2022-11-30 02:08:58
ኅዳር ፳፩
ጽዮን ማርያምኅዳር ሃያ አንድ በዚች ቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የበዓሏ መታሰቢያ ነው።
“ታቦተ ጽዮን” የሚለውንም ስያሜ ያገኘችው ጽዮን ተብላ በምትጠራው የእስራኤል ከተማ ስም ነው፡፡ ጽዮን ማለት ተፀወነ፡ ተጠጋ፣ ተማጠነ ማለት ነው፡፡ ክቡረ ዳዊትም ጽዮንን አምባ፣ መጠጊያ አድርጎ ብዙ ጠላቶቹን ተዋግቶ አሸንፎ ድልን ተጎናጽፏል።
ጽዮን የተባለችው የታላቁ የዳዊት ከተማ የተገፉና የተበደሉ ሕዝቦች ሁሉ እውነተኛ ፍርድ ለማግኘት፣ ተሰብስበው የሚሰነብቱባት ከተማ ስለነበረች፣ ጽላተ ሙሴም በዚያ ስለነበረች በርሷ ተማጽነውም ችግራቸው ሰለሚቃለል ታቦቷ “ታቦተ ጽዮን” ተብላለች፡፡
ታቦተ ጽዮን ብዙ ጊዜ "ጽላተ ኪዳን፣ ታቦተ ሕጉ" እየተባለች ትጠራለች። "ጽሌ" ማለት "ሰሌዳ" እንደ ማለት ሲሆን "ጽላት" ደግሞ በብዙ ቁጥር ነው። "ኪዳን" ደግሞ በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል ያለ "ውል - ስምምነት" ነው።
"ታቦት" ማለት "ማሕደር-ማደሪያ" እንደ ማለት ነው። ሕጉ የተጻፈባቸውን ሰላድው "ጽላት" ስንላቸው የጽላቱ ማደሪያ ደግሞ "ታቦት" ይባላል። ጽላት (ታቦትን) ያመጣ ፈጣሪ ነው። በሐዲስ ኪዳንም ምሥጢርና ሐተታ ቢኖረውም 2 ቦታ ላይ ስለ ታቦት ተጠቅሶ እናገኛለን። (2ቆሮ.6፥16 ፣ ራዕይ.11፥19)
የአምላክ ማደሪያ ቅድስት ድንግል ማርያም በቃል ኪዳን ታቦት ትመሰላለች ይኽቺም ፦
✿ የእግዚአብሔር የጌትነቱ መግለጫ የኾነችው፤
✿ በፍልስጥኤም ይመለክ የነበረ ጣዖትን ቀጥቅጣ ያጠፋች፤
✿ በድፍረት ሊነካት የሞከረ ኦዛን የቀሰፈች፤
✿ በታላቅ ክብር ወደ ሀገሯ ስትመለስ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በታላቅ መንፈሳዊ ደስታ በፊቷ የዘመረላት ፤
✿ ልጁ ሰሎሞንም ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርቶ በክብር ያኖራት ናት፡፡
ጌታ የታቦቷን አሠራር ሲነግረው "ሽምሽር ስጢን ከሚባል ከማይነቅዝ እንጨት ቀርጸኽ አብጅ ከታች እንደ ዙፋን አራት እግር አውጣለት ሞላልነቱን ኹለት ክንድ ከስንዝር ቁመቱ ክንድ ከስንዝር ወርዱን ክንድ ከስንዝር ኹለት ክንድ ከስንዝር ምስሃል ለዚኽ ቁመት የለውም አራት ቀለበት ኹለት ሙሎጊያ አበጅለት አፍአውን ውስጡን በንጹሕ ወርቅ ለብጠው በምስማኩና በምስማኩ ኹለቱን ኪሩቤል እንደሚናተፉ አውራ ዶሮዎች አንገታቸውን ደፋ አድርገኽ በላይ ሣልበት ዙሪያውን ፈለግ አውጣለት ብጽብጽ ወርቅ አፍስበት ጽላቶቹን በውስጡ አኑር" ብሎታል፡፡
ይኸውም ምሳሌ
ታቦት ፡- የእመቤታችን
ወርቅ፡- የንጽሕናዋ የቅድስናዋ
ታቹ መቀመጫው ፡- የንጽሓት እንስት
ላዩ መግጠሚያው ፡- የንጹሓን አበው
ግራ ቀኙ ፡- የሐና የኢያቄም
ወደ ውስጥ የገባችው:-የድንግል ማርያም ያቺ በመኻከላቸወም እንደኾነች እመቤታችንም ከሐና ከኤያቂም ለመገኘቷ ምሳሌ ነው።
ኹለት ክንድ ከስንዝር:- ከአዳም እስከ ኖኅ ባለው ዘመን 2260 ዘመን ይመስላል ይኸውም በኖኅ ዘመን አርአያ ድንግል ታቦተ ኖኅ ለመገኘቷ ምሳሌ፡፡
አንድ ክንድ ከስንዝር ቁመቱ :- ከኖኅ እስከ ሙሴ ባለው ዘመን ይመስላል ይኸውም 1600 ዘመን ነው። በዚህ ዘመን አርአያ ድንግል ጽላተ ሙሴ ለመገኘቷ ምሳሌ ነው፡፡
አንድ ክንድ ከስንዝር ወርዱ:- ከሙሴ እስከ እመቤታችን ባለው ዘመን ይመስላል ይኽውም 1640 ዘመን ይኾናል ይኽ በኾነ አርአያ ድንግል ታቦተ ኖኅ አርአያ ድንግል ጽላተ ሙሴ ምሳሌዎቿ የሚሆኑ አማናዊት ድንግል ማርያም ለመገኘቷ ምሳሌ ነው፡፡
አራቱ ቀለበት:- የአራት ወገን ንጽሕናዋ ምሳሌ ይኸውም ክርእይ /ኃጢአትን ከማየት/፤ ከሰሚዕ/ኃጢአትን ከመስማት/ ፤ ከገሲስ/በእጅ ዳሰሶ ኃጢአትን ከመሥራት እና ከአጼንዎ /የኃጢአት መዐዛን ከማሽተት/ እመቤታችን ከነዚኽ ኹሉ ተጠብቃለችና
ኹለቱ ቀለበት:- የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ ምሳሌ
ኹለቱ ሥዕለ ኪሩቤል:- የጠባቂ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልና የአብሳሪ መልአክ የቅዱስ ገብርኤል ምሳሌ ናቸው ይኽውም የብሉይ ሊቀ ካህናት በዓመት አንድ ቀን ገብቶ ከኹለቱ ኪሩቤል መካከል ቃል ሰምቶ ይወጣ ነበር ቅድስት ድንግል ማርያም በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል ተጠብቃ ከቅዱስ ገብርኤል ቃል ሰምታ አካላዊ ቃልን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ያለ ዘር ያለ ሩካቤ ፀንሳ ተገኝታለችና።
ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ይኽንን መንፈሳዊ ምስጢር በጥልቅት በመመርመር ድንግል ማርያምን ፡-
በምስጢር የተመላች ታቦት
እሳትን የተመላች ታቦት
የቅዱስ ቃል ታቦት
የቃል ኪዳን ታቦት በማለት ገልጿታል፡፡
ኅዳር 21 ቀን የሚከበረውም የእመቤታችን ምሳሌዎች የተገለጡበት እና የተለያዩ ሥራዎች የተሰሩበት ዕለት ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህም፡-
1. ነቢዩ ዘካርያስ ሁለንተናው ወርቅ የሆነ፣ የዘይት ማሰሮ በራሱ ላይ የነበረበትንና ሰባት መብራቶች ያሉትን መቅረዝ ሲያበራ ያየበት ዕለት ነው፡፡ ዘካ. 4፤1-2። ዘካርያስ ያየው ብርሃን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዮሐ. 8፤12፡፡ ይህ ብርሃን የታየባትና የተገለጠባት መቅረዝ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፡፡ ብርሃን መቅረዝ እንዲያዝና እንዲገለጥ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ተገልጦልናል፡፡ ጨለማ ዓለምን አብርቷል፡፡ ብርሃን ክርስቶስን ወልዳለችና እርሷም እመ ብርሃን / የብርሃን እናት/ ትባላለች፡፡
2. ታቦተ ጽዮን ዳጎንን ገልብጣ በመጣል ኃይሏን የገለጠችበት ዕለት ነው፡፡ በፍልስጥኤማውያን ተማርካ ቤተ ጣዖት ወስደው ከጣዖታቸው ከዳጎን በታች አስቀምጠዋት ነበር፡፡ ታቦተ ጽዮን ግን በላይዋ ያለውን ዳጎንን ገልብጣ ጥላ እርሷ ከላይ ተቀመጠች፡፡ በታቦት የሚገለጠው የእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡ ምክንያቱም በታቦቱ ላይ ያለው ሕገ እግዚአብሔርና ስመ እግዚአብሔር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ስም የጸና ክንድ ነውና ሁሉን ያሸንፋል። ስለዚህ ምንም እንኳ ለጊዜው ስትማረክ ደካማ ብትመስልም መማረኳ ግን ኃይሏን ለመግለጥ፣ ለአሕዛብ የጣዖትን ከንቱነት የታቦትን ክቡርነት ለመግለጥ ነበር፡፡
3. ቀዳማዊ ምኒልክ ታቦቱን ይዞ አክሱም የገባበት፣ ንግሥት ሳባ ታላቅ በዓል አድርጋ የተቀበለችበት፣
4. አብረሃ ወአጽብሐ በአክሱም ከተማ 12 ቤተ መቅደስ ያለው ቤተ ክርስቲያን በአስደናቂ ሁኔታ ሠርተው ከጨረሱ በኋላ ቅዳሴ ቤቱን ያከበሩበት፣ እንዲሁም
5. በ9ኛው መ/ክ/ዘመን ዮዲት ክርስትና ለማጥፋት በተነሳች ጊዜ በእርሷ ምክንያት ታቦተ ጽዮን ወደ ዝዋይ ሐይቅ የተሰደደችበት፡፡ በኋላም የሰላሙ ዘመን ሲመጣ ተመልሳ አክሱም የገባችበት በዚሁ በኅዳር 21 ስለሆነ በእነዚህ በተደራራቢ ታሪኮች ምክንያት በየዓመቱ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል “ኅዳር ጽዮን በአክሱም ጽዮን” የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡
የእመቤታችን ልመናዋ ክብሯ አማላጅነቷም ከእኛ ከህዝበ ክርስቲያን ጋር ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር! አሜን!
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
951 views23:08