Get Mystery Box with random crypto!

#ዝክረ ቅዱሳን ሰኔ 30 ፦ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐ | {ብሒለ አበው ወ ሕይወት መንፈሳዊ}

#ዝክረ ቅዱሳን

ሰኔ 30 ፦ መጥምቀ መለኮት
ቅዱስ ዮሐንስ ልደቱ

ዮሐንስ ማለት ‹‹ፍሥሐ ወሐሴት፣ ርኅራኄ›› ማለት ነው፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ጠራጊ የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ የብሉይ ኪዳን የመጨረሻው የሐዲስ ኪዳን ደግሞ የመጀመሪያው ነቢይ ነው፡፡ ስለ ወላጆቹ ስለ ካህኑ ዘካርያስና ስለ ቅድስት ኤልሳቤጥ በቅዱስ ወንጌል ላይ እንዲህ ተብሎ ተመስክሮላቸዋል፡፡ ‹‹በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፥ ስሟም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ።›› ሉቃ 1፡5-6፡፡
እግዚአብሔር ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ዘካርያስ ልጅ እንደሚወልድ ይነግረው ዘንድ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልን ላከው፡፡ መልአኩም በመጀመሪያ በመሠዊያው በስተቀኝ በኩል ተገልጦ ለዘካርያስ ታየው፡፡ ለሰይጣን ቀኝ የለውምና መልአኩ ግን ብርሃናዊ የማናዊ ነውና መልአክ እንደሆነ እንዲታወቅ በቀኝ በኩል ተገልጦ ታየው፡፡ አንድም ሰው ሁሉ ወደ የማናዊ ግብር የሚመለስበት ዘመን ደረሰ ሲል በቀኝ በኩል ታየው፡፡ አንድም ሰውን ሁሉ መክሮ አስተምሮ ወደ ቀኝ ወደ መንፈስ ቅዱስ ሥራ የሚመልስ ልጅ ትወልዳለህ ሲለው በቀኝ በኩል ተገልጦ ታየው፡፡ ነገር ግን ዘካርያስ የእርሱም ሆነ የሚስቱ
ዕድሜአቸው ስለገፋ የሚስቱን የመፀነሷን ነገር አላምን ቢል መልአኩ ድዳ አድርጎታል፡፡ ዮሐንስም ሲወለድ ‹‹ስሙን ማን እንበለው?›› ሲሉት በጽሑፍ አድርጎ ‹‹ዮሐንስ በሉት›› አላቸው፤ ያንጊዜም አንደበቱ ተፈታለት፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ተድላም ይሆንልሃል›› (ሉቃ 1፡13) ባለው ሰዓት አላመነም ነበር፡፡ አሁን ግን የልጁን ስም ‹‹ዮሐንስ›› ብሎ ሲለው ተዘግቶ የነበረው አንደበቱ ተፈቶለታል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ጌታችንን በዕድሜ በ6 ወር ይበልጠዋል፡፡ ርጉም የሆነ ሄሮድስ መሢሕ ሕፃን ክርስቶስ መወለዱን ሲሰማ መንግሥቴን ይቀማኛል ብሎ በመፍራት በቤቴልሔም ያሉ ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች ያሉ 144,000 (መቶ ዐርባ አራት ሺህ) የቤቴልሔም ሕፃናትን በሰይፍ ሲያስገድል ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ ስትሰደድ፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ ደግሞ ወደ ሲና በረሃ ሄዳ ልጇን ዮሐንስን ከዚያ ደብቃዋለች፡፡ ከመሄዷ በፊት ግን ከባሏ ከዘካርያስ ጋር ሲሰነባበቱ የሚሆነውንም ሁሉ እርሱ ቀድሞ ያውቅ ነበርና ‹‹ሕፃኑን ልጄን ሲያጡ እኔን ይገድሉኛል፣ አንቺ ግን ወደ በረሃው ይዘሽው ሂጂና በዚያ ሸሽጊው›› ብሎ መክሯታል፡፡ እርሷም ከሄደች በኋላ የርጉም ሄሮድስ ጭፍሮች ዮሐንስን ባጡት ጊዜ ወደ ዘካርያስ መጥተው ‹‹ልጅህን ወዴት አድርሰኸው ነው? ወዴትስ ደበቅኸው? አሁን ከደበቅህበት አምጥተህ ፈጥነህ አስረክበን›› በማለት የፍጥኝ አስረው ካሠቃዩት በኋላ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ከሚሠዋበት በቤተ መቅደስና በዕቃ ቤት መካከል አንገቱን ቆርጠው ገደሉት፡፡ የዘካርያስም ደም እስከ ሰባት ዓመት ድረስ እየፈላ ደሙ ሲካሰሳቸው ኖረ፡፡
‹‹ቅድስት ኤልሳቤጥም ልጇን ዮሐንስን ይዛ ወደ በረሃ ከገቡ አምስት ዓመት በሆናቸው ጊዜ ዮሐንስ ዕድሜው ሰባት ዓመት ከመንፈቅ ከሆነው በኋላ እናቱ ኤልሳቤጥ ሞተችበትና ብቻውን ከበረሃ ውስጥ ተወችው፡፡ ዮሐንስም በሰፊዋ በረሃ ውስጥ በአራዊቶች መካክል ብቻውን ቀረ፡፡ ለዮሐንስ ግን በእርሱ ላይ ምንም መጥፎ ነገር ሳያደርጉ የቶራና የአንበሳ የነብርም ልጆች እንደ ወንድምና እንደ እኅት ሆኑት፡፡ አራዊቶችም ሁሉ ወዳጅ ሆኑት፡፡ ምግቡም የበረሃ ቅጠል ነው፤ መጠጡም ከተቀመጠባት ድንጋይ ሥር የፈለቀችለት ውኃ ነበረች፡፡ ዮሐንስ ሰውነትን አለምልመው፣ ሥጋን አለስልሰው፣ ገጽንና ፊትን የሚያሳምሩትን ምግቦች አልተመገበም፡፡ የበረሃ ቅጠሎችንም አልተመገበም፡፡ አንቦጣ ከተባለችው ከአንዲት የበረሃ ቅጠልና ከጣዝማ ማር በስተቀር ከሚበሉት ምግቦች ሁሉ ዮሐንስ ኅርምተኛ ሆኖ የተለየ ነበር›› ይላል ቅዱስ ገድሉ፡፡ ነገር ግን ‹‹አንቦጣ›› ተብላ የምትጠራ አንዲት የበረሃ ቅጠልንና የጣዝማ ማርን እየተመገበ ማደጉን ለመግለጽ ብዙ ጊዜ በተለምዶ ‹‹የዮሐንስ ምግቡ የበረሃ አንበጣ ነበር›› ተብሎ የተሳሳተ ነገር ሲነገር ይሰማል፡
የመጥምቀ መለኮትቅዱስ ዮሐንስ ረድኤት በረከቱ ከሁላችን ጋር ይሁን
አዘጋጅ ፦ ኦብሳ ተፈሪ
https://t.me/Amde_Tewahedo_SS