2022-08-26 06:09:41
አክሳሪዎቹ ጅምር ህንጻዎች ምን ይሁኑ?
ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም
ሕንጻዎች ከተማ ወካይ ናቸው:: ከተሞች የሚይዟቸው ህንጻዎች የወደፊት መዳረሻዎቻቸውን የሚጠቁሙ ናቸው:: በተለይም ጎብኝዎች መዳረሻቸውን ሲያስቡ መነሻ የሚያደርጉት ከተሞች ያሏቸውን ህንጻዎች ታሳቢ አድርገው ነው:: ይሁን እንጂ በተለያዩ ከተሞች የሚስተዋለው የግንባታ መጓተት ገጽታን በማደብዘዝ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን በመገደብ እና የተቀዛቀዘ ኢኮኖሚን በመፍጠር የሚያስከትሉት አሉታዊ ጫና ከፍተኛ እንደሚሆን ብዙኃኑን የሚያስማማ ሀቅ ነው::
ለአብነት በባሕር ዳር ከተማ በኖርኩባቸው አራት ዓመታት ውስጥ ግንባታቸው ያልተጨረሱ ግን ሙሉ ለሙሉ በሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ ያልሆኑ ህንጻዎችን ተመልክቻለሁ:: ሕንጻዎች የብዙኃኑ የቡና ሰዓት መነጋገሪያ ናቸው::
የመነጋገሪያው ዋናው ጉዳይ ደግሞ የባለቤትነት ጥያቄ ሲሆን ተጨባጭ መልስ ግን የሚሰጥባቸው አይገኝም:: አንዳንዶች ሕንጻዎቹ የቆሙበት ቦታ የቀድሞ ባለቤት በአነስተኛ ካሳ እንዲነሳ ተደርጎ ዛሬ ላይ በከፋ ችግር ውስጥ ሊሆን ይችላል የሚል ሐሳብም ያነሳሉ::
አቶ ክንዱ ወለላው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው:: በከተማዋ በርካታ በጅምር የቀሩ ከ15 እና 20 ዓመታትን የተሻገሩ ህንጻዎችን ተመልክተዋል:: የግንባታ ባለቤቶች እነማን ናቸው? ክትትል የሚደረግባቸውስ በእነማን ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ እንዳጡ ተናግረዋል::
‘ባለሀብቶች’ ቦታ የማግኘት ሽሚያ ውስጥ ገብተዋል:: ባለሀብቶች ለከተማዋ በሚያስፈልጉ ዘርፎች ለመሠማራት ፍላጎት ሲያቀርቡ የባለሀብቶችን የኋላ ታሪክ ማወቅ ተገቢ እንደሆነ አቶ ክንዱ ጠቁመዋል::
በተለይም የእነዚህ ባለሀብቶች የግንባታ ማጠናቀቅ ተሞክሮን መቃኘት፣ ሌላ ግንባታ ኖሯቸው ያንም አጠናቀው ወደ ሥራ በማስገባት የታለመለትን ግብ ማሳካታቸውን ማረጋገጥ ከተቻለ የግንባታ መጓተትን ለማስቀረት እንደሚያስችል ገልጸዋል::
በሌላ በኩል ደግሞ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚሠማሩት ከፍተኛ ብድር ከመንግሥት በመውሰድ ነው:: ይህ ገንዘብ ቦታ ከተወሰደበት ከተማ ውጭ ለሌላ ዓላማ ውሎ በሚያመጣው ትርፍ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ታሳቢ እየተደረገ ሊሆን እንደሚችልም አቶ ክንዱ ያምናሉ::በመሆኑም የተወሰደው ብድር የታለመለትን ግብ በማሳካት በሥራ ዕድል ፈጠራ ኢኮኖሚን ማሳደግ ካልቻለ ትርፉ ኪሳራ ነው የሚል ሐሳብም አላቸው::
የግንባታዎች መጓተትም ከግንባታ እስከ ማምረት ባሉት ሂደቶች መፍጠር የነበረበትን የሥራ ዕድል በማሳጣት ለሥርዓት አልበኝነት መንገስ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ይረዳሉ:: ለይስሙላ ግንባታ ጀምሮ ብድር መውሰድ እና አለማጠናቀቅ ተገቢ ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል በመገንዘብ ጠንካራ ክትትል እና ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል::
በባሕር ዳር ከተማ ለረጅም ዓመታት በጅምር ላይ የሚገኙ ህንጻዎች አለመጠናቀቃቸው ጎብኝዎች የሚያድሩበት፣ የሚተኙበት…አማራጭ የመዝናኛና የማረፊያ ቦታ በማሳጣት ፍሰቱን በመገደብ፣ የተረጋጋ የገበያ ሥርዓት ለመፍጠር እክል በመሆን፣ የሥራ ተነሳሽነትን በመንቀፍ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን በማቀዝቀዝ የሚያሳድሩት ጫና ከፍተኛ እንደሚሆን የምጣኔ ሐብት ምሁሩ ውዱ ወርቁ ተናግረዋል::
እንደ ምሁሩ ገለጻ የሕንጻዎች በወቅቱ አለመጠናቀቅ ተገንብተው አገልግሎት ላይ የሚገኙ ድርጅቶች በውድ እንዲከራዩ በማድረግ ነዋሪው ለኑሮ ውድነት እንዲጋለጥ ያደርጋሉ:: ተከራይተው የሚያከራዩት ደግሞ ትርፋማነትን ታሳቢ አድርገው የሚሠሩ በመሆናቸው የሚሰጡትን አገልግሎት በማናር ብዙኃኑ ለከፋ የኑሮ ጫና እንዲዳረግ ምክንያት ይሆናሉ::
እንደ ምሁሩ ገለጻ የሰው ልጅ ትልቅ ትርፍ ማግኘትን ታሳቢ አድርጎ ወደ ሥራ ይገባል:: ወደ ግንባታ የመግቢያ እና የማጠናቀቂያ ጊዜን ታሳቢ አድርጎ መፈጸም ካልቻለ በመመሪያው መሠረት ተጠያቂ ማድረግ ይገባል። ካልሆነ ግን ቦታዎች እንዲሸጡ እና እንዲለወጡ ዕድል ይፈጥራል::
ባዶ ቦታዎች በህገወጥ መንገድ/በአየር ላይ /በመሸጣቸው እና ገንዘቡም በተመሳሳይ በአየር ላይ በመረጨቱ በገበያው ላይ ያልተገባ የዋጋ ንረት እንዲከሰት ምክንያት እንደሆነም አቶ ውዱ ጠቁመዋል:: እነዚህ አይነት አሠራሮች በየጊዜው እየጨመረ ላለው የቤት ኪራይ ምላሽ መስጠት እንዳይቻል እና በትንሽ ካፒታል ወደ ሥራ መግባትንም የሚገድቡ እንደሚሆኑ ገልጸዋል::
“ጅምር ህንጻዎችን በወቅቱ ማጠናቀቅ ቢቻል ኖሮ ዛሬ ላይ ተጨማሪ ሥራ መሥራት የሚያስችል ሀብት ለብክነት አይዳረግም ነበር” ይላሉ::
አቶ ውዱ አክለው እንደተናገሩት የቤት ኪራይ ዋጋ የግንባታ ወጪን መሠረት ያደርጋል::
በመጓተት ዛሬ ላይ የደረሱ ሕንጻዎች በወቅቱ የግንባታ ግብዓት ወጪ ቢጠናቀቁ ኖሮ የቤት ኪራይ የማኅበረሰቡን ገቢ ሊገዳደር ባልቻለ ነበር:: በተጨማሪም ዛሬ ላይ የሚገነቡ ሰዎችን የግብዓት እና የሰው ኃይል ሽሚያን ያስቀር እንደነበር እምነታቸው ነው::
እንደ ምጣኔ ሀብት ምሁሩ ትልቁ ክፍተት የሕዝብን ተጠቃሚነት ቀዳሚ ዓላማ በማድረግ ለባለሐብቶች ቦታ ያስተላለፈው የመንግሥት አካል ነው:: በመሆኑም ቦታን ከማስተላለፍ ባሻገር በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ወደ ሥራ ግባቸውን መከታተል እና እስከ መንጠቅ የሚደርስ እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል::
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ብርሃን ንጉሴ እንደገለጹት ቦታ ታጥሮ የሚቀመጥ እና ህንጻዎች ተጀምረው የማይጠናቀቁ ከሆነ ባሕር ዳርን የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ከተማ ማድረግ አይቻልም:: በአሁኑ ወቅት ከከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት እየተመረቀ የሚወጣውን ከፍተኛ ሥራ ፈላጊ መሸከም የሚችለው የግሉ ዘርፍ በመሆኑ ዘርፉን ማነቃቃት እና ችግሮችን ለይቶ መደገፍ እንደሚገባ ታምኖ ወደ እንቅስቃሴ መገባቱን አስታውቀዋል::
በከተማ አስተዳድሩ ግንባታቸው የተቋረጡ እና ታጥረው የተያዙ 73 ቦታዎች መለየታቸውንም ጠቁመዋል:: ሕንጻዎቹ በጅምር ለምን ረዥም ዓመታትን ዘለቁ? ባለቤታቸው ማነው? በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ ከባለሐብቶች ጋር ውይይት መደረጉንም አስታውቀዋል::
የኑሮ ውድነት እና ሀገሪቱ የቆየችበት ወቅታዊ ሁኔታ በባለሐብቶች በኩል ለግንባታ መጓተቶች በምክንያትነት የተነሱ ናቸው:: ነገር ግን እነዚህ ምክንያቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው የገለጹት ወ/ሮ ብርሃን፣ ጥናት ተደርጎ ዝቅተኛው የግንባታ መጓተት የታየበት ህንጻ ሦስት ዓመት መሆኑን ጠቁመዋል:: ሌላው አንዱን ሳያጠናቅቁ ወደ ሌላ የኢንቨስትመንት ዘርፍ መሠማራት ለግንባታዎች መጓተት ዋናው ምክንያት መሆኑንም አንስተዋል::
ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው በከተማዋ ገጽታ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩንም መምሪያ ኃላፊዋ ገልጸዋል:: ከዚህ አንጻር ከተማ አስተዳድሩ ጅምር ሕንጻዎች እንዲጠናቀቁ እና ወደ ግንባታ መግባት ያለባቸው እንዲገቡ የሚያስችል መፍትሄ አስቀምጧል:: ይህም ባለሀብቶች ግንባታ እንዲያቋርጡ ያስገደዷቸውን ምክንያቶች እንዲያሳውቁ፣ ከመቼ ጀምሮ ወደ ግንባታ እንደሚገቡ እና መቼስ ያጠናቅቃሉ? የሚሉትን ጉዳዮችን የሚያሳውቁበት የአንድ ሳምንት ጊዜ ሰጥቷቸዋል። በመመሪያ መሰረት እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ የተጠናቀቁ ሕጻዎችን በባሕር ዳር ማየት እንደሚናፍቅም ገልጸዋል::
1.8K views03:09