2022-06-12 13:57:45
በዓለ ጰራቅሊጦስ /ጰንጠቆስጤ Pentecost/
ጰንጠቆስጤ ማለት ቃሉ የግሪክ ቃል ነው። ትርጉሙም ሃምሳኛ ማለት ነው።ጰራቅሊጦስ ማለትም በጎን የሚቆም፣የሚረዳ፣የሚያፅናና ማለት ነው። በብሉይ ኪዳን ወቅት አይሁድ የፋሲካ በዓላቸውን ካከበሩ በኃላ ሃምሳውን ቀን የነፃነት በዓላቸው አድርገው ከሰነበቱ በኃላ ሃምሳኛውን ቀን በተለየ ሁኔታ ያከብራሉ ይህም ቀን በዓለ ሰዊት ይባላል። በእነርሱ ሃገር ከመጋቢት እስከ ግንቦት ያለው ወቅት ፀደይ(የእሸት ወራት) ነውና።
እንግዲህ ይህ በዓለ ሰዊት ጌታችን ባወቀ ለሐዲስ ኪዳን በዓል ሁለት ጥቅሞችን እንዲያስገኝ አርጎታል። የመጀመሪያው ለበዓለ ሃምሳ (ጰራቅሊጦስ) ምሳሌ፣መንገድ ጠራጊ፣መተርጎሚያ፣ማሳ፣አኛ መሆኑ ነው ሁለተኛው ግን በዓሉ እንዲከበር ዋናው ምክንያት የሆነው የመንፈስ ቅዱስ መውረድ(ርደተ መንፈስ ቅዱስ) ጌታችን ባረገ በ10ኛው ቀን በተነሳ 50ኛው ዕለት በዝርው የነበሩ አይሁድ ሁሉ ለበዓለ ፋሲካ እና ለበዓለ ሰዊት እንደተሰበሰቡ የተፈፀመ መሆኑ ነው። ይህ በዓልም(በዓለ ጰራቅሊጦስ) የቤተክርስቲያን የልደት ቀን በመባል ይታወቃል። በ1ቀን ብቻ በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት 3ሺህ ነፍሳት አምነው ተጠመቁ።
በሐዋርያት ትምህርት፣በህብረት እንጀራውንም በመቈረስ በጸሎት ይተጉ ነበር ይለናል መጽሕፍ ቅዱስ። ሐዋ2፥41-42
ከዚህ በተጨማሪም ከላይ እንደተጠቀሰው መንፈስ ቅዱስ የወረደበት፣በ3ሺህ ሰዎች ጥምቀት መስፋፋት የጀመረችበት፣ሐዋርያትም ፍሩሃኑ ጥቡዓን(ደፍሮች) ሆነው በእውቀት በልጽገው፣ በአእምሮ ታድሰው ዓለሙን ለመለወጥ ኃይል ያገኙባት እለት ነው። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም
“መንፈስ ቅዱስ ባይወርድላት ኖሮ የቤተክርስቲያን ህልውና ኮስምኖ ቀጭጮ ይቀር ነበር። ስለዚህም በሚገባ አነጋገር ይህች ዕለት የቤተከርስቲያን የልደት ቀን ትባላለች።” በማለት ተናግሯል።
ከዚህ የተነሳ ሌሎች ሊቃውንትም ዕለቲቱን የበዓላት ሁሉ እመቤት እንደሚሏት ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ ገልጸዋል። በዓለ ጰራቅሊጦስ ከትንሳኤ በ50ኛው ከዕርገት ደግሞ በ10ኛው ቀን ይከበራል። የትንሳኤ በዓልም የሚፈጸመው በዚህ ዕለት ነውና የትንኤው ቃለ እግዚአብሔር በዚህ ዕለት ይፈጸማል ። ይህ ክብረ በዓል የሚከብረው እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሰረት ከዕለተ ሰንበተ ክርስቲያን (እሁድ) ውጪ ሊሆን አይችልም ።
ይህ በዓል ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ለቤተ ክርስቲያን “ከእናንተ ጋር ስኖር ይህን እነግራችኋለሁ አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” እና “ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ ።” ሲል የገባው ኪዳን የተፈጸመበት ተደርጐም ይከበራል ።
ፍትሐ ነገሥትም ይህንን በዓል እንድናከብር ያዘናል ። “ ትንሳኤን ባከበራችሁ በሃምሳኛው ቀን ዕርገቱን ባከበራችሁ በአስረኛው ቀን በዓለ ጰራቅሊጦስን አክብሩ ደገኛ በዓልም ይሁንላችሁ ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዛን ዕለት በሶስት (3) ሰዓት መንፈስ ቅዱስን ሰዶልናልና ። በፈቃዱ መንፈስ ቅዱስን የተመለንበት፣ ጸጋውን ሀብቱን ያገኘንበት ፣ እርሱ በእኛ እንዳደረብን መጠን በ72 ቋንቋ የተናገርንበት ፣ ክርስቶስ እግዚአብሔር የባሕርይ አምላክ እንደሆነ ለአህዛብ ለአይሁድ ያስተማርንበት ቀን ነውና።”
ስለ አከባበሩም ተጨማሪ ሐተታዎችን ያትታል ። ይኸውም ትንሳኤን በመብል እና በመጠጥ እናዳከበርነው በዓለ ጰራቅሊጦስ ደግሞ በጾም እና በጸሎት እንድናከብር የሚል ነው።
የሰንበት መዝሙር
ሃሌታ (፫) በሰንበት ዓርገ ሐመረ ገሠፀ ባሕረ ወገሠፆሙ ለነፋሳት ወይቤሎሙ ኢትናፍቁ ወኢይምጻእ ኑፋቄ ውስተ ልብክሙ በከመ ፈነወኒ አቡየ አነኒ እፌንወክሙ ውስተ ቤተ አቡየ ብዙኅ ማኅደር ቦቱ ካዕበ እመጽእ ወእነሥአክሙ ከመ ተሀልዉ ምስሌየ በመንግሥተ አቡየ ዘበሰማያት
ምስባክ
መዝ ፵፮ ቊ ፭-፮
ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ
ምንጭ ፦
https://t.me/Amde_Tewahedo_SS
604 viewsedited 10:57