Get Mystery Box with random crypto!

ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል

የቴሌግራም ቻናል አርማ mkpublicrelation — ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል
የሰርጥ አድራሻ: @mkpublicrelation
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 34.65K
የሰርጥ መግለጫ

በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል የምዕመናን መረጃ መለዋወጫና ትምህርት መስጫ አውታር ነው፡፡

Ratings & Reviews

3.00

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

1

4 stars

0

3 stars

0

2 stars

0

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች

2024-04-09 09:06:27
ከጌዲኦ፣ ቡርጂ እና አማሮ ዞኖች ሀገረ ስብከት የተወጣጡ ሠልጣኞ የተተኪ መምህራን ሥልጠና ጀመሩ።

ማኅበረ ቅዱሳን ከደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፍሬ ሃይማኖት ሰ/ት/ቤት ጋር በመተባበር ከጌዲኢ ዞን ቡርጂ እና አማሮ ሀገረ ስብከት ሠልጣኞችን በመልመል የተተኪ መምህራን ሥልጠና አስጀምሯል።

መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም  የሥልጠናውን ማስጀመሪያ እና የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሐ ግብር በሰ/ት/ቤቱ አዳራሽተከናውኗል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርት እና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ም/ኃላፊ የሆኑት ዲ/ን ኃይሌ አርአያ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል።

ም/ኃላፊው በንግግራቸው ሠልጣኞች በቆይታቸው የተዘጋጁላቸውን የሥልጠና ዓይነቶች በትጋት መውሰድ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። በተጨማሪም የፍሬ ሃይማኖት ሰ/ት/ቤት ም/ሊቀ መንበር የሆኑት ቀሲስ ታደሰ እንደገለጹት ሠልጣኞች ተገቢውን ዕውቀት ይዘው እንዲሄዱ በሰ/ት/ቤቱ በኩል አስፈላጊው ዝግጅት በሙሉ እንደተጠናቀቀ ገልጸዋል።

ሠልጣኞቹ በቆይታቸው  የተለያዩ የሥልጠና ርእሶች እና የውይይት ሐሳቦች እንደሚዳሰሱላቸው ለማወቅ ተችሏል
13.8K views...typing, 06:06
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-04-06 21:27:07 “መቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።

እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በምኵራብም ትገረፋላችሁ፤ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል። ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።

ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤ በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ፤ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፤ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።

በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና። ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ።

በዚያን ጊዜም ማንም እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥ ወይም እነሆ፥ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳን ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ። በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል፤ ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል። ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።ሰ ማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።

ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም። ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፤ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ። እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮህ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና፤ ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ። ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።”

ወንድሞች ሆይ! ጊዜ ዋጋው የላቀ በመሆኑና የጌታችንንም የፍርድ ቀን የሚያውቅ አለመኖሩን በቅዱስ ወንጌል ስለተነገረን በበጎነት፣ በቅንነትና በእምነት ጽናት ሆነን በጸሎት እንዲሁም በጾም፣ በትጋትና በክርስቲያናዊ ምግባር በመታነጽ በሃይማኖት ልንኖር ይገባናል፡፡ ዘወትርም ለሕጉ በመገዛትና ትእዛዙን በመፈጸም እስከ መጨረሻው ጸንተን “ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና” ልንባል ያስፈልጋል፡፡ (ማቴ.፳፭፥፴፬‐፴፮)

ዕድል ፈንታችን መንግሥተ ሰማያት መውረስ ይሆን ዘንድም በምድራዊ ሕይወታችን መከራ ሥቃይ ተቀብለንና ለነፍሳችን መሥዋዕት መክፈል ይገባል እንጂ “እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘለዓለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና” ከመባል ይሠውረን፡፡ (ማቴ. ፳፭፥፵፩‐፵፫)
የአምላካችን ቸርነትና ረድኤት አይለየን፤ አሜን!
14.8K views...typing, 18:27
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-04-06 21:26:32
ደብረ ዘይት፡- ዳግም ምጽአት

ዘመነ ሥጋዌ የጌታችን መገለጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከትንበት፣ ይህም ከሰማያት ወርዶ እኛን ለማዳን ከንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው በመሆን ዓለምን ያዳነበት ነው፡፡ እርሱ እንደ ሰው ተወልዶ፣ እንደ ሕፃናት በጨርቅ ተጠቅልሎ፣ ጡት ጠብቶ፣ በየጥቂቱ አድጎ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በእግር ተመላልሶ፣ እንደ ሰው ተርቦና ተጠምቶ፣ ኀዘን መከራን ተቀብሎ በፍጹም ፍቅሩ አድኖናል፡፡

ፈውሰ ነፍስ በሆኑት ትምህርቶቹ ዓለምን አጣፍቶ፣ አዳኝ በሆኑት እጆቹ ልምሾዎችን፣ ድዊዎችንና አንካሶችን አድኖ፣ ጎባጣን አቅንቶ፣ የዕውራንን ዓይን አብርቷል፡፡ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መሆኑንም በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቀ መለኮት እጅ ተጠምቆ አስመስክራል፡፡ ብርሃነ መለኮቱ በታየበት በደብረ ታቦር ተራራም አምላክነቱን ገልጧል፡፡ (ማቴ.፫፥፲፫-፲፯፣፲፯፥፩-፰)

ይህን ሁሉ ያደረገው ሰዎች አምላክነቱን አውቀን፣ ከሰማየ ሰማያት የወረደውና መከራን ተቀብሎ በመስቀል ላይ የሞተው ለእኛ ድኅነት መሆኑን እንዲሁም ድንቅ ሥራውን የፈጸመበት ይህን ጥበቡን ተረድቶና፣ የእጁን ሥራ፣ የቃሉን ተእምራት ያመነውን ሁሉም እንደሚድነን ሲያበስረን ነው፡፡ በተጓዳኝም በመዋዕለ ስብከቱ ስለ ዳግም ምጽአቱና ምልክቶቹ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በዝርዝር በደቀ መዛምርቱ በኩል አሳውቆናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ (ማር.፲፫፥፫-፴፯)
12.6K views...typing, edited  18:26
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-04-01 11:32:18
12.7K views...typing, 08:32
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-03-30 21:13:45
ቤተ ሳይዳ ዘኢየሩሳሌም ባለ አምስት በር፣ እርከን (መመላለሻ)፣ አምስት ዓይነት ድውያን ፈውስን ለማግኘት ጥምቀቱን ሲጠባበቁ የሚኖሩባት ናት። ውኃው የቤተ አይሁድ ምሳሌ፣ አምስት መመላለሻ የሕግጋተ ኦሪት እና የአምስቱ መጻሕፍተ ሙሴ ምሳሌ በእነዚያ ተጠብቀው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው። ቀድሞ የገባባት አንዱ እንዲድን፣ እነርሱም አንድነት ቤተ እስራኤል ተሰኝተው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው። አንድም አምስቱ እርከን (መመላለሻ) የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር በዚያ ሊያምኑ ያሉ ተስፈኞችና ያመኑባትም ልጅነትን ያገኙባታልና። አምስቱ ዓይነት ድውያንም የአምስቱ ጾታ ምእመናን ከእነ ፈተናቸው ምሳሌ ነው፡፡ እነርሱም አእሩግ በፍቅረ ነዋይ፣ ወራዙት በዝሙት፣ አንስት በትውዝፍት (በምንዝር ጌጥ)፣ ካህናት በትዕቢት አእምሯችን ረቂቅ መዓረጋችን ምጡቅ እያሉ፣ መነኮሳት በስስት ምግብን በፈለጉት ጊዜ ባያገኙት ይልቁንም በአት እየፈቱ በከንቱ የመፈተናቸው ምሳሌ ሆኖ ይነገራል።

መልአከ እግዚአብሔር ወርዶ ውኃውን ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ የሚነጻባት፣ ነገር ግን በዕለቱ ከአንድ ሕመምተኛ በቀር ለሌላው ፈውስ የማይደገምባት ቦታ ናት። ሐተታው የመጠመቂያ ውኀው የማየ ጥምቀት ምሳሌ ሲሆን ውኃውን ያናውጥ (ይባርክ) የነበረው መልአክ የቀሳውስት (ካህናት) “ለቀድሶተ ማየ ጥምቀት” የመውረዳቸው ምሳሌ ነው፤ ፈውሱም የሚከናወነው በዕለተ ቀዳሚት ሲሆን የሚፈወሰው አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ የሚድነው አንድ ታማሚ ብቻ መሆኑ የአባቶቻቸው ምሕረት አለመቅረቱን ሲያሳይ፣ አለመደገሙ ደግሞ ፍጹም ድኅነት እንዳልነበረ ያሳያል፡፡

ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ የኖረ መፃጉዕን በአልጋው ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦ ያንን በሽተኛ “ትፈቅድኑ ትሕየው? … ባድንህ ፈቃድህ ነውን?” አለው። ማእምረ ኅቡዓት ክርስቶስ፣” አዎን፥ እንዲለው እያወቀ”፤ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ “የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም” ብሎ የመሰከረለት ጌታችን ፈውስን በመጠባበቅ ከመዳን ውጪ ሌላ ዓላማ ያልነበረውን ይህን ሰው አይቶ ፈቃዱን እያወቀ ግን ፍቀድልኝና ላድንህ አለው። (ዕብ.፬፥፲፪) “ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው?“ እንዲል፤ (መክ.፮፥፲፪) የሚያስፈልገንን ሳንነግረው የሚያውቅ የሚሰጠንም ከእርሱ ከፈጣሪው ውጪ በእውነት ማን አለ?

መፃጉዕ በኋላ የሚክድ ነውና “ሳልፈቅድለት ነው ያዳነኝና አልጋ ያሸከመኝ” እንዳይል፣ በዕለተ ዓርብ የሚከስበትን ሲያሳጣውና ለኋላ ጥፋቱ የገዛ ኅሊናው እንዲቀጣው ፈቃዱን ጠየቀው። “ሰው የሌለኝ ሆኖ እንጂ ያንንማ ማን ይጠላል” በሚል ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ድኅነትን ፈቅዶ ገለጠ። እስከ ውኃው መናወጥ ሳያቆየው “ተንሥእ ንሣእ ዓራተከ ወሑር …፤ ተነሥና አልጋህን አንሥተህ ሂድ” አለው፤ ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ ዘመን የተሸከመች አልጋ ተሸክሟት ሄደ።

ጌታችን መፃጉዕን ‹‹ተነሥተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› ያለው፦

• አንደኛው ቅዱስ ኤስድሮስ እንዳለው አልጋው ጠንካራ የብረት አልጋ ነበረና ጽንዓ ተአምራቱን ለማሳየት ነው፡፡

• ሁለተኛው ‹‹ታዲያ ቢያድነኝ በከንቱ መች ሆነና የገዛ አልጋዬን ትቼለት የመጣሁ ለመዳኔ ዋጋ የከፈልኩበት አይደለምን?›› እንዳይል “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ብሎታል።

ያለ ተረፈ ደዌ አንሥቶት “ያለህን ይዘህ ሂድ፤ እኔ ከአንተ አንዳች አልሻም” ባሰኘ ቃል ሸኝቶታል። ታዲያ ይህ ምስኪን መፃጒዕ “ሰው የለኝም” ብሎ የደረሰለትን ረሳ፤ ማን እንደሆነ እንኳን አላወቀውም። ወንጌላዊውም “ዘሐይወ ኢያእመረ ዘአሕየዎ …፤የዳነው ያዳነውን አላወቀውም” ይለዋል። ( ዮሐ.፭፥፲፫) ይህን ሁሉ ያደረገው አምላክ ተዘነጋ። ዛሬም ከደዌው፣ ከማጣቱ፣ ከችግሩ፣ ከሥጋ ኑሮ ጉድለቱ እንደ መፃጒዕ አምላኩን ያልረሳ ማነው? ተአምራቱን አይቶ፣ ቃሉን ሰምቶ አምላኩን ያስታወሰስ ማነው? ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠስ ማን ነው?” (ኤር. ፳፫፥፲፰)። እኛም ብንሆን ከአዳም በደል ነጻ ያደረገንን አምላክ ውለታ ዘንግተን የምናፌዝ ሁላችንንም ወደ ልባችን እንድንመለስ ነቢዩ እንዲህ ሲል ይመክረናል “እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ፡፡” (ኢሳ.፳፰፥፳፪ )

መፃጉዕ ያዳነው ማን እንደሆነ ሲጠየቅ እንኳን አላወቀም። ወንጌላዊውም “የዳነው ያዳነውን አላወቀውም” ብሎ ገልጾታል። (ዮሐ.፭፥፲፫) በምኩራብ አግኝቶት ያዳነውን እንዳወቀውም ሄዶ ለአይሁድ “ያዳነኝ እርሱ ጌታ ኢየሱስ ነው” ብሎ ነገራቸው፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቤተ መቅደስ ሳለ ያን ያዳነውን ሰው አገኘውና “ዑቅ ኢትአብስ ዳግመ እንከ ከመ ዘየአኪ ኢይርከብከ፤ ከዚህ የከፋ “ስለ ደዌ ሥጋ ፈንታ ደዌ ነፍስ” እንዳያገኝህ ሁለተኛ እንዳትበድል” (ቁ.፲፬) ያለውን ዘንግቶ ደዌ ዘኃጢአትን ጠርቶ ተወዳጃት፤ በዕለተ ዓርብ የጌታውን ጉንጮች የጸፉች እጁም ደርቃ ሰላ ቀርታለች።

ዛሬም ቢሆን እንደ መፃጉዕ ሰዎች በኃጢአት ብዛት ልባቸው የደረቀና ያበጠ፣ ሰውነታቸው የሰለለ፣ ዓይነ ሕሊናቸው የታወረ፣ እግረ ልቡናቸው የተሰበረ ብዙዎች ሕሙማን በጠበል ቦታ፣ በገዳማት እና በአድባራት አሁንም አሉ፡፡ ፈውስን ይሻሉ፤ ድኅነትን ይፈልጋሉ፡፡ እንደ መፃጕዕ ቦታቸውን ሳይለቁ እግዚአብሔርን በተስፋ ቢጠብቁት አንድ ቀን ይፈወሳሉ።

ስለዚህ ይህ ሳምንት ጌታችን ድውያንን ስለመፈወሱ የሚነገርበትና እኛም ባለን ዓቅም በነፍስ በሥጋ የተቸገሩትን ሁሉ መርዳትና ማገዝ እንዳለብን የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡ ሕሙማንን መጠየቅ፣ የታሰሩትን መጎብኘትና ማስፈታት፣ የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስ፣ ያዘኑትን ማረጋጋት ከጌታችን የተማርናቸው ክርስቲያናዊ ምግባራት ናቸው፡፡

በዚህ ዕለት የእግዚአብሔር አምላካችን ፈዋሽነትና አዳኝነት እንዲሁም ታዳጊነትና የወደቁትን የማይረሳ እውነተኛ መድኃኒት መሆኑ የሚዘከርበትና ምስጋና የሚቀርብበት ነው። ቅዱስ ዳዊትም "እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፣ ወይመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ፣ አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ፤ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፣ እኔም አቤቱ ማረኝ እልሃለሁ” በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት በዝማሬው አረጋግጧል።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና” ሲል ሲቀኝ፣ (መዝ.፸፪፥፲፪) ጻድቁ ኢዮብም እንዲሁ “ረዳት (ኃይል) የሌለውን ምንኛ ረዳኸው” በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት መስክሯል፡፡ (ኢዮ.፳፮፥፪) ስለዚህ ገንዘብ፣ ሥልጣን፣ ወገን፣ ረዳት የለኝም በማለት ተስፋ የቆረጥን ሰዎች እግዚአብሔር ከሰውም፣ ከሥልጣንም፣ ከገንዘብም በላይ ነውና እርሱን ተስፋ አድርገን ሁል ጊዜ በስሙ መጽናናት እና የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣል እንደሚገባን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ የሚፈልጉህ ሁሉ በአንተ ደስ ይበላቸው፤ሐሤትም ያድርጉ፡፡ ሁል ጊዜ ማዳንህን የሚወዱ ዘወትር እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን ይበሉ” እንዳለው ሁል ጊዜም በአምላካችን እግዚአብሔር ደስተኞች
13.2K views...typing, 18:13
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-03-13 14:11:20
ኑ! የከበረች ሕይወትን እናትርፍ !
መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ፣
+++
ገቢው በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠመው ማኅበራዊ ቀውስና ድርቅ የተጎዱ ወገኖቻችንን፣ ገዳማትና አብነት ት/ቤቶች ለመደገፍ የሚውል።
የመግቢያ ትኬቱን፡-
1. በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 4ኛ ወለል (ቤተ አብርሃም)
2. በወረዳ ማእከላት ጽ/ቤቶች
3. በማኅበረ ቅዱሳን ንዋያተ ቅድሳት መሸጫ ሱቆች
4. በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ የዕለት ገንዘብ መሰብሰቢያዎች
5. በአሐዱ ባንክ ሁሉም ቅርንጫፎች
6. በሰ/ት/ቤት ጽ/ቤቶች
ለበለጠ መረጃ
• 09 44 71 82 82
• 09 42 40 76 60

ማኅበረ ቅዱሳን
13.8K views...typing, 11:11
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-03-10 12:37:11 ዘወረደ የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ነው። ስያሜውም የቅዱስ ያሬድ ነው። ትርጉሙም “ከሰማያት የወረደ” ማለት ነው። ቅድመ ዓለም ከአባቱ ከአብ የተወለደ ፣ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም የተወለደ ነው። ስም አጠራሩ  ያለና የነበረ፣ እግዚአብሔር፣ በፈቃዱ ዓለምን ለማዳን የመምጣቱን ምሥጢር የምንረዳበት ሳምንት ነው። ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ‹ጾመ ሕርቃል› እየተባለም ይጠራል፡፡ ሕርቃል (ኤራቅሊዮስ) በ፮፻፲፬ ዓ.ም የነበረ የቤዛንታይን ንጉሥ ነው፡፡ለክርስቲያኖች ባደረገው ርዳታ ምክንያት አንድ ሳምንት ጾመውለት ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ጾመ ሕርቃል እየተባለ ይጠራል፡፡ ሙሉ ታሪኩ በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ አንቀጽ ፲፭ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ሳምንት ቤተ ክርስቲያን ስለ ጾም ጥቅምና እንዴት መጾም እንዳለብን ታስተምረናለች፡፡ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው “አከለክሙ መዋዕል ዘኃለፈ ዘተቀነይክሙ ለግዕዘ ሥጋክሙ፤ ለሥጋቸሁ ፈቃድ የተገዛችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል፤ ከአሁን በኋላ ግን ጹሙ፣ ጸልዩ ለእግዚአብሔር ተገዙ” እያለ የጾም አዋጅ ያውጃል። ጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ፣ ፈቃደ ነፍስን ለፈቃደ እግዚአብሔር የምናስገዛበት መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡

ጾሙ በሚጀመርበት ሰንበት በሚሰበከው ምስባክ እንዲህ ብሎ ያሳስበናል፤ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣ በረዓድም ደስ ይበላችሁ” ጾም ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከሌሎች ምቾቶችና ደስታዎች ከመከልከል ያለፈ ጥልቅ ትርጉም ያለው ተግባር ነው። (መዝ.፪፥፲፩-፲፪) “ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ከመ ያብርህ ብርሃነ ስብሐቲሁ በላዕሌነ፤ (የእግዚአብሔር) የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም፤ወንድማችንንም እንውደድ” እንዲል። (ጾመ ድጓ)

በዘወረደ እሑድ የሚነበቡት ምንባባትም ይህንን የጾምን ጸጋ የያዙ ናቸው።

“ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡” (ያዕ.፬፥፮-፲)

“በውኑ እንግዲህ በስሙ እናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን፥ ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡” (ዕብ.፲፫፥፲፭-፲፮)

በጾም የተጠቀሙ ቅዱሳንን እያሰብን ለጾም እንድንተጋም ወደ እነርሱ እንድንመለከት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡“ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና።” (ዕብ.፲፫፥፱) ሳምንቱ በሚጀምርበት ሳምንት የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት እንዲህ ይላል፡፡ ጾመ ድጓው አባቶቻችን ያገኙትን በረከት እንደምናገኝበት ሲገልጽ “የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም፤ ወንድሞቻችንም እንውደድ፤ ኤልያስ በጾም ወደ ሰማይ አርጓልና፤ዳንኤልም ከአናብስት አፍ ድኗልና፡፡”

ጾም ፈቃደ ነፍስን በፈቃደ ሥጋ ለማሠልጠን የአጋንንት ኃይል ለመቋቋም የሚያስችል የክርስቲያኖች ጋሻ በመሆኑ በሃይማኖት ለሚመሩ ምእመናን እጅግ አስፈላጊና ከምንም በላይ የሕይወታቸው መርሕ መሆን እንደሚገባ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ በማለት   ያስተምራል፡፡ ” አሁንም ወንድሞቻችን በዚህ በሥጋችን ሳለን ፈቃደ ሥጋችንን ልንሠራ አይገባም፤ ፈቃደ ሥጋቸውን የሚሠሩ ሰዎች በወዲያኛው ዓለም ምውታን ናቸውና፡፡ የሥጋችሁን ፈቃድ በነፍሳችሁ ፈቃድ ድል ከነሣችሁት ለዘለዓለም ሕያዋን ትሆናላችሁ፡፡ የነፍሳቸውን ፈቃድ የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና፡፡" (ሮሜ ፰፥፲፪-፲፬)

ጾም አበው ቅዱሳን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ቀምረው፣ በበታ ወስነው፣ በሁኔታ ገድበው... ባስቀመጡልን ወቅት ከእህልና ከውኃ በመከልከልና ሰውነትን በማድከም ብቻ ሳይሆን ለስሕተት ከሚዳርጉ ነገሮችና ቦታዎች ተቆጥቦ በጸሎት መትጋትም እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም ይህንን እውነታ በተመለከተ እንዲህ ይላል፡፡ “እኔ ግን እዘንልን፤ ለምንልን ባሉኝ ጊዜ ማቅ ምንጣፍ ለብሼ አዘንኩላቸው፤ ሰውነቴን በጾም አደከምኩዋት፤ ልመናዬም እኔም ወደመጥቀም ተመለሰችልኝ፡፡” (መዝ. ፴፬/፴፭፥፲፫)

ጾም ከሥነ ምግባራት ሕግ አንዱ በመሆኑ እንኳንስ ያልተፈቀደውን የተፈቀደውም ቢሆን የማይጠቅም ከሆነ ፈጽሞ በመተው ለእግዚአብሔር ያለንን ፍጹም ፍቅር የምናስመሰክርበት ምሥጢር ነው፡፡

ጾም ከመብልና ከመጠጥ ጋር የተያያዘም በመሆኑ መብል ጊዜያዊ ስለሆነ ማለትም በዚህ ዓለም እስካለን ብቻ የምንገለገልበት እንጂ ዘለዓለማዊ ስላይደለ ለጊዜያዊ መብልና መጠጥ ምክንያት ከሃይማኖት ሥነ ምግባር እንዳንወጣ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ሲመክሩ “መብል በእግዚአብሔር ዘንድ ግዳጅ አይፈጽምልንም ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ብንበላም አይረባንም፤ አይጠቅመንም፤ ብንተወውም አይጎዳንም” በማለት ሲመክሩን ቅዱስ ጳውሎስም የመብልና የሆድ ጊዜያዊነት አስመልክቶ እንዲህ በማለት አስተምሯል፡፡ (፩ኛቆሮ.፰፥፰)

“ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅመኝም፡፡ ሁሉ ተፈቅዶልኛል በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳን አይሠለጥንብኝም፡፡ መብል ለሆድ ነው ሆድም ለመብል ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ያሳልፋቸዋል”፤ (፩ኛቆሮ.፮፥፲፪-፲፫) “ለሚጠፋ ምግብ አትሥሩ፤ ይልቅስ የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት ስለሚሆን ምግብ ሥሩ” እንደ ተባለ (ዮሐ. ፮፥፳፯) ካለን ጊዜ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጊዜ በመስጠት ቢበሉት የማያስርበውን፣ ቢጠጡት የማያስጠማውን፣ የዘለዓለም ሕይወት የምናገኝበትን ሥጋ እና ደሙን ተቀብለን መንግሥቱን እንድንወርስ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።

ሥርዓት ቅዳሴ
ከሠራኢ ካህን፣
ቅዳሴ፡
ዘእግዚእነ
“ዘበእንቲኣነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ፡ ወረደ እምሰማያት። ተሰብአ፡ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል፤ ስለ እኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ፤ በመንፈስ ቅዱስ ግብር  ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ፡፡”

ወንጌል፡ ዮሐ.፫፥፲-፳፬
የዕለቱ ምንባባት:-
•  በሠራኢ ዲያቆን (ዕብ.፲፫፥፯-፲፯)
•  በንፍቅ ዲያቆን (ያዕ.፬፥፮-ፍጻሜ)
•  በንፍቅ ካህን (የሐዋ. ፳፭፥፲፫-ፍጻሜ)

ምስባክ፡ “ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር” (መዝ.፪፥፲፩)

ወንጌል፡ ዮሐ.፫፥፲-፳፬

ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ፤ እንድናመልከው እኛን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን!
12.6K views...typing, edited  09:37
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-02-06 14:38:38
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ አገር እንዳይገቡ ተከለከሉ

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአሜሪካ የነበራቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎት ጨርሰው ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ እንዳይገቡ መከልከላቸው ተሰምቷል።

ብፁዕነታቸው ከሳምንታት በፊት በቋሚ ሲኖዶስ እውቅና ወደ ሀገረ ስብከታቸው በመሄድ የአጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ዓመታዊ በዓል፣ የከተራና የጥምቀት በዓላትን ከመንፈስ ልጆቻቸው ጋር ያከበሩ ሲሆን ለአዳጊ ሕጻናትም ማዕረገ ዲቁና መስጠታቸው ይታወቃል።

ብፁዕነታቸው በአሁኑ ሰዓት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያው እንደሚገኙ ታውቋል።
13.8K views...typing, edited  11:38
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-02-02 15:01:30
የዳውሮ ሀ/ስብከት አዳሪ የአብነት ት/ቤት ተመረቀ።

በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት በዳውሮ ሀ/ስብከት በምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም የተገነባው አዳሪ የአብነት ት/ቤት ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም የዳውሮና ኮንታ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ምእመናን በተገኙበት ተመርቋል።

ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ት/ቤት ባልተስፋፋባቸውና የአገልጋይ ካህናትና ዲያቆናት እጥረት ባለባቸው  በደቡብ፣በምእራብና በምሥራቅ በሚገኙ አህጉረ ስብከት አብነት ትምህርትን ለማስፋፋት እየሠራ የሚገኝ ሲሆን ይህ የአብነት ት/ቤት ኘሮጀክት አንዱ ነው።

  በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል አስተባባሪነት በአውሮፓ በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ ምእመናን የገንዘብ ድጋፍ የተገነባው የአዳሪ አብነት ት/ቤት  40 ተማሪዎችን በአዳሪነት ፣ 100 ተማሪዎችን በተመላላሽነት ተቀብሎ ማስተማር የሚችል ሲሆን ለት/ቤቱ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ቁሳቁሶች የተሟሉለት መሆኑንና ለግንባታውም ከ 3.8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉ ተገልጿል።

በምርቃቱ መርሐግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ መልእክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የአብነት ት/ቤቱ  መገንባት በአገልጋይ እጥረት ምክንያት በሀ/ስብከቱ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያትን ለማስከፈትና የሚታየውን የአገልጋዮች እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ  ከሁሉም ወረዳዎች  ተማሪዎች ተመርጠው እንደሚገቡ በመግለጽ ለኘሮጀክቱ መሳካት ድጋፍ ላደረጉ ምእመናን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና ለሀ/ስብከቱ መንበረ ጵጵስና በታርጫ ከተማ አስተዳደር በተሰጠው ቦታ ላይ ብፁዕነታቸው የመንበረ ጵጵስና ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
12.9K views...typing, 12:01
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-01-21 20:50:12

12.8K viewsDesalegn Abebe, 17:50
ክፈት / አስተያየት ይስጡ