተፈፃሚ የሚሆንባቸው ጥፋቶችበህጋዊነት መርህ እንደተመለከተው በደንብ መተላለፍ ህግ ወይም በሌላ ህግ የተደነገጉ ጥፋቶች ብቻ የሚያስቀጡ ሲሆን የሚያስቀጡትም በህጉ የተቀመጡትን ቅጣቶች ብቻ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የደንብ መተላለፍ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ የሚሆኑት ለተፈፀመው ድርጊት የበለጠ ቅጣት የሚደነግጉ አንቀፆች በሌሉ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም አንድ ድርጊት የሚያስቀጣው በወንጀል ህግ ወይም በደንብ መተላለፍ ህግ በአንደኛው እንጂ በሁለቱም ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲሁም የወንጀል ህግ ወደ ኋላ ተመልሶ የማይሰራ መሆኑ መርህ በተመሳሳይ ለደንብ መተላለፍ ይሰራል፡፡ በመሆኑም የደንብ መተላለፍ ተግባሮች የሚያስቀጡት በተፈፀመበት ጊዜ ፀንተው ባሉት ድንገጌዎች መሰረት እንጂ ከድርጊቱ በኋላ የወጣን ህግ ወደ ኋላ ተመልሶ እንዲፈፀም በማድረግ አይሆንም፡፡
በሌላ በኩል የደንብ መተላለፍ ተግባርን ለመፈፀም የሚደረጉ የመዘጋጀትና የሙከራ ድርጊቶች የማያስቀጡ ሲሆን ለደንብ መተላለፍ የሚደረግ ማነሳሳት፣አባሪነት እና ወንጀል ከፈፀመ በኋላ ወንጀል አድራጊውን መርዳት አያስቀጣም፡፡ ይህ ማለት የሚቀጣው ደንብ ተላላፊው ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ እንዲሁም የህግ ሰውነት የተሰጠውን ሰው በአነሳሽነት ወይም በአባሪነት የማይቀጣ ሲሆን የድርጅቱ ሀላፊ ወይም ሰራተኛ የሚቀጣው በወንጀል ህጉ መሰረት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ደንብን ወይም መመሪያን በዋና ደንብ ተላላፊነት በሚጥስበት ጊዜ ብቻ ነው፡፡
በተጨማሪም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 743 እንደተደነገገው የማያስቀጡና ይቅርታ የሚሰጡ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ እነዚህም በህግ የታዘዙ ወይም የተፈቀዱ ድርጊቶች፣ የሞያ ስራ ግዴታ፣ የተጎጂው ፍቃድ ፣ ፍፁም የሆነ መገደድ፣አስፈላጊ ሁኔታ እና ህጋዊ መከላከልን የሚመለከቱ የወንጀል ህግ ድንጋጌዎች ለደንብ መተላለፍም ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡ ይሁንና ደንብ የተላለፈ ማንም ሰው ህግ አለማወቅን ወይም የማድረግ መብት አለ ብሎ መሳሳትን እንደመከላከያ ምክንያት አድርጎ ሊያቀርብ አይችልም፡፡
ለደንብ መተላለፍ ተፈፃሚነት ያላቸው ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎችለደንብ መተላለፍ መደበኛ የሆኑ የወንጀል ቅጣቶች ተፈፃሚ የማይሆኑ ስለሆነ ምንጊዜም ቢሆን ለወንጀሎቹ በተወሰኑት ፅኑ እስራት ወይም በቀላል እስራት አይቀጡም፡፡ ይህም የሚያመለክተው ደንብ መተላለፍ ከወንጀል የሚለየው በሚያስከትለው የተለየ ቅጣት እንደሆነ ነው፡፡ ስለሆነም የደንብ መተላለፍ ድርጊቶች በተፈፀሙ ጊዜ የሚወሰነው ነፃነትን የሚያሳጣ ቅጣት የማረፊያ ቤት እስራት እንጂ የማረሚያ ቤት እስራት አይሆንም፡፡ መደበኛ የማረፊያ ቤት እስራት የሚፈፀመው ከፍርድ ቤቶች ወይም ከፖሊስ ጣቢያዎች ጋር በተያያዙ ልዩ የመቆያ ቦታዎች ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንዲሁም በማረፊያ ቤት እስራት ፈንታ የግዴታ ስራን ፍርድ ቤት ሊወስን የሚችልባቸውን ሁኔታዎች የደንብ መተላለፍ ህጉ ደንግጎ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በማናቸውም ጊዜ ቢሆን በማረፊያ ቤት እስራት እንዲቀጣ የተፈረደበት ሰው ወደ ጠባይ ማሻሻያ ወይም ማረሚያ ቤት እንዲላክ ፣በወንጀል ምክንያት ከተቀጡት እስረኞች ጋርም እንዲቀላቀል ማድረግ አይቻልም፡፡
በወንጀል ህጉ አንቀጽ 747 እና 768 እንደተደነገገው የደንብ መተላለፍ ድርጊቶች በተፈፀሙ ጊዜ የሚወሰነው ቅጣት እና የህጉ ልዩ ድንጋጌዎች የሚያስቀምጡት ከፍተኛ ቅጣት የማረፊያ ቤት እስራቱ የሚቆይበት ጊዜ ከአንድ ቀን እስከ ሶስት ወር ይሆናል( በደጋጋሚነት እና በመደራረብ ጊዜ ከሁለት ዓመት የማረፊያ ቤት እስራት አይበልጥም) ፡፡ በተጨማሪም ደንብ ተላላፊዎች ወታደሮች ወይም ወጣት ጥፋተኞች ሲሆኑ የሚፈፀመው የተለየ ቅጣት እንደተጠበቀ ሆኖ በደንብ መተላለፍ ረገድ የሚፈፀሙ ቅጣቶች በደንብ መተላለፍ ህግ በተደነገገው መሰረት ይሆናል፡፡ እንዲሁም ለህብረተሰቡ ሲባል የጥበቃ ወይም የሕክምና እርምጃዎች መወሰድ ሲኖርባቸው በተለየ ኃላፊ ሊሆኑ የማይችሉ ሰዎችን በሚመለከት ፍርድ ቤት አግባብነት ላለው የአስተዳደር ባለስልጣን ያሳውቃል፡፡
ሌላው በደንብ መተላለፍ ህጉ ለደንብ መተላለፍ ጥፋት የተቀመጠው ቅጣት የገንዘብ መቀጮ ቅጣት ነው፡፡ ይኸውም ጥፋተኛው ደጋጋሚ ካልሆነ ወይም የህጉ ልዩ ድንጋጌ የበለጠ ካልወሰነ በቀር በደንብ ተላላፊ ላይ የሚጣል መቀጮ ከአንድ ብር እስከ ሶስት መቶ ብር ለመድረስ የሚችል ሲሆን ጥፋቱ በተደጋገመ ጊዜ የሚደረገው የቅጣት ማክበጃ እንደተጠበቀ ሆኖ ተላላፊው ጣፋቱን የፈፀመው በአፍቅሮ ንዋይ እንደሆነ መቀጮው እስከ አምስት መቶ ብር ሊደርስ ይችላል፡፡ እንዲሁም ለተፈረደበት ሰው ቢያስፈልግም ከፋፍሎ በየጊዜው ዕዳውን እንዲከፍል በመፍቀድ ፍርድ ቤቱ እስከ ሶስት ወር ለመድረስ በሚችል የመክፈያ ጊዜ ሊወስንለት የሚችል ሲሆን ሁኔታዎች በቂ ምክንያት ያስገኙ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የመከፈያ ጊዜውን እስከ አንድ አመት ሊያራዝመው ይችላል፡፡...
ይቀጥላል
649 views17:25