Get Mystery Box with random crypto!

የኢትዮጵያ ዜግነትን ስለማጣትና ፤ የሌላ ሀገር ዜግነት በማግኘት የኢትዮጵያ ዜግነት ስለሚቀርበት ሁ | Tsegaye Demeke - Lawyer

የኢትዮጵያ ዜግነትን ስለማጣትና ፤ የሌላ ሀገር ዜግነት በማግኘት የኢትዮጵያ ዜግነት ስለሚቀርበት ሁኔታ
===========================
1. #ኢትዮጵያን ዜግነት ስለመተው
የሌላ አገር ዜግነት ያገኘ ወይም ሊሰጠው ቃል የተገባለት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን የመተው መብት አለው፤
ዜግነቱን ለመተው የፈለገ ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣኑ በሚወስነው ቅጽ መሠረት አስቀድሞ ለባለሥልጣኑ ማሳወቅ አለበት፤
ለአካለ መጠን ያላደረሰ ሰው ዜግነቱን ለመተው የሚችለው በወላጆቹ የጋራ ውሳኔ ወይም ከወላጆቹ አንዱ የውጭ አገር ሰው ከሆነ ኢትዮጵያዊ በሆነ ወላጁ ውሳኔ ይሆናል፤
ዜግነቱን ለመተው መፈለጉን ያሳወቀ ኢትዮጵያዊ፣
የሚፈለጉበት ብሔራዊ ግዴታዎች ካሉ እነዚህኑ ከመወጣቱ፣ ወይም በወንጀል ተከስሶ ወይም ተፈርዶበት ከሆነ ከክሱ ነፃ ከመደረጉ ወይም የተወሰነበትን ቅጣት ከመፈጸሙ፤ በፊት የዜግነት መልቀቂያ አይሰጠውም።
ባለሥልጣኑ የዚህ አንቀጽ ድንጋጌዎች መሟላታቸውን ካረጋገጠ በኋላ ዜግነቱ የሚቋረጥበትን ቀን የሚገልጽ የዜግነት መልቀቂያ የምስክር ወረቀት ለባለጉዳዩ ይሰጠዋል፡
የዜግነት መልቀቂያ የምስክር ወረቀት ያልተሰጠው ማንኛውም ባለጉዳይ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡
2. #የሌላ ሀገር ዜግነት በማግኘት የኢትዮጵያ ዜግነት ስለሚቀርበት ሁኔታ
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በራሱ ፍላጎት የሌላ አገር ዜግነት ካገኘ ዜግነቱን በራሱ ፈቃድ እንደተወ ይቆጠራል፣
ከወላጆቹ አንዱ የውጭ አገር ዜጋ በመሆኑ ወይም በውጭ አገር በመወለዱ የሌላ አገር ዜግነት ያገኘ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን አስቀድሞ እንዲተው ካልተደረገ በስተቀር ለአካለ መጠን ካደረሰ በኋላ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሌላ አገር ዜግነቱን ትቶ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ለመቀጠል መምረጡን ለባለሥልጣኑ ካላሳወቀ ዜግነቱን በፈቃዱ እንደተወ ይቆጠራል፣
ራሱ ጠይቆ ሳይሆን በማናቸውም ሌላ ምክንያት ላይ ተመሥርቶ በሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት የተነሳ የሌላ አገር ዜግነት ያገኘ ኢትዮጵያዊ፤
ባገኘው የሌላ አገር ዜግነት መብቶች መጠቀም ከጀመረ፣ ወይም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ያገኘውን የሌላ አገር ዜግነት ትቶ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ለመቀጠል መምረጡን ለባለሥልጣኑ ካላሳወቀ ዜግነቱን በፈቃዱ እንደተወ ይቆጠራል።
ከኢትዮጵያ ዜግነቱ በተጨማሪ የሌላ አገር ዜግነት ይዞ የተገኘ ሰው የኢትዮጵያ ዜግነቱ ቀሪ እስከሚሆን ድረስ የኢትዮጵያ ዜግነት ብቻ እንዳለው ሆኖ ይቆጠራል፡፡


#Join_our_telegram_channel
https://t.me/Consultancy2012
Call us for #Legal_Service
Tsegaye Demeke - Lawyer