2022-07-13 12:10:02
ከሁለት ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ለምግብ እጥረት ተዳርጓል
ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደጋጋሚ ይከሰታል፤ ለአጭር ወይም ለረጅም ዓመታት ሊቆይም ይችላል፤ የሰው ልጆችን ህይወት ከሚቀጥፉ አደጋዎች ውስጥ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፤ ድርቅ::
በግንቦት 2022 አ.ኤ.አ ዓለም አቀፍ የድርቅ ቀን ሲከበር “ድርቅ በቁጥሮች ሲገለፅ” በሚል ርዕስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀረበ ጥናታዊ ሪፖርት እንዳመላከተዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምድር ላይ ከሚደርሱ አደጋዎች መካከል 15 በመቶዉ በድርቅ ምክንያት የሚመጣ ነው::
ድርቅ እ.ኤ.አ ከ1970 እስከ 2019 ድረስ በተፈጥሮ አደጋ ከሞቱ ሰዎች ውስጥ የ45 በመቶውን ድርሻ ይይዛል:: ድርቅ በምጣኔ ሀብት ደረጃም ከፍተኛ ኪሳራ ያደርሳል፤ እ.ኤ.አ ከ1998 እስከ 2017 ድረስ ብቻ እንኳን ዓለም 124 ቢሊዩን ዶላር እንድታጣ ምክንያት ሆኗል::
ድርቅ በሚያስከትለው ጣጣ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ሁለት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ሕዝብ ለምግብ እጥረት ተጓልጧል፤ 160 ሚሊዬን ህፃናትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለሚመጣ ችግር ተጋላጭ መሆናቸውንም ከሪሊፍ ዌብ ዶት ኢንተርናሽናል ድረ ገጵ ያኘነው መረጃ ያመላክታል::
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ የድርቅ እውነታዎች (1900-2022) ድረቅ ካለፈዉ ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በ10 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፤ በመቶ ቢሊዮኖች የሚገመት ሀብትም እንዲወድምም ምክንያት ሆኗል::
እጅግ ከባድ ድርቅ በተደጋጋሚ ካጠቃቸው አህጉራት መካከል አፍሪካ ቀዳሚ ናት፤ ባለፉት 100 አመታት ከ300 መቶ በላይ የድርቅ ክስተቶች በአህጉሪቱ አጋጥሟል:: ይህም በዓለም ከተከሰቱት ድርቆች 44 በመቶውን የሚይዝ ነው::
ባለፈው ምዕተ ዓመት በአውሮፖ 45 ከፍተኛ የተባሉ የድርቅ ክስተቶች ተመዝግበዋል፤ እነዚህ ክስተቶችም በሚሊዬን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት እና ለተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች ዳርገዋል:: በምጣኔ ሀብት ደረጃም 27 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ኪሳራ አድርሷል:: በአሁኑ ወቅትም በአውሮፖ በአመት በአማካይ 15 በመቶዉ የአህጉራቱ መሬት እና 17 በመቶዉ ሕዝብ በድርቅ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሳባቸው ይገኛሉ::
በአሜሪካም እ.ኤ.አ ከ1980 ወዲህ በድርቅ ምክንያት ከፍተኛ የምርት መቀነስ ማለትም 249 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ኪሳራ ደርሷል:: ድርቅ በእስያም ከፍተኛውን ሰብዓዊ ኪሳራ ባለፉት አመታት ማድረሱንም የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያመላክታል::
ድርቅና ምስራቅ አፍሪካ
አፍሪካ ከሌሎች አህጉሮች በተለየ መልኩ በድርቅ በተደጋጋሚ ትጠቃላች፤ ቀደም ብለን እንደገለፅነው እ.ኤ.አ ከ1900 እስከ 2022 ድረስ በአህጉሪቱ ከ300 የሚልቁ የድርቅ ክስተቶች ታይተዋል:: እ.ኤ.አ ከ2000 እስከ 2019 ድረስ ደግሞ 134 ክስተቶች ተመዝግበዋል፤ ከዚህ ውስጥ 70 ያህሉ ማለትም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በምስራቅ አፍሪካ የተከሰቱ ናቸው::
ምስራቅ አፍሪካ በተደጋጋሚ ለድርቅ የሚጋለጥ የአፍሪካ ቀጣና ነው:: በዚህም በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት፣ ለስደትና ለተለያዩ ማሕበራዊ ቀውሶች ተዳርገዋል:: በርካታ የቀንድና የጋማ ከብቶች ሞተዋል እንዲሁም ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዎች ደርሰዋል:: ባለፉት ሁለት ዓመታት የያዝነውን ዓመት ጨምሮም ከፍተኛ ድርቅ ተከስቶ ሌላ ራስ ምታት ሆኗል::
የምስራቅ አፍሪካን በተደጋጋሚ በድርቅ መጎዳት ለማሳየት በቅርቡ ዶቼ በሌ ያወጣዉን መረጃ መመልከት በቂ ነዉ:: የተመድ የሰብዓዊ እርዳታዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን በእንግሊዘኛ ምህጻሩ ኦቻ እንዳለው እ.ኤ.አ በ2022 መጀመሪያ ላይ ባወጣው የሰብዓዊ ቀውስ ዘገባ የጠቀሰው የሶማሌ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ፣ በክልሉ በሚገኙት ሁለት ዞኖች ይመረታል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የሰብል መጠን በእጅጉ ቀንሷል። በኦሮምያ ክልል ቦረና ዞን ደግሞ በርካታ የቀንድ ከብቶች ሞተዋል።
ደቡብና ምስራቅ ኢትዮጵያን በመታው ድርቅ ሰበብ ቢያንስ 6 ሚሊዮን ሰዎች በዚህ ዓመት የህይወት አድን እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። የሶማሌ ክልልን እና ምሥራቅና ደቡብ ኦሮምያን ይበልጥ ባጠቃው በዚህ ድርቅ አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች አርብቶ አደሮች ናቸው። በነዚህ አካባቢዎች በሶስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ አልጣለም። ኦቻ እ.ኤ.አ በ2022 መጀመሪያ ላይ ባቀረበው የሰብዓዊ ቀውስ ዘገባ የጠቀሰው የሶማሌ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ፣ በክልሉ በሚገኙት ፋፋን እና ሲቲ በተባሉት ዞኖች ይመረታል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የሰብል መጠን በእጅጉ ቀንሷል። እንደ ቢሮው ከተጠበቀው የማሽላና የበቀሎ ምርት 70 በመቶው አልያዘም፤ በተመሳሳይ ሁኔታ የስንዴ ምርትም በ30 በመቶ ቀንሷል። በደቡብ ኦሮምያም በአማካይ 70 በመቶ ሰብል መጥፋቱን 267 ሺህ የቀንድ ከብቶች በመኖና በውኃ እጥረት መሞታቸውን አስታውቋል። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የቀንድ ከብቶች በመኖና ውኃ እንዲሁም በክትባት እጦት ህይወታቸው አደጋ ላይ ነው። በተለይ በኦሮምያ ቦርና ዞን ችግሩ የከፋ ነው።የቦረናን ሁኔታ የኦሮምያ ክልል ግብርና ቢሮ ና የእንሰሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቃሲም ጉዮ ሰሞኑን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
በድርቁ ምክንያት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ኦቻ በዘገባው አስፍሯል። በሶማሌ ክልል የሚገኙ 2.3 ሚሊዮን በደቡብ ኦሮምያ ደግሞ 870 ሺህ ሰዎች በውኃ ችግር እየተሰቃዩ ነው። ዶክተር ቃሲምም ድርቁ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እያስከተለ መሆኑን በትምህርትም ላይ ተጽእኖ ማድረጉን ተናግረዋል። የውኃና የእንሰሳት መኖ ችግርም ከአቅም በላይ መሆኑን አስረድተዋል።
በኦቻ ዘገባ መሠረት በኢትዮጵያ ድርቅ ባጠቃቸው አካባቢዎች የሚገኙ ከ6.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጎርጎሮሳዊው አዲስ ዓመት የምግብ እርዳታ ይሻሉ።
እንደ ኢትዮጵያም ባይሆን በኬንያም ድርቅ ተመሳሳይ ችግር አስከትሏል። ሰሜን ኬንያ ውስጥ በሚገኘው ማርሳቢት በተባለው ወረዳ የቀንድ ከብቶች እየሞቱ ነው። ፊሊፕ ኤዎቶን ቬልት ሁንገር ሂልፈ የተባለው የእርዳታ ድርጅት ባልደረባ ናቸው። በማርሳቢት ድርቅ ያስከተለውን ጉዳት ለዶቼቬለ ገልጸዋል።
“በየመንደሮቹ የሞቱ እንሰሳት ይታያሉ። በህይወት የሚገኙት ላሞችና ግመሎችን ጨምሮ አንዳንድ እንሰሳት መራመድ አይችሉም። ኅይለኛው ሙቀት ይገድላቸዋል። የሚሞቱትም በቂ ውኃ ስለሌለን ነው። ህብረተሰቡ እነዚህን እንሰሳት ውኃ ለማምጣት ይጠቀምባቸዋል። ውኃ ለማምጣት ረዥም ርቀት መጓዝ አለባቸው። አቅም ስለሌላቸው ግን አብዛኛዎቹ ይህን ማድረግ አይችሉም።”
በማርሳቢት ስጋት የሆነው የአሁኑ ጉዳት ብቻ አይደለም፤ የወደፊቱም እንጂ። በአሁኑ ጊዜ በወረዳዋ የሚገኙ 183 ሺህ ሰዎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ይሁንና ዝናብ ካልዘነበ የእርዳታ ፈላጊዎቹ ቁጥር ከፍ ማለቱ እንደማይቀር ኤዎተን ይሰጋሉ። በአካባቢዉ በሶስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ አልጣለም። እስካሁን በሚታወቀው የአካባቢው የድርቅ ታሪክ ይህን ያህል ጊዜ ዝናብ ሳይጥል የቀረበት ጊዜ እንደሌለ ፊሊፕ ኤዎቶን ገልጸዋል። በኬንያ አንዳንድ ግዛቶች ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑ ግድቦችና የውኃ ማቆሪያዎች ካለፈው ታኅሳስ አንስቶ ደርቀዋል።
594 views09:10