Get Mystery Box with random crypto!

የዳውሮ ሀ/ስብከት አዳሪ የአብነት ት/ቤት ተመረቀ። በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት በዳውሮ ሀ/ስ | ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል

የዳውሮ ሀ/ስብከት አዳሪ የአብነት ት/ቤት ተመረቀ።

በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት በዳውሮ ሀ/ስብከት በምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም የተገነባው አዳሪ የአብነት ት/ቤት ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም የዳውሮና ኮንታ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ምእመናን በተገኙበት ተመርቋል።

ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ት/ቤት ባልተስፋፋባቸውና የአገልጋይ ካህናትና ዲያቆናት እጥረት ባለባቸው  በደቡብ፣በምእራብና በምሥራቅ በሚገኙ አህጉረ ስብከት አብነት ትምህርትን ለማስፋፋት እየሠራ የሚገኝ ሲሆን ይህ የአብነት ት/ቤት ኘሮጀክት አንዱ ነው።

  በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል አስተባባሪነት በአውሮፓ በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ ምእመናን የገንዘብ ድጋፍ የተገነባው የአዳሪ አብነት ት/ቤት  40 ተማሪዎችን በአዳሪነት ፣ 100 ተማሪዎችን በተመላላሽነት ተቀብሎ ማስተማር የሚችል ሲሆን ለት/ቤቱ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ቁሳቁሶች የተሟሉለት መሆኑንና ለግንባታውም ከ 3.8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉ ተገልጿል።

በምርቃቱ መርሐግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ መልእክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የአብነት ት/ቤቱ  መገንባት በአገልጋይ እጥረት ምክንያት በሀ/ስብከቱ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያትን ለማስከፈትና የሚታየውን የአገልጋዮች እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ  ከሁሉም ወረዳዎች  ተማሪዎች ተመርጠው እንደሚገቡ በመግለጽ ለኘሮጀክቱ መሳካት ድጋፍ ላደረጉ ምእመናን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና ለሀ/ስብከቱ መንበረ ጵጵስና በታርጫ ከተማ አስተዳደር በተሰጠው ቦታ ላይ ብፁዕነታቸው የመንበረ ጵጵስና ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።