Get Mystery Box with random crypto!

   የሕይወት ጀርባችን ወደ እግዚአብሔር ሆኖ፤ ከአርያም መቅደስ ስለ ሰው ልጆች መዳን የሚለቀቀውን | በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪

   የሕይወት ጀርባችን ወደ እግዚአብሔር ሆኖ፤ ከአርያም መቅደስ ስለ ሰው ልጆች መዳን የሚለቀቀውን የቸርነት ብርሃን ማየት ስላቃተን፤ ታይቶ ሳይቆይ የሚጠፋውን የዓለምን ብርሃን ለመጨበጥ ስንል፥ መልሰን እናገኛቸው ብንል የማይቻል፥ ብዙ የዕድሜ ዓመታቶቻችንን አቃጥለናል፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን ፊታችንን ያዞርንለት ብርሃን የተረጋገጠ ዋስትና አስይዞ፤ የመኖር ሕልውናችንን ሊያሳርፈውና ሊያረጋጋው አልቻለም፡፡

   እረፍት የተነፈገና መረጋጋት ያጣ ስብእና ደግሞ ሰላም የለውም ውኃ ሲቀጥንም ሆነ ሲወፍር ይነጫነጫል፡፡ የሚፈልገውን አግኝቶም ሆነ አጥቶ ያኮርፋል፡፡ ከውስጣዊ አካሉ የሚደመጥ እፎይታ ተነፍጎ ዘወትር ይቅበዘበዛል፡፡ ከገንዘብ፣ ከውበት፣ ከእውቀት፣ ከሥልጣንና ከአቅም ውስጥ አደላድሎ የሚያስቀምጥ አንድ የሰላም ወንበር እየፈለገ ይኳትናል፡፡ ግን የለም አያገኝም፡፡

   ንስሐ ያልገባች ነፍስ፤ እነዛ በመጀመሪያ አዳም ጋር የተሰሙት ፍርሃት፣ ማጣት፣ ባዶነት፣ ብቸኝነት የተባሉ ስሜቶች ስለሚሰሟት፤ እነዚህን ለማፈን ሲባል በሥጋ ወከባ የሚምታታ ትንንቅ ውስጥ ትገባለች፡፡ ምንም አይነት ሥጋዊ ብልሃትና ሙከራ የነፍስን ክፍተት ይሞላ ዘንድ አይቻለውምና፤ ፍርሃቱ ወደ ጭንቀት፣ ማጣቱ ወደ ብስጭት፣ ባዶነቱ ወደ ተስፋ መቁረጥ፣ ብቸኝነቱ ወደ ጣዕም አልባ ሕይወት እየተሸጋገረ፤ አድራሻ ጠፍቶት እንደሚባትት መንገደኛ ወዲህም ወዲያም እየተራወጠች ትንከራተታለች፡፡

   ነፍስ በባሕሪይዋ የእግዚአብሔር አካል ናትና፤ የሰው ልጅ ስብእና ሲፈጠር ይሄድ ወደነበረበት፥ የእግዚአብሔር ፈቃድ ወደሆነው ከፍታ መርቀቅን ሁልጊዜ ትፈልገዋለች (የሞትን ነገር ውስጣችን የሚጠላብን ለዚህ ነው) ፡፡ ይህ ማለት ነፍስ ከስድስተኛው ቀን ወደ ሰባተኛው የእረፍት ቀን የመሻገር ስበት በረቂቅነቷ ውስጥ አለ፡፡ ከላይዋ ሆኖ ጀቡኖ የያዛት ሥጋ ግን ወደ መጣበት አፈር ለመመለስ ይፈጥናልና፤ ይሄ የሥጋና የነፍስ መስተቃርናዊ ሂደት የሚታረቀው፤ የሰው ልጅ ንስሐ በሚባል መንገድ ላይ መጓዝ ሲጀምር ብቻ ነው፡፡

   እንዲህም ከሆነ፤ ንስሐ ማለት ነፍስና ሥጋን በአንድ መንፈሳዊ ክር ሰፍቶ የሚያይዝ የምሕረት መርፌ ነው፡፡ በአካላችን ውስጥ የሚገኙ ሰማያዊና ምድራዊ ማንነቶችን አንድ ገጽ የሚሰጥ ልዩ መታወቂያ ነው፡፡ እርስ በእርስ የሚጣሉ ሁለት ባሕሪያትን የሚያስማማ መለኮታዊ ሸንጎ ነው፡፡

 {ዓለም}  ☜☜ሥጋ   ነፍስ☞☞ ️ {እግዚአብሔር}
 {ዓለም} ☞☞ሥጋ  ️[ንስሐ]  ነፍስ☞☞ {እግዚአብሔር}
                 
   ሞትና ትንሣኤ ስለሚባሉትም ጉዳዮች እዚህ ጋር ማንሣት እንችላለን፡፡ ሞት በመንፈሳዊ ፍቺው ሲተነተን በአጭሩ የሥጋና የነፍስ መለያየት ማለት ነው፡፡ ከላይኛው አንቀጽ ባወጋነው አሳብ ስንመለከተው፤ የነፍስና የሥጋ የተለያየ ጉዞ የመጨረሻ ውጤት እንበለው፡፡ ከአፈር የተገኘው ሥጋ ወደ "አፈር ትመለሳለህ" የሚልን ፈቃዱን የተከተለ ውሳኔ ስለሰማ፤ ወደ ተፈጠረበት ምድር ባሕሪይው እየተጎተተ .. እየጎተተ ይሄዳል፡፡ ይሄ መቼም የማይቀር ነው፡፡ ሥጋ የለበሰ ሰው ሁሉ ወደ ሞት ይጓዛል፡፡

   ሰውን የቱን ያህል መንፈሳዊ ብርታትና ጽናት ይኑረው ወደ ሞት የሚገሰግሱበት የሥጋ ባሕሪያት ራሳቸውን የቻሉ ጾር እየሆኑ ያስቸግሩታል፡፡ ፍጹም የሆነው መለኮት እንኳ ሥጋ በተዋሐደው ጊዜ "መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው" ሲል የሥጋን ታላቅ መገዳደር አስታውቆአል፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል 26፥41)

   በመጀመሪያው የማኅፀን ሥርዓት የሚወለደው ሥጋ ከፊቱ የሚጠብቀው ሞት ነው፡፡ ነፍስ የቱን ያህል ብትታገለውም የመፍረስን ሕያው ቃል በባሕሪዩ አንዴ ያደመጠው ሥጋ፤ በየዕለቱ ቀን በቆጠረ ቁጥር እየፈረሰ እየፈረሰ ይሄዳል፡፡ ታዲያ ምን ይሻላል?

   ማኅፀኒቱ መለወጥ አለባት፡፡ የመጀመሪያቱ ሔዋን ከእባቡ ጋር በፈቃድ ተስማምታ ከእርሷ የሚወለደው ዘሯን ሁሉ ወደ ሥጋ ፈቃድ አንከባላ አስገብታዋለች፡፡ ስለዚህ ሌላ የአወላለድ ሥርዓት ያስፈልጋል .. መንፈሳዊ ማኅፀን!

   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የሚያሳድደውን የአዳምን ባሕሪይ ገንዘብ አድርጎ በሥጋ የተወለደው ለዚህ ነው፡፡ ወደ ሞት እየገሰገሰ የሚሄደውን ሥጋ እስከ መጨረሻ ታግሦ ተከተለውና፤ ሥጋ በመስቀል ላይ "በቃ" ብሎ ሲጨርስ፤ መሞት የሌለበት መለኮት፥ የተዋሐደውን ሥጋ አዲስ ሥርዓት አሳየው፡፡ ከመቃብር አነሣው፡፡ ፈርሶ ከመቅረት ነጻ አወጣው፡፡

   ይህንን አዲስ የትንሣኤ ሥርዓት እኛ እንድናገኘው ደግሞ፤ ከጎኑ ደምና ውኃ ሆና ከወጣቺው አዲስቷ ሔዋን (ቤተክርስቲያን) ጋር ሰማያዊ ጋብቻ ፈጽሞ ከማይጠፋ ዘር ወለደን፡፡ አሁን ዳግም ከመንፈስና ከውኃ የሚወለድ ሥጋ፤ እንደ ቀዳሚው አዳም በሥጋ ማኅፀን ከመወለዱ የተነሣ ሞትን ቢቀምስም፤ ለሁለተኛ ጊዜ በተወለደበት ማንነቱ በኩል ግን ሞትን ድል አድርጎ ይነሣል፡፡ "አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር" ይሆናል፡፡ በትንሣኤ ነፍስና ሥጋ ስለማይለያዩ ሞት የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡

   እንኪያሳ ከዚህ ገለጻ አንጻር ደግሞ ንስሐ ማለት፤ ከሥጋ ፈቃድ የተወለደው ሥጋ ወደ ሞት እየገሰገሰ ከነፍስ ለመለያየት ሲቸኩል፤ ነፍስንም አራውጦ ይዟት እንዳይሞት (ኃጢአትን እንዳያትምባት) የሚከላከል ጠበቃ ነው፡፡ ሰው ንስሐ እየገባ ነው ማለት፤ በመሲሑ ድንቅ ሥራ አምኖ ዳግም የተወለደበት ሥርዓት እንዳይበላሽ እየጠበቀ ነው ማለት ነው፡፡

   "የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና"፤ ከፈጸመው ኃጢአት ለመላቀቅ ሲል ንስሐ የማይገባ ሰው፤ ዳግም ቢወለድም እንኳ ከፈቃደ እግዚአብሔር የመለየቱ መግፍኤ ከትንሣኤው በኋላም እንዲሞት ያደርገዋል፡፡ (ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥23) ስለዚህ ንስሐ የማይገባ ሰው "ሁለት ሞት" ይሞታል ማለት ነው፡፡ አንደኛ የሥጋ ባሕሪይን በመያዙ የሥጋን ሞት ይሞታል፤ ሁለተኛ ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን ባለመፍቀዱ ምርጫው ተከብሮለት ቀደም ሲል አምላክን አልፈልግም ወዳለው ወደ ዲያቢሎስ ማደሪያ እንዲሄድ ይሆናል፡፡ ይሄ ደግሞ ለነፍስ ሞት ነው፡፡

   ነገሩስ ያለ ንስሐ የሚመላለስ ምዕመን፤ ሦስት ሞት ነው የሚሞተው፡፡ ንስሐ ማለት ፊትን ወደ እግዚአብሔር ጀርባን ወደ ዓለም አድርጎ የመጓዝ ሂደት ነው ብለን ጀምረናልና፤ ከንስሐ ሕይወት ተለይቶ የሚኖር ሰው በተገላቢጦሽ ፊቱን የሚያዞረው በቁም ወደ ምትገለዋ ዓለም ነው፡፡ በዓለም ውስጥ የመኖር ሕግ መንፈሳዊ ጠባያትን ይገላል፡፡ 'ለሥራው ዕድገት ስትል ዋሽ፣ ለትምህርት ስኬት ነውና ኮርጅ፣ ለገንዘቡ መጠራቀም ጉቦ ውሰድ፣ ብዙ ጥሪት እንዲኖር ለቸገረው አትስጥ፣ ደስታን እንዳታጣ የሰውን ችግር አትስማ፣ ካንተ ውጪ ማንም የለህምና ራስህን ብቻ ውደድ፣ ዘመኑ የፉክክር ነውና የተመኘኸውን ለመጨበጥ ሌላውን ገፍተህ እለፍ፣ ..' እያለ፤ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የተባሉትን ቅዱስ ጠባያት የማንነትህ አካል እንዳታደርግ በዓለም ውስጥ ጩኸቱ ከአድማስ ጥግ እስከ አድማስ ጥግ የሚሰማለት ክፉው መንፈስ፤ በፖሊሲ፣ በመርህ፣ በኑሮ ውድነት፣ በዘመን ለውጥ፣ በእንጀራ ጉዳይ፣ በመኖር ጥያቄ ጀርባ እየተከለለ ሰው የመሆንህን ንጹሕ ጠባያት እንዳትገለጽ በስልት አፍኖ፤ በጠባብ የርኩሰት አስፓልት ላይ ይመራሃል፡፡

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን . . .
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek