Get Mystery Box with random crypto!

በወንጀል ክርክር የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያ አቀራረብና በፍ/ቤቱ የሚሰጥ ብይን/ትእዛዝ ====== | Tsegaye Demeke - Lawyer

በወንጀል ክርክር የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያ አቀራረብና በፍ/ቤቱ የሚሰጥ ብይን/ትእዛዝ
=========================
1. የመጀመርያ መቃወሚያ

ተከሳሹ ማንነቱ ካረጋገጠ በላ ፍ/ቤቱ ክሱን ለተከሳሹ ያነብለታል፡፡ ክሱ ግልፅ ስለመሆኑም ይጠይቀዋል፡፡ ተከሳሹ ክሱ ግልፅ መሆኑን ካረጋገጠ በላ የመጀመሪያ መቃወሚያ ካለው ይጠይቃዋል፡፡ የመጀመርያ መቃወሚያ ያለው መሆኑን ኣለመሆኑን ሳያረጋገጥ ፍ/ቤቱ የእምነት ክህደት ቃል ወደ መቀበል መሄድ የለበትም፡፡

በተከሳሹ ሊቀርብ የሚችል መቃወሚያ በሁለት መልኩ ሊታይ ይችልል፡፡ ኣንዳኛ በቁ.130 (1) እንደተመለከተው ተከሳሹ በክሱ ማመልከቻ ፎርም ወይም ይዘት ላይ የሚቀርብ መቃወሚያ ነው፡፡ይህ ዓይነቱ መቃወሚያ በወ/መ/ሕ/ስ/ስ/ቁ.111 እና 112 የተዘረዘሩትን ነገሮች የሚመለከት ነው፡፡

(1) በቁ. 111 ላይ የተመለከቱት ነገሮች ስናይ፤ ማንኛውም የክስ ማመልከቻ፡-

ቀንና ዓመተ ምህረት የተፃፈበትና የተፈረመበት ፣
የተከሳሹ ስም የያዘ ፣
ተከሳሹ የተከሰሰበት እና የወንጀሉ መሰረታዊ ነገር ያካተተ ፣
ወንጀሉ የተፈፀመበት ጊዜና ስፍራ ያመላከተ ፣
የተበደለው ሰው ስም ወይም ወንጀሉ የተፈፀመበት ንብረት (ተገቢ በሆነ ጊዜ) የሚያመለክት፣
ተከሳሹ ወንጀሉን በመፈፀም ተላልፏል የተባለበት የሕግ ዓንቀፅ የያዘ መሆነ አለበት፡፡

(2) በቁ.112 የተመለከተው ደግሞ ተከሳሹ የተከሰሰበትን ወንጀል ለይቶ ኣውቆ መልስ ለመስጠት እንዲችል እያንዳንዱ ክስ ወንጀሉንና ሆኔታውን በዝርዝር መግለፅ እንዳለበት ነው፡፡

ስለዚህ በቁ.111 ወይም 112 ላይ ከተመለከቱት ሁኔታዎች (ነገሮች) ኣንዳንዶቹ በክሱ ማመልከቻ ላይ ያልተካተቱ ሆኖው ያገኛቸው እንደሆነ ተከሳሹ በመቃወሚያ መልክ ሊያነሳቸው እንዲሚችል ነው፡፡

ሁለተኛውና በተግባርም በተደጋጋሚ ሲነሳ የሚስተዋለው መቃወሚያ በቁ.130 (2) ላይ የተደነገገውን ነው፡፡ በዚህ ንኡስ ዓንቀፅ ስር በመቃወሚያነት ሊነሱ የሚችሉ በርከት ያሉ ምክንያቶች ተዘርዝረው የሚገኙ ሲሆን፤ ኣብዛኛዎቹ የመቃወሚያ ነጥቦች በተከሳሹ ወይም በጠበቃው ብቻ ሊነሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ በቁ.130(2) (ሐ) መሰረት የይርጋ ጊዜን ኣስመልክቶ የሚቀርብ ተቃውሞ ግን ተከሳሹ ባያነሳወም ዓቃቤ ሕጉ ሊያነሳው ይችላላ ወይም ፍ/ቤቱ በራሱ ውሳኔ ክሱን መዝጋት ኣለበት (የወ/ሕግ ዓንቀፅ 216 (2)) ፍ/ቤቱ ሌላ ማድረግ ያለበት የተከሳሹ ፍፁም ወይም ከፊል ሃላፊነት ኣጠራጣሪ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ሁሉ ተከሳሹ ተቃውሞ ባያቀርብም ስለዚሁ ነገር ልዩ እውቀት ያለውን የአዋቂ ኣሳብ መጠየቅ ነው፡፡ ቢያስፈልግም በተከሳሹ ጠባይ ፣ ባለፈ ህይወት ታሪኩና በሁኔታዎቹ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ትዝዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡

በተለይ ተከሳሹ የኣእምሮ በሽታ ያለበት ወይም በሚጥል በሽታ የሚታወክ ለመሆኑ፤ ወይም መስማትና መናገር የሚሳነው ለመሆኑ ወይም ኣእምሮን በሚያደነዝዝ ነገር ወይም በመጠጥ አዘዉታሪነት በሽታ የተለከፈ ለመሆኑ የሚያመለክቱ ሁኔታዎች በተገኙ ጊዜ ፍ/በቱ ለዚሁ ልዩ እውቀት ያለውን ሰው ኣሳብ የመጠቅ ግዴታ ኣለበት ፡፡
(የወ/ሕግ ዓንቀፅ 51)

በመቃወሚያነት መቅረብ የሚችል ምን እንደሆነና መቃወሚያው ማንሳት ያለበት ማን እንደሆነ ካየን ዘንድ የሚቀርብበት ጊዜ መቼ ነው? የኣቀራረቡ ፎርምስ ምን መሆን ኣለበት የሚለውን ማየት ኣስፈላጊነቱ ኣጠያያቂ ኣይደለም፡፡

ተከሳሹ መቃወሚያ ካለው ማቅረብ ያለበት ክሱ ከተነበበለት በላ መሆኑን ከላይ ተገልፆዋል፡፡ ክሱ ከተነበበለት በላ ብቻ ሳይሆን መቃወሚያ ካለው ወድያው ማቅረብ አለበት፡፡ ይህ ኣባባል ታሳቢ የሚያደርገው ተከሳሹ ክሱ ከሚሰማበት ቀን ኣስቀድሞ እንዲደርሰው ስለሚደረግ ኣንብቦ ሊነሳ የሚችል መቃወሚያ ለማቅረብ ተዘጋጅቶ ይመጣል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡ ክሱን ወዲያው ካልተቃወመ መቃወሚያውን በላ ማንሳት እንደማይችልም በመርህ ደረጃ በስነ ስርዓት ሕጉ ተደንግጓል (ቁ.130 (3)) ፡፡ ሆኖም ይህ ንኦስ ቁጥር መርህ ብቻ ሳይሆን የመርሁን ልዩ ሁኔታም ደንግጓል፡፡ ይኸዉም፤

“… ፍርድ ቤቱ ሲጠይቀው ተከሳሹ የክሱን ማመልከቻ ወድያው ካልተቃወመ በቀር ቆይቶ እንዲህ ያለውን መቃወሚያ ነገሩ በሚሰማበት በሌላ ጊዜ ሊያነሳ ኣይችልም፡፡ ስለሆነም መቃወም የሚችለው መቃወሚያው የሚፀና ፍርድ ከመስጠት የሚያግድ በሆነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡” የሚል ነው፡፡

እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ጥያቄ “የሚፀና ፍርድ ከመስጠት የሚያግድ” እና ዘግይተውም ቢሆን ሊቀርቡ የሚችሉ መቃወሚያዎች የተኞቹ ናቸው? የሚል ነው፡፡ ለዚህ ጥያቂ መልስ ሊሆኑ የሚችሉ ሶስት ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡
ቁ.130 (2) (ለ) ተከሳሹ በዚሁ ክስ ከዚህ ቀደም ተከሶ ነፃ የወጣ ወይም የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑ ወይም
ቁ.130 (2) (ሐ) ክስ የቀረበበት ወንጀል በይርጋ ሕግ የታገደ ወይም ምሕረት ወይም የኣዋጅ ምሕረት (ይቅርታ) የተደረገለት መሆኑን ወይም
ቁ.130 (2) (ሰ) ለፈፀማቸው ተግባሮች ሃላፊ ያለመሆኑን ባመለከተ ጊዜ ነው፡፡

የመጀመሪያው ምሳሌ ብንመለከት በስነ ስርዓት ሕጉ ብቻ የተቀመጠ ሳይሆን በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ዓንቀፅ 23 ላይም “ማንኛዉም ሰው በወንጀል ሕግና ስነ ስርዓት መሰረት ተከሶ የመጨረሻ በሆነ ውሰኔ ጥፋተኛነቱ በተረጋገጠበት ወይም በነፃ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና ኣይከሰስም ወይም ኣይቀጣም” በሚል መልኩ ተገልፆ ይገኛል፡፡ በሁለተኛው ምሳሌ የተጠቀሰ ይቅርታን በተመለከተም ሕገ መንግስተዊ እውቅና ያገኘ ነው (ዓንቀፅ 71 (7)) ፡፡ እንዲሁም የይርጋ ጉዳይ በፍርድ ቤት ሳይቀር መነሳት ያለበት መቃወሚያ በመሆኑና ሃላፊ ያለመሆን ጥያቄም ኣስገዳጅ ድንጋጌ ሆኖ በወንጀል ሕግ የሰፈረ በመሆኑ ክሱ እንደተነበበ ወድያው ባይቀርቡም የሚፀና ፍርድ ከመስጠት የሚያግዱ በመሆናቸው በማንኛውም ጊዜ ሊነሱ የሚችሉ መቃወሚያዎች ናቸው፡፡

የሚፀና ፍርድ ከመስጠት የሚያግድ መቃወሚያ ሲገኝ ጊዜ ዘግይቶም ቢሆን ሊነሳ ይችላል ብሎ ሕጉ ሲያስቀምጥ ይህን ተከትሎ የሚነሳ ጥያቄ በስር ፍርድ ቤት ሳይነሳ ቀርቶ በይግባኝ ፍርድ ቤት ይግባኙ በሚታይበት ጊዜ ቢነሳስ ተቀባይነት ኣለው ወይ የሚል ይሆናል፡፡ እንግዲህ ይህ ልዩ ሁኔታ ከኣጠቃላይ የሕገ መንግስቱ መርሆዎችና ከቅጣት ዓላማ ኣንፃር መታየት ስላለበት በይግባኝ ፍርድ ቤት በሚሰማበት ወቅት የተነሳ መቃወሚያ ቢሆንም እንኳ ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል፡፡ የመዝገብ ቁጥሩ ማስታወስ ባልችልም በ1967 ዓ.ም አንድ ሰው የግድያ ወንጀል ፈፅሟል በሚል በትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን ማእከላዊ /ከፍተኛ/ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦበት ጥፋተኛ ሆኖ ስለተገኘ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት ይፈረድበታል፡፡ ፍርዱን በመቃወም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባይ ያቀረበ ሲሆን የጠ/ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎትም መዝገቡ ከመረመረ በላ ክሱ በይርጋ ጊዜ የታገደ ሆኖ ስላገኘው በዞኑ ፍ/ቤት የተሰጠን የጥፋተኛነትና የቅጣት ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ይግባይኝ ባይን በነፃ እንዲለቀቅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡