Get Mystery Box with random crypto!

በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪

የቴሌግራም ቻናል አርማ bemaledanek — በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
የቴሌግራም ቻናል አርማ bemaledanek — በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
የሰርጥ አድራሻ: @bemaledanek
ምድቦች: ያልተመደበ
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 2.09K
የሰርጥ መግለጫ

♥አላማው
☞መንፈሳዊ ወንድምነት እህትነት ማጠናከር
☞መንፈሳዊ ምግብን ተመግበን ንስሀ ገብተን በቅዱስ ቁርባኑ የበቃን መሆን
☞ተሞክሮዎችን በማካፈል መልካም ፍሬዎችን ማግኘት
አስተያየት ከለዎ👉 @Hiyab_Nat ያድርሱን 👉ወደ ግሩፕ ለመቀላቀል @egzabehertalakenew

Ratings & Reviews

3.50

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

1

4 stars

0

3 stars

0

2 stars

1

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 2

2022-06-28 11:54:28 2•  ንስሐ    2.1•  ንስሐ ምንድነው? ክፍል - ፩     ✞ ፊትን ወደ እግዚአብሔር ጀርባን ወደ ዓለም ✞    አዳምን ወላጅ ሆኖ ያስገኘ የሥጋ ማኅፀን የለም፡፡ ለመጀመሪያው የሰው ልጅ የመጀመሪያ እናትና አባት አልነበረውም፡፡ የአዳም እናቱም አባቱም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፡፡ አዳም የተጸነሰባት ማኅፀን የአምላክ ፈቃድ ነበረች፡፡    ቀዳሚው የሰው ልጅ ከተጸነሰ በኋላ እስኪወለድ ድረስ…
708 views08:54
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-06-23 13:01:42    የሕይወት ጀርባችን ወደ እግዚአብሔር ሆኖ፤ ከአርያም መቅደስ ስለ ሰው ልጆች መዳን የሚለቀቀውን የቸርነት ብርሃን ማየት ስላቃተን፤ ታይቶ ሳይቆይ የሚጠፋውን የዓለምን ብርሃን ለመጨበጥ ስንል፥ መልሰን እናገኛቸው ብንል የማይቻል፥ ብዙ የዕድሜ ዓመታቶቻችንን አቃጥለናል፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን ፊታችንን ያዞርንለት ብርሃን የተረጋገጠ ዋስትና አስይዞ፤ የመኖር ሕልውናችንን ሊያሳርፈውና ሊያረጋጋው አልቻለም፡፡

   እረፍት የተነፈገና መረጋጋት ያጣ ስብእና ደግሞ ሰላም የለውም ውኃ ሲቀጥንም ሆነ ሲወፍር ይነጫነጫል፡፡ የሚፈልገውን አግኝቶም ሆነ አጥቶ ያኮርፋል፡፡ ከውስጣዊ አካሉ የሚደመጥ እፎይታ ተነፍጎ ዘወትር ይቅበዘበዛል፡፡ ከገንዘብ፣ ከውበት፣ ከእውቀት፣ ከሥልጣንና ከአቅም ውስጥ አደላድሎ የሚያስቀምጥ አንድ የሰላም ወንበር እየፈለገ ይኳትናል፡፡ ግን የለም አያገኝም፡፡

   ንስሐ ያልገባች ነፍስ፤ እነዛ በመጀመሪያ አዳም ጋር የተሰሙት ፍርሃት፣ ማጣት፣ ባዶነት፣ ብቸኝነት የተባሉ ስሜቶች ስለሚሰሟት፤ እነዚህን ለማፈን ሲባል በሥጋ ወከባ የሚምታታ ትንንቅ ውስጥ ትገባለች፡፡ ምንም አይነት ሥጋዊ ብልሃትና ሙከራ የነፍስን ክፍተት ይሞላ ዘንድ አይቻለውምና፤ ፍርሃቱ ወደ ጭንቀት፣ ማጣቱ ወደ ብስጭት፣ ባዶነቱ ወደ ተስፋ መቁረጥ፣ ብቸኝነቱ ወደ ጣዕም አልባ ሕይወት እየተሸጋገረ፤ አድራሻ ጠፍቶት እንደሚባትት መንገደኛ ወዲህም ወዲያም እየተራወጠች ትንከራተታለች፡፡

   ነፍስ በባሕሪይዋ የእግዚአብሔር አካል ናትና፤ የሰው ልጅ ስብእና ሲፈጠር ይሄድ ወደነበረበት፥ የእግዚአብሔር ፈቃድ ወደሆነው ከፍታ መርቀቅን ሁልጊዜ ትፈልገዋለች (የሞትን ነገር ውስጣችን የሚጠላብን ለዚህ ነው) ፡፡ ይህ ማለት ነፍስ ከስድስተኛው ቀን ወደ ሰባተኛው የእረፍት ቀን የመሻገር ስበት በረቂቅነቷ ውስጥ አለ፡፡ ከላይዋ ሆኖ ጀቡኖ የያዛት ሥጋ ግን ወደ መጣበት አፈር ለመመለስ ይፈጥናልና፤ ይሄ የሥጋና የነፍስ መስተቃርናዊ ሂደት የሚታረቀው፤ የሰው ልጅ ንስሐ በሚባል መንገድ ላይ መጓዝ ሲጀምር ብቻ ነው፡፡

   እንዲህም ከሆነ፤ ንስሐ ማለት ነፍስና ሥጋን በአንድ መንፈሳዊ ክር ሰፍቶ የሚያይዝ የምሕረት መርፌ ነው፡፡ በአካላችን ውስጥ የሚገኙ ሰማያዊና ምድራዊ ማንነቶችን አንድ ገጽ የሚሰጥ ልዩ መታወቂያ ነው፡፡ እርስ በእርስ የሚጣሉ ሁለት ባሕሪያትን የሚያስማማ መለኮታዊ ሸንጎ ነው፡፡

 {ዓለም}  ☜☜ሥጋ   ነፍስ☞☞ ️ {እግዚአብሔር}
 {ዓለም} ☞☞ሥጋ  ️[ንስሐ]  ነፍስ☞☞ {እግዚአብሔር}
                 
   ሞትና ትንሣኤ ስለሚባሉትም ጉዳዮች እዚህ ጋር ማንሣት እንችላለን፡፡ ሞት በመንፈሳዊ ፍቺው ሲተነተን በአጭሩ የሥጋና የነፍስ መለያየት ማለት ነው፡፡ ከላይኛው አንቀጽ ባወጋነው አሳብ ስንመለከተው፤ የነፍስና የሥጋ የተለያየ ጉዞ የመጨረሻ ውጤት እንበለው፡፡ ከአፈር የተገኘው ሥጋ ወደ "አፈር ትመለሳለህ" የሚልን ፈቃዱን የተከተለ ውሳኔ ስለሰማ፤ ወደ ተፈጠረበት ምድር ባሕሪይው እየተጎተተ .. እየጎተተ ይሄዳል፡፡ ይሄ መቼም የማይቀር ነው፡፡ ሥጋ የለበሰ ሰው ሁሉ ወደ ሞት ይጓዛል፡፡

   ሰውን የቱን ያህል መንፈሳዊ ብርታትና ጽናት ይኑረው ወደ ሞት የሚገሰግሱበት የሥጋ ባሕሪያት ራሳቸውን የቻሉ ጾር እየሆኑ ያስቸግሩታል፡፡ ፍጹም የሆነው መለኮት እንኳ ሥጋ በተዋሐደው ጊዜ "መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው" ሲል የሥጋን ታላቅ መገዳደር አስታውቆአል፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል 26፥41)

   በመጀመሪያው የማኅፀን ሥርዓት የሚወለደው ሥጋ ከፊቱ የሚጠብቀው ሞት ነው፡፡ ነፍስ የቱን ያህል ብትታገለውም የመፍረስን ሕያው ቃል በባሕሪዩ አንዴ ያደመጠው ሥጋ፤ በየዕለቱ ቀን በቆጠረ ቁጥር እየፈረሰ እየፈረሰ ይሄዳል፡፡ ታዲያ ምን ይሻላል?

   ማኅፀኒቱ መለወጥ አለባት፡፡ የመጀመሪያቱ ሔዋን ከእባቡ ጋር በፈቃድ ተስማምታ ከእርሷ የሚወለደው ዘሯን ሁሉ ወደ ሥጋ ፈቃድ አንከባላ አስገብታዋለች፡፡ ስለዚህ ሌላ የአወላለድ ሥርዓት ያስፈልጋል .. መንፈሳዊ ማኅፀን!

   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የሚያሳድደውን የአዳምን ባሕሪይ ገንዘብ አድርጎ በሥጋ የተወለደው ለዚህ ነው፡፡ ወደ ሞት እየገሰገሰ የሚሄደውን ሥጋ እስከ መጨረሻ ታግሦ ተከተለውና፤ ሥጋ በመስቀል ላይ "በቃ" ብሎ ሲጨርስ፤ መሞት የሌለበት መለኮት፥ የተዋሐደውን ሥጋ አዲስ ሥርዓት አሳየው፡፡ ከመቃብር አነሣው፡፡ ፈርሶ ከመቅረት ነጻ አወጣው፡፡

   ይህንን አዲስ የትንሣኤ ሥርዓት እኛ እንድናገኘው ደግሞ፤ ከጎኑ ደምና ውኃ ሆና ከወጣቺው አዲስቷ ሔዋን (ቤተክርስቲያን) ጋር ሰማያዊ ጋብቻ ፈጽሞ ከማይጠፋ ዘር ወለደን፡፡ አሁን ዳግም ከመንፈስና ከውኃ የሚወለድ ሥጋ፤ እንደ ቀዳሚው አዳም በሥጋ ማኅፀን ከመወለዱ የተነሣ ሞትን ቢቀምስም፤ ለሁለተኛ ጊዜ በተወለደበት ማንነቱ በኩል ግን ሞትን ድል አድርጎ ይነሣል፡፡ "አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር" ይሆናል፡፡ በትንሣኤ ነፍስና ሥጋ ስለማይለያዩ ሞት የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡

   እንኪያሳ ከዚህ ገለጻ አንጻር ደግሞ ንስሐ ማለት፤ ከሥጋ ፈቃድ የተወለደው ሥጋ ወደ ሞት እየገሰገሰ ከነፍስ ለመለያየት ሲቸኩል፤ ነፍስንም አራውጦ ይዟት እንዳይሞት (ኃጢአትን እንዳያትምባት) የሚከላከል ጠበቃ ነው፡፡ ሰው ንስሐ እየገባ ነው ማለት፤ በመሲሑ ድንቅ ሥራ አምኖ ዳግም የተወለደበት ሥርዓት እንዳይበላሽ እየጠበቀ ነው ማለት ነው፡፡

   "የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና"፤ ከፈጸመው ኃጢአት ለመላቀቅ ሲል ንስሐ የማይገባ ሰው፤ ዳግም ቢወለድም እንኳ ከፈቃደ እግዚአብሔር የመለየቱ መግፍኤ ከትንሣኤው በኋላም እንዲሞት ያደርገዋል፡፡ (ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥23) ስለዚህ ንስሐ የማይገባ ሰው "ሁለት ሞት" ይሞታል ማለት ነው፡፡ አንደኛ የሥጋ ባሕሪይን በመያዙ የሥጋን ሞት ይሞታል፤ ሁለተኛ ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን ባለመፍቀዱ ምርጫው ተከብሮለት ቀደም ሲል አምላክን አልፈልግም ወዳለው ወደ ዲያቢሎስ ማደሪያ እንዲሄድ ይሆናል፡፡ ይሄ ደግሞ ለነፍስ ሞት ነው፡፡

   ነገሩስ ያለ ንስሐ የሚመላለስ ምዕመን፤ ሦስት ሞት ነው የሚሞተው፡፡ ንስሐ ማለት ፊትን ወደ እግዚአብሔር ጀርባን ወደ ዓለም አድርጎ የመጓዝ ሂደት ነው ብለን ጀምረናልና፤ ከንስሐ ሕይወት ተለይቶ የሚኖር ሰው በተገላቢጦሽ ፊቱን የሚያዞረው በቁም ወደ ምትገለዋ ዓለም ነው፡፡ በዓለም ውስጥ የመኖር ሕግ መንፈሳዊ ጠባያትን ይገላል፡፡ 'ለሥራው ዕድገት ስትል ዋሽ፣ ለትምህርት ስኬት ነውና ኮርጅ፣ ለገንዘቡ መጠራቀም ጉቦ ውሰድ፣ ብዙ ጥሪት እንዲኖር ለቸገረው አትስጥ፣ ደስታን እንዳታጣ የሰውን ችግር አትስማ፣ ካንተ ውጪ ማንም የለህምና ራስህን ብቻ ውደድ፣ ዘመኑ የፉክክር ነውና የተመኘኸውን ለመጨበጥ ሌላውን ገፍተህ እለፍ፣ ..' እያለ፤ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የተባሉትን ቅዱስ ጠባያት የማንነትህ አካል እንዳታደርግ በዓለም ውስጥ ጩኸቱ ከአድማስ ጥግ እስከ አድማስ ጥግ የሚሰማለት ክፉው መንፈስ፤ በፖሊሲ፣ በመርህ፣ በኑሮ ውድነት፣ በዘመን ለውጥ፣ በእንጀራ ጉዳይ፣ በመኖር ጥያቄ ጀርባ እየተከለለ ሰው የመሆንህን ንጹሕ ጠባያት እንዳትገለጽ በስልት አፍኖ፤ በጠባብ የርኩሰት አስፓልት ላይ ይመራሃል፡፡

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን . . .
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
854 views10:01
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-06-23 13:01:08 2•  ንስሐ

   2.1•  ንስሐ ምንድነው?

ክፍል - ፩

    ✞ ፊትን ወደ እግዚአብሔር ጀርባን ወደ ዓለም ✞

   አዳምን ወላጅ ሆኖ ያስገኘ የሥጋ ማኅፀን የለም፡፡ ለመጀመሪያው የሰው ልጅ የመጀመሪያ እናትና አባት አልነበረውም፡፡ የአዳም እናቱም አባቱም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፡፡ አዳም የተጸነሰባት ማኅፀን የአምላክ ፈቃድ ነበረች፡፡

   ቀዳሚው የሰው ልጅ ከተጸነሰ በኋላ እስኪወለድ ድረስ በምቾት የኖረባት ስፍራ ዔድን ገነት ትባላለች፡፡ ልጅ ከእናት ማኅፀን ተወልዶ ዓይኑን በመግለጥ የመጣበትን ዓለም ለማወቅ እንደሚጀምር፤ የእውቀትን ዛፍ ገና ያልበላው አዳም በገነት ሳለ በእግዚአብሔር የፈቃድ ማኅፀን ውስጥ ነው የነበረው፡፡ ወይንም በቀላሉ ገነትን አዳምን አርግዛ እንዳለች አንዲት ነፍሰጡር በምናብ እንሳላት፡፡ የነፍሰጡሯ የእርግዝና ወራት (አዳም በገነት የሚቆይበት ጊዜ ማለት ነው) "በእግዚአብሔር አንድ ቀን በሰው ልጅ አንድ ሺህ ያህል ዓመት ነበር፡፡" (2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፥8)

   ሺህውም ዓመት ሲፈጸም (ስድስተኛውን ቀን ሲጨርስ) አዳም ከገነት ይወለዳል፡፡ ማለት በሰባተኛው ቀን ላይ የሰው ልጅ ከእውቀት ዛፍ በልቶ ዓይኑን በመግለጥ በወላጁ (በእግዚአብሔር) ክንድ ውስጥ ይታቀፋል፡፡ ወደ ቀጣዩ ሥርዓት ማደግ (መርቀቅ) ይጀምራል፡፡

   የቀደመው ወንዱ ልጅ በገነት መኖሩን እንደቀጠለ፤ በራእየ ዮሐንስ ምዕራፍ ዐሥራ ሁለት ላይ የተጠቀሰው ዘንዶ ብዙ ነፍሳትን በልቶ ሳይወፍር በፊት "የቀደመው እባብ" ሳለ በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ የቀደመቺው ሴት ፊት [አዳምን ሊበላ አስቦ] ቆመ፡፡

   ዘንዶው ከሰማይ ሥርዓት ከእግዚአብሔር እውነትና ፈቃድ በማፈንገጥ ወድቋል፡፡ በዚህም የተነሣ ውድቀት የክፉው መንፈስ ልዩ ማንነትና መገለጫ ባሕሪይ ሆኗል፡፡ ስለ መውደቅ ስናነሣ፤ ውድቀት ወደ ታች እንጂ ወደ ላይ አይመለከተውም፡፡ ምክንያቱም ወደ ላይ አይወደቅም፡፡ በመሆኑም ዲያቢሎስ በመውደቅ ውስጥ ባለ ጠባይ ራሱን ስለሚገልጥ፤ የአሳቡም ሆነ የሥራው መነሻና መድረሻ ሕግ ሁልጊዜ ራሱንም ሌላውንም ወደ ታች መጣል ነው፡፡

   ከላይ በተጨዋወትነው መሠረት፤ የአዳም ሰብአዊ ባሕሪይ ከስድስተኛው ቀን ወደ ላይኛው ሰባተኛው ቀን በመጓዝ ላይ ነበር፡፡ በማብራሪያ ግልጽ ለማድረግ፤ የሰው ልጅ መጀመሪያ የተፈጠረበት ሰብአዊ ተክለ ቁመና ሙሉ በሙሉ ሕያው በመሆንና ባለመሆን መካከል ቦታ ያለ ነበር፡፡ እናም የአዳም ባሕሪይ ከዚህ ከመካከል ላይ ተነሥቶ ፍጹም ሆኖ ወደ ሚቀጥለው ሥርዓት ወደ ሚረቅበት ልዕልና ለመሻገር ሺውን ዓመት በገነት ጨርሶ የሕይወትን እና የእውቀትን ዛፍ በየጊዜያቸው መብላት ያስፈልገው ነበር፡፡

   ሆኖም ውድቀትን በላዩ ይዞ የሚንቀሳቀሰው መንፈስ፤ የፍጡራን ከእግዚአብሔር ፈቃድ መውጣት ልክ እንደርሱ ወደታች መጣልን እንደሚያስከትል ከራሱ ስለተገነዘበ፤ "አትብላ!" ብሎ እግዚአብሔር ያለ ቀኑ እንዳይበላት የከለከለውን የዛፍ ፍሬ እንዲበላ "ሥጋሽ ከሥጋዬ አጥንትሽ ከአጥንቴ" ባላት አካሉ በኩል አዳምን ገፋፋው (መንፈስ ከውስጥ ሲገባ ከገዛ አካላችን ጋር መፋለም የመሰለ ጦርነት ነው የሚከፍተው)፡፡ ያቀደውም ሆነለት፡፡ "አዳም ሆይ ከወላጅህ ከእግዚአብሔር ይልቅ የሚስትህን ፈቃድ ለመፈጸም ወድደሃልና፤ ወደ መጣህበት መሬት ተመለስ፡፡ አፈር ነህና፤ ወደ አፈርም ትመለሳለህ" የሚል ቃል ከአምላክ ተደመጠ፡፡ የሰው ልጅ ሕልውና ወደ ሰባተኛው ቀን መርቀቅ ትቶ ወደ ኋላ ወደ አንደኛው ቀን (አፈር የተፈጠረው በመጀመሪያው ቀን ነው) በመመለሱ ምክንያት ዲያቢሎስ ውጥኑ ሰመረለት፡፡ ወደ ላይ ከማረግ ይልቅ እንደርሱ ወደታች መውደቅን አዳም በባሕሪዩ እንዲያውቀው አደረገው፡፡

   አዳም ከገነት (ከፈቃደ እግዚአብሔር) ወጥቶ ወደ መጣበት ምድር (የእግዚአብሔር አሳብ ወዳልነበረው) መሬት ሲመለስ፤ መቼም ጀርባውን ለአምላክ ፊቱን ለምድር ሰጥቶ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ አዳም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ተለይቶ በመውጣት የሰው ፈቃድ ወዳመጣው ከፀሐይ ሥርዓት በታች በተወሰነ አኗኗር ውስጥ ገባ፡፡ የአዳምና የሔዋን ከገነት ተለይቶ መውጣት በአካል ብቻ የተከናወነ ሳይሆን፤ በባሕሪይም ጭምር የሚገለጥ እውነት ነው፡፡ ለምሳሌ በአዳም ባሕሪይ ውስጥ የተሰማው ሞት የሰውነትን ባሕሪይ በሚይዙት የአዳም ልጆች ላይ ሁሉ ይዋረሳል፡፡ በተለምዶ "የአዳም ኃጢአት" እየተባለ የሚነገረውም ጉዳይ ይህ ነው፡፡ ስለዚህ አዳም በባሕሪይው ጭምር ነው ከገነት የወጣው ስንል፤ የአዳም ልጆች የሆኑት ሰዎች ሁሉ የሕይወት ገጻቸውን  ወደ መጡበት ምድር (ሥጋ) አዙረው፤ ለእግዚአብሔር ፈቃድና እውነት (ለነፍስ) ጀርባ ሰጥተው ከአምላካቸው ፈቃድ እየወጡ .. እየወጡ ይኖራሉ እያልን ነው፡፡

   ንስሐ የምንላት መንፈሳዊ ሚስጢርም የምትመጣው እዚህ አዳም ፊቱን ከእግዚአብሔር አዙሮ ከወጣባት ቅጽበት ጀምሮ ነው፡፡ የሰው ልጅ "እንደ አምላክ" በመሆን ከንቱ ምክር ተታልሎ ከፈጣሪው ከተጣላ በኋላ፤ አስታራቂ ማኅተም ሆና ከመሃል የምትገባው ረቂቅ ኃይል ንስሐ የምንላት የምሕረት ክፍል ናት፡፡

   ንስሐ የሚለው ቃል በጥሬ ትርጓሜው ጸጸት፣ ሐዘን፣ ቁጭት፣ ቅጣት፣ የኃጢአት ካሳ ማለት ነው (የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት)፡፡ ይህንንም ብያኔ ወደ አዳም ታሪክ መልሰን ስናየው፤ አዳም ከእውቀት ዛፍ በልቶ ራቁቱን መሆኑን ዓይኖቹን ገልጦ ባወቀ ጊዜ፤ የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላለፉ ከውስጡ ጠባይ የነቃ ፍርሃት፣ ባዶነት፣ ብቸኝነትና መገፈፍ ተሰምቶታል፡፡ እነዚህ ስሜቶች በኋላ እጅ ለእጅ ተያይዘው አዳምን ንስሐ ወደምንለው ቦታ አምጥተውታል፡፡ አዳም ባጠፋው ጥፋት ራሱን እየወቀሰ (ቁጭት)፤ ለምን በላሁት በሚል አሳብ እየተብሰከሰከ (ጸጸት)፤ ስላጣው ጸጋና ኃይል እየተከዘ (ሐዘን)፤ እግዚአብሔር ይምረው ዘንድ ለመጠየቅ ለረጅም ጊዜያት ራሱን እየገሠጸና እያለቀሰ ሱባዔ ይዟል (ቅጣትና የበደል ካሳ)፡፡

   እስከአሁን በተነጋገርነው መሠረት ላይ ሆነን ንስሐን ጠቅልለን ስናየው፤ ንስሐ ማለት የሰው ልጆች ባሕሪይ አቅጣጫውን አስተካክሎ ፊቱን ወደ እግዚአብሔር ጀርባውን ወደ ውድቀት የሚያዞርበት ሰማያዊ ሂደት ነው፡፡

   አንድ አማኝ ሰው ንስሐ ገባ ስንል፤ እርምጃውን ወደ እግዚአብሔር መንገድ አቀና እያልን ነው፡፡ በአዳምኛው ቋንቋ ስንናገረው፤ "ወደ መጣችሁበት ተመለሱ" ሲል ወደ ወደድነው የሥጋ ፈቃድ እንድንመለስ ምርጫችንን አክብሮ ለለቀቀን አምላክ፤ "የለም የለም ጌታ ሆይ፥ ተሳስቼ ነውና ወዳንተ (ወደ ነፍስ ፈቃድ) መመለስ እፈልጋለሁ" ብለን የምንናገርበት የተቀደሰ ድምፅ ነው፡፡

   በአንጻሩ ንስሐ አልገባንም ማለት፤ ፊታችንን ወደ ዓለም ጀርባችንን ወደ እግዚአብሔር ሰጥተን እየተጓዝን ነው ማለት ነው፡፡ ንስሐ ሳንገባ የነፍስ ፈቃድ የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት እንኳ ቢኖረን፤ የእምነት አካሄዳችን ጀርባውን ለእግዚአብሔር እንደሰጠ ወደ እግዚአብሔር እንደመሄድ ያለ የኋልዮሽ ጉዞ ነው የሚሆነው፡፡ ፊቱን ለአውራ ጎዳናው ቀጥ አድርጎ መጓዝ ሲችል፤ ወደኋላ እየሄደ መንገዱን የሚያቋርጥ መኪናን ጥሩ ምሳሌ አድርገን ለዚህ እንጠቅሳለን፡፡

በእርግጥም ከንስሐ ራቅ ብሎ የሚገኝ ኑሮአችንን አጢነን ስናየው፤ ፍላጎቱን፣ እቅዱን፣ ሩጫውን፣ ጉልበቱንና ጊዜውን ለሥጋ ጉዳዮች አብዝቶ እያዋለ፤ ከተፈጥሮው ውስጥ ሕይወት ሆና ስለምታንቀሳቅሰው ነፍሱ ግን አጥርቶ ማስተዋል ተስኖት ይታያል፡፡ ይሄ መሬት የረገጠ እውነት ነው ፊትን ወደ ዓለም ጀርባን ወደ አምላክ የሚያሰኘው፡፡
887 views10:01
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-06-15 12:21:57    ቃለ እግዚአብሔርን በአእምሮ ያይደለ በልብ መማር ወደ ፍቅር መልክ ያደርሳል፡፡ ሰፊ ጊዜን ሰጥቶ የአምላክን ቃል ከአንጀት መማር ፍቅርን ያሳድጋል፡፡ ለምን ቢሉ..."የእግዚአብሔር ቃል" በራሱ ፍቅር ነውና፡፡ እርሱ ሥጋ ለብሶ በዓለም ላይ የፍቅር ድምፆችን (ወንጌል) እንዳሰማ ሁሉ፤ ድምፁን ከእውነት በሰማን ጊዜ ፍቅርነቱ ከውስጣችን ሥጋ ይለብሳል፡፡ በአሳብ፣ በእቅድ፣ በድርጊት፣ በአኗኗር ውስጥ ዘልቆ ይገለጻል፡፡ ቃሉ "መንፈስና ሕይወት" ነው፡፡
  
                    ✞ በሌሎች ጫማ መቆም ✞

   የእግዚአብሔርን ፍቅር ከላይ በተገለጹት ሁለቱ መንገዶች እያገኘን፤ ይሄንን ፍቅር ደግሞ ሰዎች ላይ በመተረጎም የተጨባጭነት አቅሙን ማሳደግ ግድ ይለናል፡፡ ምክንያቱም "ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?" (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፥20)

   "ስጠኝ" ያለውን ፍቅር ለሌሎች "መስጠት" ፍቅርን ከነበረው ደረጃ ላይ የማሳደጊያና የማበልጸጊያ መንገድ ነው፡፡ ተወዳጁ ሲያስተምር "ስጡ ይሰጣችኋል" ብሎ ለተማሪዎቹ የነገራቸውም ጉዳይ ይህንን ነው፡፡ ፍቅርን ስጡ፥ ፍቅርም ይሰጣችኋል፡፡ (የሚሰጣችሁ ግን የሰጣችሁት አካል ላይሆን ይችላል)

   ለሌሎች መስጠት እንዲቻለን ደግሞ በሌሎች ጫማ ላይ መቆም ያስፈልጋል፡፡ የሰውን ጉድለት ለመሙላት በሰው ጉድለት መጉደል ያስፈልጋል፡፡ የሰውን ውድቀት ለመውደቅ "ይህ ወድቀት በኔ ደርሶ ቢሆን" ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የሰውን ችግር ለመቸገር "ይህ ችግር በኔ ደርሶስ ቢሆን" ብሎ ማሰብ ያሰፈልጋል፡፡ የሰው ሐዘን ለማዘን የራስን ያለፈ ሐዘን እያሰቡ የአሁንን ስሜት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በወገኑ ቦታ ላይ ራሱን እያስገኘ የማያምሰለስል ሰው እንደምን አድርጎ ፍቅርን መስጠት ይችላል?

   ዛሬ ዛሬ ላይ ዓለማችን በተለይ በዘፈኑና በፊልሙ ላይ ያሰለጠነቺን ፍቅር ዝሙት ተኮሩን የጾታ ግንኙነት ብቻ ነው፡፡ የመዝናኛው ዘርፍ በልብ በተወከለ ሽፋን ተጽዕኖ የሚያደርሰው አእምሮ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ነው በቁንጅና፣ በሐብትና በቁስ የተመሠረተ የጾታ ፍቅርን ትንሽ ደግነት ለውሶ የሚያሳየው (እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ከሌሉ የመዝናኛው ኢንደስትሪ ቀጥ ይላል)፡፡

   ይሄንን የመዝናኛውን ዘርፍ እንደወረደ የጋተው ትውልዳችን፤ ፍቅር ማለት በሌሎች ጫማ ውስጥ ሆኖ መራመድ ሳይሆን በራስ ምቾት ልክ ሌላውን መስፋት አድርጎ፤ መሙላት የሚገባውን ጉድለት ሸሽቶ ሁሉም ውበት ያለውን፣ ሐብት ያለውን፣ ዝና ያለውን ይፈልጋል፡፡ ፍቅር ወደታች መውረድ ሆኖ ሳለ፤ ፍቅርን ፍለጋ ወደላይ ይወጣል፡፡ በዛ ከፍ ባለበትም ቦታም ላይ በፍቅር ስም የሚነግደውን የዓለም ሥርዓት ያገኛል፡፡ እርሱም እንዲህ ብሎ ይመክረዋል "እየመረጥክ ስጥ!"

            ✞ ፍቅርን የሚዋጋ ባሕሪይ መታገል ✞

   ዲያቢሎስን ኃያል እምነት አያስፈራውም፡፡ እርሱም ራሱ አማኝ ስለሆነ፡፡ (የያዕቆብ መልእክት 2፥19)

   ባይሆን በፍቅር ያለች ጥቂት እምነት ታስጨንቀዋለች፡፡ በሰው ልጆች ማመንና በርኩሳን መናፍስት ማመን መካከል የተሰመረው ብቸኛ ድንበር ፍቅር ነው፡፡ እኛ አፍቅረን ማመን ስንችል፤ መናፍስት ጠልተው ነው የሚያምኑት፡፡

   ስለዚህ ዲያቢሎስ ካሉት ባሕሪያችን ውስጥ አትኩሮ የሚዋጋው ፍቅርን ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ጠቅለል ያለው የፍልሚያ ይዘት ይሄ ነው፡፡ የሙሴን አምላክ የሰቀሉት አይሁዳውያን ሙሴን ያምኑ ነበረ፡፡ ፍቅር ግን ጭራሹኑ አልነበራቸውም፡፡

   ይሄ በክርስቶስና በአሳዳጆቹ መካከል ያለው ውጊያ፤ በክርስትና መንገድ ላይ በሚጓዙ ምዕመናን ላይ የዘመኑን ገጽታና ቅርጽ እየዋጀ እስከ ዕለተ ምፅዓት ይቀጥላል፡፡ እኛም በስሙ የተጠራን ክርስቶሳውያን ስንሆን፣ ይሄ ውጊያ በባሕሪያችን ተጽፎ ይቀመጣል፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ በቤተመቅደስ ውስጥ ያሉ ሰዎች እውነተኛውን ቤተመቅደስ ሊያፈርሱ እንደታገሉ፤ ቤተመቅደስ የተባለ ሰውነታችን ውስጥ የሚያደፍጡ መናፍስት የቤተመቅደሳችንን መልክና መሠረት (ፍቅር) ሊያፈርሱ ይታገላሉ፡፡ ይሄ ፍትጊያ ወደ ውጪ ሲገለጥ፤ በስሙ የተጠሩ በቤቱ ያሉ ሰዎች ፈተና ይሆኑብናል፡፡ (በቤተክርስቲያንም ብናይ፥ ሴቲቱን ለማዳከም የሚሮጠው ኃይል ከውጪ ይልቅ የውስጥ ልጆቿን ይጠቀማል)

   በመሆኑም በባሕሪያችን ተመሳስሎ ገብቶ፤ ፍቅርን (የክርስቶስን ባሕሪይ) የሚዋጋ እኛነታችንን በተለየ ትኩረትና አቅም መፋለም ያስፈልገናል፡፡ ፍቅርን ለመስጠት በሞከርንባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ላይ ወደኋላ የሚስበንን ጠባይ (ክፉ መንፈስ) ለብቻው ለይተን በእምነት ጦር ዕቃዎች መቅጣት አለብን፡፡ ፍቅርን እንዳንኖር የተለያዩ የኑሮ ምክንያቶችን መደበቂያ የሚያደርገውን ጠላት ምሽግ ማፍረስ ይጠበቅብናል፡፡

-------------------
ከፍቅር የጀመርነው ዘመቻችን እዚህ ደርሷል፡፡ በቀጣይ ንስሐን የምናይበት መንገዳችንን እንጀምራለን፡፡ ለንስሐ ጉዞአችንም ፍቅር መነሻችን (አልፋ) እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ ቀድሞውኑ ንስሐ ለመግባትም ፍቅር ያስፈልጋላ፡፡ በኃጢአት አጥፍቻለሁ ብሎ ለመጸጸት ምክንያት የሚሆነው ፍቅር ነው፡፡ ያለ ፍቅር ንስሐ እንግባ ብንል ኃጢአትን መዘገብ እንጂ መናዘዝ አይሆንልንም፡፡ ፍቅርን "አንድ ጊዜ አረፍ በል" ካላልነው ብዙ ያስወራናል፡፡ አስጀምሮ ላስፈጸመን ለፍቅር እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን...
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
1.1K views09:21
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-06-15 12:21:34 1•  ፍቅር     1.3•  ፍቅር ከሌለ ምን የለም? ክፍል - ፭ ✞ ዲያቢሎስ አንዳች አለው ✞    መንፈሳዊ ውጊያ ብለን የምንሰይመው በቅዱስና በርኩስ መንፈስ መካከል ያለ ጦርነት ከአጠራሩ ብቻ ለመገንዘብ እንደሚያስችለው የፍልሚያው አጠቃላይ ገጽታ ከዓይን የተሰወረ ረቂቅ ነው፡፡ በግዙፍ ሥጋ አእምሮና አካል የውጊያውን መልክ መረዳት በፍጹም አይቻልም፡፡    ከመንፈሳዊና ከሥጋዊ ባሕሪያት ውሕደት…
986 views09:21
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-06-02 21:04:29    እዚህ ጋር ስለ አንድ የመናፍስት የጥፋት ዘዴ ስናወራ፤ "ሰው አምላክ ሆነ"ን ለመኖር (በተግባራዊ የክርስትና ሕይወት ለመመላለስ) የሚፈቅድ ስብዕና [ቢያንስ በቀላሉ] እንዳይኖረን፤ ክፉዎቹ በባሕሪያችን ውስጥ አስቀድመው ስፍራ ለመያዝ ዛር ሆነው አብረው ከማኅፀን ጀምሮ ተመሳስለው በመወለድ፤ ተዋሕዶ ማለት በምድር እርምጃ ሰማያዊ መንገድን የመሄድ የፍቅር ጉዞ መሆኑን እንዳንረዳ ይከላከላሉ፡፡ እንዴት ነው የሚከላከሉት ስንል፤ አንድ ግለሰብ ከልጅነቱ አንሥቶ የእርሱ ብቻ በመሰለው ጠባዩ ውስጥ እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ነገር የሚሸሽ ሆኖ ሲያድግ፤ በሥጋዊ የሕይወት ጎን አጋድሎ የቁስ አቅጣጫዎችን ብቻ በመከተል ሃይማኖቱን ከባሕል ማክበሪያት በዘለለ ሳይጠቀምበት ረጅሙን ዕድሜ ያቃጥለዋል፡፡

   በእንዲህ አይነት የሕይወት ገጽ ታሪኩን እያሰፈረ የመጣ ሰው፤ በኋላ ላይ ስለ ክፉ መናፍስት አሠራርና ሚስጢራዊ ውጊያ መረጃ አግኝቶ ቢነቃም እንኳ፤ ማንነቱን ገንብቶ የሠራ ባሕሪው ውስጥ ያለ ልምዱ የእግዚአብሔርን ፍቅር ከማወቅ ተነጥሎ ስለቆየ፤ ስውር ባላንጣዎቹን በመዋጋት ጊዜ ሳለ ክፉዎቹ ከዛሬ ነገ እየበረቱ እርሱ ግን እየደከመ መሆኑን ሲያይ ተስፋ ቆርጦ እጅ መስጠት ሰፊ ዕድሉ ይሆናል፡፡

   ነገ የሚጨምሩ የቀን ክፋቶች በኛ ላይ አንዳች እንዳይኖራቸው ወደ ተዋሕዶ አንድነት በፍቅር በኩል ማደግ ያስፈልጋል፡፡

   ቀደም ሲል እንደተነጋገርነው "በእኔ ላይ አንዳች የለውም" ማለት "ስለ ፍቅር በፍቅር ከእግዚአብሔር ጋር አንድ በሆነ ሰውነት ላይ ዲያቢሎስ ማሸነፍ አይቻለውም" ማለት ነው ተባብለናል፡፡ የማቴዎሰ ጽሕፈት እንደነገረን ደግሞ በየቀን ዘወትሮች ላይ ዲያቢሎስ በክፋት አንዳች ለማድረግ መጣሩን ጸንቶ ይቀጥላል፡፡ በሌላ አገላለጽ "እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ" ወደሚለው የተዋሕዶ ከፍታ እንዳናድግ ጠላት ለደቂቃ ሳይተኛ ሴራ ይጠነስሳል፡፡ ከዚህም የተነሣ ነገ ላይ እርግጠኛ ሆኖ የሚጠብቀን ጉዳይ የክፉው መንፈስ ወጥመድ ነው፡፡

    ታዲያ መድኃኒታችን "በእኔ ላይ አንዳች የለውም" ሲለን "ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር የተሳሰረ ሕይወት እስካላችሁ ድረስ የጠላታችሁ ፈተና ባያቋርጥም፤ በእናንተ ላይ ድል ተቀዳጅቶ የአሸናፊነት ጽዋን አይጠጣትም" የሚል ውድ መልእክትን እያስተላለፈልን ነው፡፡ ጥርት ያለ ምስል እንዲኖረን አንድ ምሳሌ እንሳል፡፡

   ከእግዚአብሔር ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ቆመናል፡፡ ከጀርባችን ደግሞ ዲያቢሎስ ከኋላችን ትይዩ በሆነ አንጻር ቦታ ላይ ሆኖ ከፈጣሪ መዳፍ ሊለያየን ወደኋላ ይጎትተናል፡፡ ባላጋራው ስቦ ስቦ ከእግዚአብሔር ነጥሎ እንዳያስቀረን ልንታገልበት የምንችለው አማራጭ የጨበጥነውን እጅ አጥብቆ በኃይል መያዝ ነው፡፡ ዲያቢሎስ ዛሬ የጀርባ ጉትታው እንዳልተሳካለት ሲያይ፤ ነገ ደግሞ በግራ ጎን በኩል መጥቶ ሊለያየን መጎተቱን ይቀጥላል (ነገ ሌላ ክፋት ነው ያለው ተብሎአላ)፡፡ እኛም የያዝነውን እጅ አጥብቀን እንደጨበጥን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ ከነገ ወዲያም እንዲሁ አቅጣጫ ተቀይሮ በቀኝ በኩል እንጎተታለን፡፡ በእያንዳንዱ ቀን ስበት ላይ ከእግዚአብሔር ሳንለይ አያይዞ የሚያቆየን ብቸኛው ሥራችን ታዲያ፤ የያዝነውን እጅ ላለመልቀቅ ወስኖ እንደጨበጡ መቅረት ነው፡፡ (እጀ መንገዴን የምጽፈው፤ እግዚአብሔር በመንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ ሊያሳልፈን ያስፈለገበት አንዱ ጽንሰ አሳብ ይኸው ነው፡፡ መናፍስት በየቀኑ ስልት እየቀያየሩ በጎተቱን ቁጥር፤ የያዝነውን የመለኮት መዳፍ ላለመልቀቅ የምናደርገው ጥረት አዳዲስ ብርታቶችንና የፍልሚያ እውቀቶችን እያስተማረን ይሄዳል፡፡ እነዚህ ትምህርቶች ናቸው በጊዜ ውስጥ ከትንሹ ወደ ትልቁ እየተሰበሰቡ "ለውጥ" የሚሆኑት)

   ስዕሉን በውጊያ ቋንቋ ስናብራራው፤ መናፍስት በየዕለቱ አዳዲስም ሆነ ነባር የውጊያ ስልቶችን እየለዋወጡ በየቀኑ አንዳች ክፋት ሊያደርጉብን ጥርስ ነክሰው ይፋለማሉ (ባሕሪያቸው በየጊዜው የርኩሰት ጽልመቱን እያደመቀ እያመደቀ እንደሚሄድ ልብ ይሏል!)፡፡ በዚህ ውስጥ እኛ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የምንሆንበት (የምንጨባበጥበት) የመንፈሳዊ ልምምድ ኃይል የፍቅር ጉልበት ከሌለው፤ ከዛሬ ነገ በሚብስ መከራ በተፈተንን ቁጥር የጨበጥነውን እጅ እየለቀቅን፤ "ሰው አምላክ ሆነ"ን በመኖር ተዋሕዶአችን መካከል ላይ ነፍስ እየገባ፤ ክርስቶስን ለመምሰል የምንከተለው ጎዳና ዕንቅፋት የበዛበት ረጅም እየመሰለ፤ የእምነት ኑሮ ራሱን የቻለ አሰልቺና የጣር ሥራ እየሆነ፤ ይሄድ .. ይሄድና በመድረሻው ላይ ተሸንፈን ቁጭ እንላለን፡፡ አሁን ከዛ አስከትሎ የዓለሙ ገዢ "በእናንተ ላይ አንዳች አለኝ"ን በስኬት ይዘምራል፡፡

(የተሰመሩባቸውን በማስተዋል አንብቧቸው በነገራችን፥ መናፍስት አብረው ሲያነቡ የትምህርቱን ሙሉ አሳብ በሚገባ ስለሚረዱ፤ በጣም አንኳር የሆኑ መረጃዎችን ካለማጤን እንድናልፋቸው አእምሮን ያስቸኩላሉ አሊያም ይጋርዳሉ፡፡ ስለዚህ ነው አስፈላጊ ቃላት ላይ በማስመር ይህ ተንኮላቸው እንዳይሳካላቸው የሚጣረው)

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን...
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
1.3K views18:04
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-06-02 21:03:40    ክርስቶሳዊነት በአውሬው አስተዳደር ውስጥ ርስት የለውም፡፡ (ልብ ብላችሁ እዩ) መልካም ስብዕና ይነገድበታል እንጂ አይወደድም፡፡ ይመከራል እንጂ አይኖርም (ኖ ጠብቆ ይነበብ)፡፡ ጥሩ ነው ይባላል እንጂ አይመረጥም፡፡ አፍቃሪ ሰው፣ ለጋሽ ሰው፣ ሩኅሩኅ ሰው፣ የዋህ ሰው፣ ቀና ሰው፣ ታዣዥ ሰው፣ ድሃ ሰው፣ ሐቀኛ ሰው በሁሉም መስክ ላይ አባራሪዎች አሉበት፡፡ "በመላ ክፋት" የተያዘቺው ምድር ለክፉ እንጂ…
888 views18:03
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-05-30 23:10:15    ክርስቶሳዊነት በአውሬው አስተዳደር ውስጥ ርስት የለውም፡፡ (ልብ ብላችሁ እዩ) መልካም ስብዕና ይነገድበታል እንጂ አይወደድም፡፡ ይመከራል እንጂ አይኖርም (ኖ ጠብቆ ይነበብ)፡፡ ጥሩ ነው ይባላል እንጂ አይመረጥም፡፡ አፍቃሪ ሰው፣ ለጋሽ ሰው፣ ሩኅሩኅ ሰው፣ የዋህ ሰው፣ ቀና ሰው፣ ታዣዥ ሰው፣ ድሃ ሰው፣ ሐቀኛ ሰው በሁሉም መስክ ላይ አባራሪዎች አሉበት፡፡ "በመላ ክፋት" የተያዘቺው ምድር ለክፉ እንጂ ለደግ ስብዕና ኮታ አላዘጋጀችም፡፡ አስተማሪያችን እንቅጩን ስለነገረን ግን አይገርመንም "በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ" (የዮሐንስ ወንጌል 16፥33)

   ክርስቲያንነት መከራን በመቀበል ማኅተም የተዘጋ የሕይወት መጽሐፍ ከሆነ፤ በመከራ የመጽናኛ፣ መከራን የመቋቋሚያ፣ የመከራን ሚስጢር የመማሪያ፣ ከመከራ የመውጫ መንገድ ደግሞ በአንጻሩ ይኖር ዘንድ ግድ ነው፡፡ ("ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል" (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፥13)) ይሄ መንገድ እንደ መከራው አይነትና ይዘት አቅጣጫው ቢለያይም መነሻ መሠረቱ የሚነሣው ግን ከፍቅር ነው፡፡

ሐዋሪያው፦ "በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።" (ወደ ሮሜ ሰዎች 8፥37-39)

   እግዚአብሔርን ከልብ በመውደድ ፍቅር ውስጥ በዓለም ሳለን የምናያቸው መከራዎች ሁሉ ቀድመው የተሸነፉ ናቸው፡፡ ይሄንን ገልብጠን ብናነበው፤ መለኮታዊ ፍቅር ከማንነቱ ላይ የማይፈልቅለት ሰው በመከራዎች ሁሉ የተሸነፈ ነው፡፡

   ጌታ "ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች" ሲል እንደተናገረው በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ የመከራ ጽልመቶች ፈረቃቸውን እየጠበቁ መጥቆራቸው አይቀሬ ነው፡፡ (የዮሐንስ ወንጌል 9፥4) በዛ ዙሪያ ገባው በማይታይበት ድቅድቅ ጨለማ ላይ ሳለን፤ የሚወጉ የመሬት እሾህች ቢያደሙንም፣ ወለል የመሰሉ ጉድጓዶች ወደታች ቢጥሉንም፣ ዕንቅፋቶች በየርቀቱ ተቀምጠው ቢነድሉንም፣ መቆማቸው ከማይታይ ግንዶች ጋር ብንጋጭም፤ እየዳበስንም ቢሆን መራመዳችንን የምንቀጥለው ነፍስ ውስጥ በምትበራ የፍቅር ፋኖስ ስንመራ ነው፡፡

   ማንም በማይሠራባት የቀን ስብራት፤ ውስጣችንን ጠግና የምታሠራን ፍቅር ናት፡፡ መከራውን እንደማናሸንፍ እየተሰማን እንኳ ለማሸነፍ ተስፋ የምንቀጥለው በፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ያለበት ልብ በሌሊትም ሲያይ፤ ፍቅር አልባው ደግሞ የቀን ፀሐይን እየጠበቀ ይወጣል፡፡

   ክርስቲያናዊ አኗኗር የመከራ መጋዘን እንደሆነ ተነጋግረናል፡፡ በእያንዳንዱ መንፈሳዊ ሥራ ላይ ዲያቢሎስ የመከራ ክፍልን ከጀርባ አዘጋጅቶ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም መጸለይ መከራ ነው፣ መስገድ መከራ ነው፣ ንስሐ መግባት መከራ ነው፣ መቁረብ መከራ ነው፣ መማር መከራ ነው፣ መስጠት መከራ ነው፣ መታዘዝ መከራ ነው፣ ማክበር መከራ ነው፣ የዋህ መሆን መከራ ነው፣ ሐቅን መናገር መከራ ነው፣ ሐሜትን መቃወም መከራ ነው፣ ወዘተ... (ሰማያዊ ዕሴቶች በሙሉ እንዳይገለጡ የሚታገላቸው ሌሊት አለባቸው)

   ክፉው መንፈስ ከእግዚአብሔር የሆኑትን የነፍስ ጎዳናዎች በመከተል ላይ መከራን መቀበል ገሐድነት ያለው ዋጋ እንደማይገኝበት በማሳየት፤ ለመንፈሳዊ ምግባሮች መሥዋዕትነት መክፈል ብክነት እንደሆነ በዓለም ዜጎች አመለካከት ውስጥ አሰልጥኖ አምላካዊ ፍቅርን አጥፍቷል፡፡ ይሄንን ቃል በተጨባጩ የዘመናችን መስክ ሥጋ ለብሶ በአንድ ቅርጽ ብቻ ስናየው፤ ትውልዳችን ከአስተዳደጉ ጀምሮ ሃይማኖታዊ ክብደትን የመሸከም ጫንቃው እንዳይጠነክር ቤተሰብ፣ ማሕበረሰብና ትምህር ቤት ስለ ቅዱሳን፣ ስለ ጻድቃንና ስለ ሰማእታት ታሪክና ክብር አላሰተማሩትም፡፡ ልጆች የተጋድሎ ምሳሌ እንዲያደርጓቸው በአርአያነት የሚቀረጹላቸው ታላላቆች መንፈሳዊ ገድልና ሥነ ሕይወት ያላቸው አይደሉም፡፡ ስለዚህ መከራን የመታገል ኃላፊነት ግድ ሲሆን፤ ታዳጊዎች መቸገር ያለባቸው ከሰማይ ዝቅ ላሉ የእንጀራ ስኬቶች እንጂ በሳይንስና በገንዘብ የማይደረስበት እምነት ላይ አቅምና ጊዜ እንዳያባክኑ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ እንደ ውኃ ሲጠጡት በከረመው ምድራዊ ርዕዮት ይሞላሉ፡፡ (መሬታዊ ተክለ ቁመና ደግሞ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ያለች "ማንም የማይሠራባት ጨለማ" ላይ ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን የፍቅር ኃይል፤ ሥጋዊ ጉድለቶችን የማሟያ የቁስ ፍላጎት አድርጎ ይቀይረዋል፡፡)

   ፍቅር ከሌለን ረቂቅ ጦርነቶችን የምንዋጋባቸው የእምነት ጦር ዕቃዎችን በልበ ሙሉነት አንታጠቅም፡፡ የመከራ ዶፍ በዘነበ ጊዜ የምንሸሸግበት ዋሻ የለንም፡፡ ከፈተና ገጽ ጀርባ ያለውን ትምህርት የምናስተውልበትን እርጋታ አንታደልም፡፡ ከመጸለይ ንጋት በፊት፣ ከመስገድ ጸዳል አስቀድሞ፣ ንስሐ ገብቶ ከመቁረብ ብርሃን መጀመሪያ የሚኖረውን አላሠራ የሚል ዲያቢሎሳዊ ለሊት ለማሳለፍ የምንችልበትን ጽናት አናገኝም፡፡ (እግዚአብሔርን ያላፈቀረ ሰውነት አንትኩኝ ባይ ሆደ ባሻ ነው፡፡ ራሱን በተኮሰው፣ ዓይኑን ባቃጠለው፣ ሆዱን በቆረጠው፣ እግሩን ባዳለጠው፣ ሥራው በደከመው፣ ትምህርት በከበደው፣ ምቾቱ በራቀው፣ ሌሊቶች በከበቡት ቁጥር እንዳማረረ፣ እንደተበሳጨ፤ እንዳሳበበ፣ እንደሸሸ፣ እንደተልፈሰፈሰ፣ ለምን በኔ ብቻ እንዳለ ይኖራል፡፡)

   "በወደደን በእርሱ" ብሎ የሚነሣው የሮሜው መልእክት ዓ.ነገር መዝጊያ "እንበልጣለን" ነው የሚለው፡፡ ቁመታቸው ከረዘመ፣ ግዝፈታቸው ከተለቀ፣ ጡንቻቸው ከጠነከረ፣ ርስታቸው ከሰፋ መከራዎች ሁሉ የምንበልጠው በፍቅር በኩል ነው፡፡ እንበልጣለን ከሚለው ቃል ወዲያ መደምደሚያው አራት ነጥብ (::) ነው የሚገኘው፡፡ ይሄ ደግሞ "በወደደን" ብሎ በጀመረ ድንቅ ፍቅር ባለው ሃይማኖታዊ መንገድ ላይ የመከራዎች ሁሉ መጨረሻቸው መሸነፍ (መበለጥ) ነው ማለታችንን እርግጠኛ ያደረግልናል፡፡

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን...
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
843 views20:10
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-05-30 23:09:52 1• ፍቅር   1.2• ፍቅር ካለ ምን አለ? ክፍል - ፫ ✞ አንድ ሰው ሕዝብ ነው፥ ሕዝብም አንድ ሰው ነው ✞ "መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ። የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና…
658 views20:09
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-05-27 12:55:14   ደግ መሆን ሁለት መሥፈርት አለው፡፡ አንደኛ ደግ ነገር ማድረግ፥ ሁለተኛ ደግ ያልሆነውን አለማድረግ የሚባሉ ሁለት መሥፈርቶች አሉ፡፡ ደግ ነገር የሚያደርግ ሰው ክፉውንም የሚያደርግ ከሆነ ደግ አይባልም፡፡ ክፉውንም ደጉንም የማያደርግ ሰው ደግነትን አልኖራትም፡፡ መብትም እንደዚሁ ሁለት መሥፈርት አለው፡፡ አንደኛ የራስን ፈቃድ መፈጸም፥ ሁለተኛ የሌሎችን ፈቃድ አለመንካት፡፡ (ለምሳሌ በዲሞክራሲው ርዕዯት ሁሉም ሰው ያለመታሰር መብት አለው፤ የሌላው ሰው ያለመታሰር መብት ከጣሰ ግን መብቱ ይገፈፋል)

   በዚህም መሠረት እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ሁለት መሥፈርቶችን አሟልቶ መያዝ ይኖርበታል፡፡ አንደኛ ራሱን ከአባቱ ፈቃድ አለመለየት፥ ሁለተኛ ወንድም እህቶቹን ሁሉ ከአባቱ አለመለየት፤ እንዳይለዩ መጠበቅ፤ ከወጡም መመለስ፡፡ እነዚህን ሁለቱንም ኩታ ገጠም አድርጎ ማንነቱን በማይገነባ ቤተመቅደስ ላይ እግዚአብሔር አያድርበትም ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ "የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።" (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 3፥10)

    ሰው ጽድቅን ሁሉ ፈጽሞ አንድ ሰውን እንኳ ባይወድ (ቢያማ፣ ቢሰድብ፣ ቢገፋ፣ ቢጥል፣ ቢያጎሳቁል፣ ቢቀማ፣ ቢፈርድ፣ ቢከለክል፣ ቢነጥቅ፣...) ሰውየው ከክፉው መንፈስ ጋር ነው፡፡ ጽድቅን በሚችለው እያደረገ ሁሉንም ሰው ከአንጀቱ የወደደ እርሱ ከተቀደሰው መንፈስ ነው፡፡ (ዐሥርቱ ትእዛዛት ስለ እግዚአብሔርና ስለ ሰው ለምን እንደሆኑ ልብ ይሏል! "እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።" (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፥21))

   አጠገብ ያለን ቤተሰብ አሊያ ወዳጅ መውደድ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለቺውን የባሕሪይ ፍቅር አትወክልም፡፡ እንስሳትም እንዲሁ ያደርጋሉና፡፡ ሰው ግን የተፈጥሮ ገጽታው ፍቅር ነውና፤ አባቶችን ሁሉ እንደ አባቱ፣ እናቶችን ሁሉ እንደ እናቱ፣ ወንድሞችን ሁሉ እንደ ወንድሙ፣ እህቶችን ሁሉ እንደ እህቱ ሲወድ በእርግጥም እርሱ የአምላክ ምሳሌ ስለመሆኑ ያስረግጣል፡፡ (ክርስቲያን አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን የመሰለበት ልጅነቱ የሚተረጎመው ሌሎችን በመወደዱ ፍቅር ውስጥ ነው፡፡ አብ በራሱ አካል ለራሱ አሳቢ ሆኖ ሳለ፥ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስም አሳባቸው እንደሆነ፤ ክርስቲያንም ለራሱና ለወገኑ ሁሉ ያስባል፡፡ ወልድ በራሱ አካል ለራሱ ተናጋሪ ሆኖ ሳለ፥ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስም ቃላቸው እንደሆነ፤ ክርስቲያንም ለራሱና ለወገኑ ሁሉ ድምፅ ይሆናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በራሱ አካል ለራሱ እስትንፋስ ሆኖ ሳለ፥ ለአብና ለወልድም ሕይወታቸው እንደሆነ፤ ክርስቲያንም ለራሱና ለወገን ሁሉ ሕይወት ይኖራል፡፡)

  እግዚአብሔር ሕዝብን ሁሉ እንደ ግለሰብ፥ ግለሰብን ሁሉ እንደ ሕዝብ የወደደበት ፍጹም ፍቅሩ በልባችን ማኅደር ሳይታተም፤ መርጠን የምንወድና መርጠን የምንጠላ ከሆን የሃይማኖት መሠረታዊ ሕጎች ከውስጣችን ተንደውብናል ማለት ነው፡፡

    ሰው ሰውን [ሁሉ] ሳይወድ እልፍ ቢሰግድ፣ ሙሉ ቀን ቢጸልይ፣ አጥንቱ እስኪገለጥ ቢጦም፣ በዮርዳኖስ ባሕር ቢጠመቅ፣ ቅዱስ ቁርባንን ከሱራፌል እጅ ቢቀበል፣ ሚሊዮን ብሮችን ዐሥራት ቢያወጣ፣ ክፉ መናፍስትን ማሸነፍ ቢችል፣ መላእክት ቀርበው ቢያገለግሉት ምንም ዋጋ የለውም፡፡ (ቀዝቃዛ ውኃ ያጠጣ ሰው ግን ዋጋው አይጠፋበትም) "ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?" (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፥20)

   የልዑል አምላክ የመጨረሻው ብቸኛ ዓላማ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ ጥግ እንዲደርሱ ነው፡፡ (1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፥3-4) እንኪያስ ይህንን መለኮታዊ ፍቅር የሚጋራ ማንኛውም አማኝ በፈጣሪ ፊት ልዩ ቦታና ሞገስ ይሰጠዋል፡፡ ሰውን የሚያስብ ሰው እግዚአብሔር ያስበዋል፡፡ ሰውን ያከበረ ሰው እግዚአብሔር ያከብረዋል፡፡ ሰውን የሚጠብቅ ሰው እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፡፡ ሰውን የሚያስቀድም ሰው እግዚአብሔር ያስቀድመዋል፡፡ ሰውን ያሳረፈ ሰው እግዚአብሔር እረፍት ይሆነዋል፡፡ ሰውን የተንከባከበ ሰው እግዚአብሔር ይንከባከበዋል፡፡ ሰውን ያገዘ ሰው እግዚአብሔር ያግዘዋል፡፡ ሰውን ያበረታ ሰው እግዚአብሔር ያበረታዋል፡፡ (አባባል እንዳይመስላችሁ! ስታነቡት ሳይሆን ስትኖሩት ይታወቃችኋል)

   (አልገባንም እንጂ) የመዳን አጭር መንገድ ወገንን ማዳን ነው፡፡ የመፈወስ ቀላሉ ጉዞ ለሌላው ፈውስ መሆን ነው፡፡ የመደሰት ነጻው አቅጣጫ የሌሎች ደስታ መሆን ነው፡፡ ሰላም የማግኘት ቅርቡ በር ሰላምን ለሌሎች ማስገኘት ነው፡፡ ከሕመም የመጠበቅ ትልቁ ጸሎት ለታመሙት መጸለይ ነው፡፡

(ወደ ቅዱስ ቁርባን እየሄድን ፍቅርን መነሻችን ለምን እንዳደረግን አሁን ግልጽ ነው፡፡ ፍቅር በሌለው ሥጋና ደም ውስጥ የፍቅር ሥጋውና ደሙ አይወሐድም!)
ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን...
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
1.1K views09:55
ክፈት / አስተያየት ይስጡ