2022-07-04 17:07:22
+ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዲህ አለ +
“ከልቦቻችን በማይነቀሉ የፍቅሩ ችንካሮች ተቸነከርን:: ያዝነው አንለቀውም እርሱም አቀፈን አልተወንም:: ወደ እርሱ በሃይማኖት አቀረበን:: ከእርሱም ወደ ቀኝ ወደ ግራ አንሸሽም:: እንደ ቀለበት በልባችን እንደ ማኅተም በክንዳችን አኖርነው:: እንደ ዕንቁ በልባችን ሳጥን አስቀመጥነው:: እንደ ወርቅ በሕሊናችን መዝገብ አኖርነው::
እንደ ግምጃ ለበስነው:: እንደ ሐር ግምጃ ተጎናጸፍነው:: እንደ ወታደር ሰይፍ ታጠቅነው:: ለጦር ዕቃ እንደተዘጋጀ የድል ጋሻ ተደገፍነው:: ተከዜና ግዮን በኢሎል ወር እንደሚሞሉ ፍቅሩ በልባችን መልቶአል:: እንደ መከር ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ እንደ ክረምት ጊዜም የጤግሮስ ወንዝ ስንዴ ሲያሹት እንደሚሆን እንደ ኤፍራጥስ ወንዝ ልባችንን በወንጌል ፈሳሽነት አረሰረሰው:: መርከባችንንም በሃይማኖት ወንዝ አስዋኘው"
መጽሐፈ ምሥጢር 24:20
"ከእኛ ወገን ክርስቲያን እየተባሉ በገዛ መንገዳቸው የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው ... የእንስሳ ሥጋ ከመብላት የሚከለከሉ የሰውን ሥጋ ለመብላት ግን የሚተጉ እነዚህ ናቸው"
"ስምዖን ጴጥሮስ ከሐዋርያት ሁሉ አብልጦ ክርስቶስን ወደደው:: ክርስቶስ ግን ከሐዋርያት ሁሉ አልቆ ወንጌላዊው ዮሐንስን ይወድደው ነበር::
ስለወደደው ግን አለቃ መሆንን ለዮሐንስ አልሠጠም:: እርሱ ከወደደው በላይ እርሱን የሚወደውን አለቃ አደረገው እንጂ"
"ክርስቶስን መውደድ ከወንድሞቹ ይልቅ በጴጥሮስ ላይ በዛ:: ከወንድሞቹ ይልቅ ወደ ጌታ ኢየሱስ ለመድረስ ቸኩሏልና ከመርከቢቱ ዘልሎ ወደ ባሕር ተወረወረ እንጂ በመርከብ ለመጎተት አልቆየም::
ወደ ወደደው ለመድረስ ቀደማቸው:: ከመርከቢቱ ላይ ያዘለለችው ወደ ጥልቁም ባሕር የወረወረችው ፍቅር እርስዋ የክህደቱን መጽሐፍ ደመሰሰችለት::
ራሱን ወደ ጥልቁ የጥብርያዶስ ባሕር በወረወረ ጊዜ የዕዳው መጽሐፍ ሰጠመ:: እርሱ ግን በብዙ ጭንቅ በብዙም ፍለጋ በዋናተኞችም በብልጠታቸው ጥበብ እንደሚገኝ እንደሚያበራ ዕንቁ ሆኖ ከባሕር ውስጥ ወጣ"
ከመጽሐፈ ምሥጢር ውብ ገጾች
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሰኔ 27 2014 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
471 viewsንፁህ ልብን ፍጠርልኝ , 14:07