2021-07-31 20:03:55
ውርስ አጣሪው የተሾመበት ኑዛዜ ዋጋ ያለው ኑዛዜ መሆኑ አከራካሪ ሆኖ ሲገኝ ወይም፣
በሌላ ምክንያት ውርስ አጣሪውን በመለየት ላይ የሚያጠራጥር ነገር ሲኖር ወይም፣
ብዙ ውርስ አጣሪዎች ለምሣሌ ስልጣናቸው 947 የሚመነጭ ብዙ ያለ ኑዛዜ ወራሾች ኖረው በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 958 በሚደነግገው መሠረት ውርሱን በመተባበር በመግባባት ለማስተዳደርና ለማጣራት ያልተስማሙ እንደሆነ ወይም፣ ከወራሾቹ መካከል አንዱ አካለ መጠን የላደረሰ ልጅ ወይም የተከለከለ ሰው ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት ለምሣሌ በአገር ባለመኖሩ፣ እብደቱ በግልጽ ያልታወቀ ሰው በመሆኑና በሌሎች ምክንያቶች ጥቅሙን ለማስከበር የማይችል በሆነ ጊዜ ወይም፣
የውርሱ አስተዳዳር ወይም የማጣራቱ ስራ ልዩ ችግር ያስነሣና ልዩ ሙያ ያላቸውን ሰወች ወይም ሌላ ችግሩን ለመቅረፍ የሚችል የውርስ አጣሪ መሰየም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወይም፣
በሕግ ሟች ኑዛዜ ወይም በዳኞች የተሰየመው አጣሪ ቸልተኛና ትጉህ ያልሆነ እንደሆነ ወይም የማጭበርበር ባህሪ የሚታይበትና ሀቀኝነት የጉደለው የሆነ አንደሆነ ወይም አጣሪው የማጣራት ስራውን በሚገባ ለመፈፀም ችሎታ የሌለው መሆኑ የታወቀ እንደሆነ፣
ዳኞች ከማናቸውም በጉዳዩ ያገባኛል ከሚል ባለጉዳይ ጥያቄ አቅራቢነት በሕግ፣ በኑዛዜ ወይም በፍርድ ቤት ውሣኔ ተሰይሞ የነበረውን የውርስ አጣሪ በመሻር በአካባቢው ውል ለማዋዋል ስልጣን የተሰጠውን ሰው ወይም ማናቸውንም ለስራው ብቁ ነው ብለው የሚመርጡትን ሌላ ሰው በውርስ አጣሪነት ለመሰየምና ለመተካት እንደሚችሉ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 951 ተመልክቶ እናገኘዋለን፡፡
በውርስ ህጋችን በግልጽ እንደተመለከተው በህግ፣ በሟች ኑዛዜ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ የተመረጠ ወይም የተተካ የውርስ አጣሪ የሚከተሉት ግዴታዎችና ሀላፊነቶች ይኖሩበታል፡፡
ሟች በህይወት ዘመኑ ያደረገው ኑዛዜ ካለ ኑዛዜውን መፈለግና የሟችን የኑዛዜ ወይም ያለኑዛዜ ወራሾች እነማን እንደሆኑ ማረጋገጥ፣
የውርስ ንብረት ከብልሽትና ከብክነት ለመታደግ ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ በመውሰድና ሌሎችንም አስፈላጊ ተግባራት በመፈጸም የውርሱን ሀብት ማስተዳደር፣
በግልጽ የታወቁ፣ ክርክርን የማያስነሱ መከፈል ያለባቸውን የውርስ እዳዎች በፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 1014 በተቀመጠው ቅደም ተከተል መሰረት መክፈል፣
ሟቹ በልዩ ኑዛዜ ያደረጋቸውን ስጦታዎች መክፈልና የሟችን የኑዛዜ ቃል ለመፈጸምና ውጤት ለመስጠት ማንኛውንም አስፈላጊ ጥንቃቄ ማድረግ፣
ጥያቄው ያገባኛል በሚል ማናቸውም ባለጉዳይ ሲቀርብና ዳኞችን የሚያሳምን ሆኖ ሲገኝ ስለስራው መልካም አፈጻጸም አንድ ዋስ ወይም ሌላ የመልካም ስራ አፈጻጸም ማረጋገጫ ሊሆን የሚችል መያዣ ማቅረብ፣
ስራውን ለመተው ሲፈልግ አዲስ አጣሪ እስከሚሰየምና ተተክቶ ስራውን እስከሚጀምር ድረስ የአጣሪነት ስራውን የማከናወን፣
ሟች በአደረገው ኑዛዜ ስለአጣሪነቱ የስልጣን ወሰንና ስለስራው አፈጻጸም የሰጠውን መመሪያና ትእዛዝ ተከትሎ የመስራትና ዳኞችም ስለስልጣኑ ወሰንና ስለስራው አፈጻጸም የሚሰጡትን ትእዛዞች በማክበር የአጣሪነት ስራውን ማከናወን፣
ውርሱን አጣርቶ ከጨረሰ በኋላ ለወራሾቹ ስለማጣራቱ የስራ ክንውን ሪፖርት ማቅረብ፣
ውርስ አጣሪው ማናቸውንም የህጉን ድንጋጌዎች በሟች ኑዛዜ የተሰጡትን መመሪያዎች ወይም በዳኞች የተሰጡትን ትእዛዞች በሚቃረን በጥፋቱ ወይም በቸልተኝነቱ መንገድ ለሚያደርጋቸው ጉዳዮችና በዚያ መሰረት ለሚደርስ ጉዳት በሀላፊነት የመጠየቅ ግዴታ እንዳለበት፣
ከፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 952፣ 954-957 እንደዚሁም የፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 960 እና 961 በማየት መረዳት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ህጉ በህግ፣ በሟች ኑዛዜ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ በውርስ አጣሪነት ለሚሰየሙ ሰዎች ያስቀመጠላቸው መብት አለ፡፡ ከመብቶቹ መካከል እጅግ በጣም አስፈላጊው የውርስ አጣሪነት ስራ ማንም ሰው በፈቃዱ ብቻ ሊያከናውነው የሚገባና ማንም ሰው ያለፈቃዱ የአጣሪነት ስራዎችን ለመቀበል የማይገደድ መሆኑ ነው፡፡ አንድን ተግባር አንድ ሰው ተገድዶ እንዲያከናውን ማድረግ የተከለከለና መሰረታዊ የሆነውን የሰው ልጅ ነጻነት መብት የሚነካ በመሆኑ የውርስ አጣሪነትን ተግባር አንድ ሰው ሳይፈልግ እንዲቀበልና እንዲሰራ ማድረግ እንደማይቻል የፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 953 በግልጽ ይደነግጋል፡፡ ሁለተኛው መብቱ ደግሞ ውርስ አጣሪው ስራውን እፍጻሜ ለማድረስ ወይም ለተወሰነ ጊዜ ለመስራት በግልጽ ግዴታ የገባ ካልሆነ በቀር በማናቸውም ጊዜ ስራውን መተው የሚችል መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ በጥንቃቄ መታየት ያለበት ጉዳይ ‹በግልጽ ግዴታ የገባ ካልሆነ በቀር› የሚለው ሀረግ ነው፡፡ በዝምታ በህግ፣ በሟች ኑዛዜ ወይም በዳኞች የውርስ አጣሪ ሆኖ እንዲሰራ መመረጡን ተቀብሎ ስራ መጀመሩ ብቻውን የማጣራት ስራውን በማናቸውም ጊዜ የመተው መብቱን አያስቀርበትም፡፡ ስራውን የመተው መብቱ ቀሪ የሚሆነው በግልጽ እራሱን ግዴታ ያስገባ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡
ሌላው እዚህ ላይ መታየት ያለበት ውርስ አጣሪው ይህንን የማጣራቱን ስራ የመተው መብቱን እንደፈለገው ሊጠቀምበት አይችልም፡፡ የሟች ውርስ ንብረት የግድ መጠበቅና በጥንቃቄ መያዝ ስለሚገባው ሌላ ተተኪ አጣሪ እስኪመረጥና ስራውን እስኪረከብ ድረስ ስራውን እየሰራ መቆየት ያለበት መሆኑ የፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 954 ድንጋጌዎችን በማየት ለመረዳት ይቻላል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ለውርስ አጣሪ የተቀመጠለት መብት አጣሪው ውርሱን ለማጣራት ለሰራው ስራ የአገልግሎት ዋጋ የማግኘት መብት ያለው መሆኑ ነው፡፡ የውርሱ አጣሪ የአገልግሎት ክፍያውን የሚያገኘው ሟች በኑዛዜው ውስጥ በሰጠው መመሪያ ወይም ወራሾቹ በሚያደርጉት ስምምነት ወይም ዳኞች በሚሰጡት ውሳኔ መሰረት ሊሆን እንደሚችል የፍትሀ ብሄር ህግ ቁጥር 959 ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም አጣሪው ውርሱን በማጣራት ለሰራው ስራና ግልጋሎት ከውርሱ ንብረት ላይ ከላይ ባስቀመጥናቸው ሁኔታዎች ሲወሰንለት የአገልግሎት ዋጋ የማግኘት መብት እንዳለው መታወቅ ይኖርበታል፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የውርስ ህግ መሰረት ‹ውርሱን ስለማጣራት› የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ምንነትና ይዘት እንደዚሁም ጠቀሜታ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ የመጀመሪያው በምእራፍ ሁለትም ለመጠቆም እንደተሞከረው ‹የሟች ውርስ መከፈት› እና ‹የሟችን ውርስ ማጣራት› የሚሉት ጽንሰሀሳቦች እጅግ በጣም የተለያዩ ናቸው፡፡ የሟች ውርስ መከፈት የምንለው ሟች ህይወቱ ካለፈበት ቅጽበት ጀምሮ ምንም አይነት የሲቪል መብት ግዴታ ሊኖረው ስለማይችል ህጉ የሟች ህይወት ካለፈችበት ሰኮንድ ጀምሮ የሟች መብትና ግዴታ ለሟች ወራሾች ለማስተላለፍ የሚያደርጋቸውን ጥንቃቄ የሚመለከት ነው፡፡
የሟች ውርስ የሚከፈተውም ሟች መኖሪያ ስፍራና ሟች በሞተበት ጊዜ እንደሆነ በፍትሀ ብሄር ህግ ቁጥር 826 ተመልክቷል፡፡ የሟችን ውርስ ማጣራት የምንለው ደግሞ የሟችን ያለኑዛዜና በኑዛዜ ወራሾች የሚለዩበት፣ የሟች እዳ የሚከፈልበት፣ የሟች አበዳሪዎች እና ተበዳሪዎች የሚለዩበት፣ ንብረቱ በሟች ወራሾች እስኪተላለፍና ውርሱ እስከሚዘጋበት ቀን ድረስ የንብረት ማስተዳደር ስራዎች የሚከናወንበት ውስብስብ ተግባር ነው፡፡
3.9K views17:03