2022-09-13 09:55:57
የአዲስ ዓመት ቁርጥ ውሳኔ (New Year’s Resolution)
በመላው ዓለም ዙሪያ በሚልየን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሚለማመዷቸው ልምምዶች መካከል አዲስ ዓመት ሲመጣ በአንድ በሕይወታቸው ለማምጣት በሚፈልጉት ለውጥ አንጻር ቁርጥ የሆነን የለውጥ ውሳኔን የማስተላፍ ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ልምምድ ጥሩም መጥፎም ጎን አለው፡፡
የአዲስ ዓመት ቁርጥ ውሳኔ ጥሩ ጎኑ ባለፈው አመት ያታገሉንን ሁኔታዎች ለመለወጥ ከአዲስ ዓመት ጋር የሚመጣን መነሳሳት መጠቀም ስለምንችል ነው፡፡ ለውጥ ሳያመጡ ከዓመት ወደ ዓመት ከመሸጋገር ቢያንስ ያንን መጠቀሙ የተሻለ ነው፡፡
የአዲስ ዓመት ቁርጥ ውሳኔ ጥቅም-የለሽ የሚሆነው ግን አንድን ለውጥ ለማምጣ የግድ አዲስ ዓመትን የመጠበቅ ልማድ ካለንና ካልገፋንበት ነው፡፡ የሕይወት ለውጥ የአንድ ቀን ዘመቻ ጉዳይ ሳይሆን ሂደትና የሕይወት ዘይቤ ሊሆን ስለሚገባው ማለት ነው፡፡ ይህንን ለውጥ ሂደት የመሆኑን እውነታ ካልተገነዘብን ቁርጥ ውሳያችን ከመስከረምና ከጥቅምት ወራት አልፎ አይሄድም፡፡
ነገሩን ስንጨምቀው ሁል ጊዜ በሕይወታችን ማሻሻል፣ መጀመር፣ ማቆም . . . የምንፈልጋቸው ነገሮች መኖራቸው ካልቀረ፣ አዲሱን አመት በመጠቀም በአንዳንድ ነገሮች ላይ ቁርጥ ውሳኔን ብናስተላልፍ መልካም ነው፡፡
ከዚያም ጋር ግን አንድን የጀመርነውን ነገር ያለማቆምንም ቁርጥ ውሳኔ ብናስተላልፍ የበለጠ የተሻለ ነው፡፡ (ይንን ውሳኔ ለማስተላለፍ ከፈለጋችሁ “ጀምሮ መጨረስ” የሚለው መጽሐፌ ያግዛችኋል)፡፡
ይህንን ሃሳብ ተግባራዊ ለማድግ እንዲመቻችሁና የአዲስ አመት ቁርጥ ውሳኔ ስታስተላልፉ የሚከተለውን መርህ ለመከተል ሞክሩ፡-
1. መለወጥ (መጀመር፣ መቆም …) ያለበትን ነገር ነጥሎ መለየትና ማወቅ፡፡
2. ለውጡ የሚጀመርበትን ቀን መወሰን፡፡
3. ለውጡን ለማምጣት መውሰድ ያብኝን እውነታን ያገናዘበ እርምጃ ማስቀመጥ፡፡
4. በለውጡ ሂደት ላይ የንባብ፣ የሰው ምክርና የመሳሰሉትን ድጋፍ ማግኘት፡፡
5. መጀመር! ከጀመሩ አለማቆም! የማቆም አዝማሚያ ሲከሰት እንደገና መጀመር!
Dr Eyob Mamo
መልካም አድስ አመት 2015
721 views06:55