2022-10-31 21:14:59
ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከ10 ሺሕ የሚበልጡ ነባር መደበኛ ተማሪዎችን ሕዳር 5 እና 6/2015 ዓ.ም እንደሚቀበል አሳወቀ።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መማክርት ጉባኤ (ሴኔት) በዛሬው ዕለት በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ መክሯል።
መማክርት ጉባኤው ተወያይቶ ውሳኔ ካስተላለፈባቸው ጉዳዮች የ2015 ዓ.ም አካዳሚክ ካሌንደርን ገምግሞ ማጽደቅ አንዱ ነው።
የ2015 ዓ.ም አካዳሚክ ካሌንደር በሬጅስትራርና አልሙናይ ጉዳዮች ዳይሬክተር በሆኑት መ/ር ሳሙኤል ሳርካ ቀርቧል።
በቀረበው አካዳሚክ ካሌንደር መሰረት በሁሉም የትምህርት ፕሮግራሞች ዩኒቨርሲቲው ነባር መደበኛ ተማሪዎችን ሕዳር 5 እና 6/2015 ዓ.ም እንደሚቀበል ተገልጿል።
ነባር መደበኛ ተማሪዎች ሕዳር 5 እና 6/2015 ዓ.ም ምዝገባ እንደሚያካሄዱ፤ የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ (DOCO) ሕዳር 07 እንደሚጀምር፤ የካቲት 17/2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ሴሚስቴር ማጠናቀቂያ እንደሆነ እንዲሁም ከየካቲት 20/2015 ዓ.ም እስከ መጋቢት 01/2015 ዓ.ም ድረስ የሴሚስቴር ማጠቃለያ ፈተና እንደሚሰጥ በቀረበው አካዳሚክ ካሌንደር ተብራርቷል።
ዩኒቨርሲቲው በሦስቱም ካምፓሶቹ በሁሉም የትምህርት ፕሮግራም ከ10 ሺህ የሚበልጡ ነባር መደበኛ ተማሪዎችን በመቀበል የመማር ማስተማር ሂደትን እንደሚያስቀጥል በመድረኩ ተጠቁሟል።
ነባር መደበኛ ተማሪዎችን ለመቀበል ከቀለብ፣ ከመኝታ ቤት፣ ከሕክምና፣ ከካውንስሊንና ጋይዳንስ (ከስነ-ልቦና ምክር) እንዲሁም ከስፖርትና መዝናኛ አንጻር በቂ ዝግጅት መደረጉ በመድረኩ ተመላክቷል።
መማክርት ጉባኤው የቀረበውን አካዳሚክ ካሌንደር ገምግሞ በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን፤ ነባር መደበኛ ተማሪዎች ሕዳር 5 እና 6/2015 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲው በመግባት ምዝገባ እንዲያካሄዱ ተወስኗል።
ጥሪ የተደረገላቸው ነባር መደበኛ ተማሪዎች ከወዲሁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ በተጠቀሱት ቀናት ምዝገባ እንዲያካሄዱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ አሳስበዋል።
381 views18:14