2022-08-12 21:48:24
አጫጭር መረጃዎች
1፤ የዩክሬን መሠረተ ልማት ሚንስትር ኦሌክሳንደር ኩብራኮቭ አገራቸው ሰሞኑን 23 ሺህ ቶን እህል በመርከብ ወደ ኢትዮጵያ እንደምትልክ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል። ጥራጥሬውን የገዛው የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንደሆነ ሚንስትሩ ጠቁመዋል። ዩክሬን ጥራጥሬ ምርቷን ወደ ኢትዮጵያ የምትልከው፣ በጦርነቱ ምክንያት ወደቦቿ ላይ ተከማችቶ የከረመውን የእህል ምርቷን ለዓለም ገበያ እንድታቀርብ በሦስተኛ አደራዳሪዎች አማካኝነት ከሩሲያ ጋር በደረሰችው ስምምነት መሠረት ነው።
2፤ የሕዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ዛሬ በስኬት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል። የግድቡ ውሃ ሙሌት መጠናቀቅ የተበሰረው፣ ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በግድቡ በተገኙበት ስነ ሥርዓት ላይ ነው። የግድቡ መካከለኛ ክፍል ከፍታ 600 ሜትር፣ የግራና ቀኙ ክፍል ደሞ 611 ሜትር መድረሱን ተከትሎ፣ ውሃው በግድቡ አናት ላይ ፈሷል።
3፤ መንግሥት ለትግራይ መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንደገና መጀመርን የድርድር ቅድመ ሁኔታ እንደማያደርግ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ መናገራቸውን መግለጫውን የተከታተለው ዶይቸቨለ ዘግቧል። አገልግሎቶቹን እንደገና ለመጀመር ግን፣ የጸጥታ፣ የደኅንነትና የሕግ ጉዳዮችን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ መለስ ጠቁመዋል። መንግሥት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ዕቅድ አውጥተው ወደ ተግባር እንዲገቡ ፍላጎቱ መሆኑን መለስ ጨምረው ገልጸዋል።
4፤ ኢሰመጉ መንግሥት መንገደኞች ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የመግባት መብታቸውን እንዲያስከብርና በከተማዋ ዙሪያ ባሉ ፍተሻ ኬላዎች ላይ መንገደኞችን የሚያጉላሉ፣ የሚደበድቡ፣ የሚያስሩ እና ከመንገደኞች ጉቦ የሚቀበሉ የጸጥታ ኃይል አባላትን በሕግ እንዲጠይቅ ዛሬ ባወጣው ጠይቋል። ሸኖ፣ አለልቱ፣ በኪ፣ ሰንዳፋ እና ለገጣፎ የፍተሻ ኬላዎች ላይ ጸጥታ ኃይሎች መታወቂያ እያዩ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ መታወቂያ የሌላቸውን ወደመጡበት እየመለሱ መሆኑን ኢሰመጉ ገልጧል። ሰላምና ትራንስፖርት ሚንስቴሮች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡት ነሐሴ 3 ላይ መጠየቁንም ኢሰመጉ ጠቅሷል።
5፤ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን በግጭትና ጦርነት ለወደሙ የትምህርትና ጤና መሠረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ 3.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ መንግሥት ካዘጋጀው የመልሶ ግንባታ ሰነድ መመልከቱን ሪፖርተር ዘግቧል። የትምህርትና ጤና ሚንስቴሮች በዓለም ባንክ ድጋፍ በሦስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚተገበር የ5 ዓመት የመልሶ ግንባታ ዕቅድ አዘጋጅተዋል። በትምህርት መሠረተ ልማቶችና በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ የደረሰው ኪሳራ ብቻ 2.2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚፈልግ በሰነዱ ተመልክቷል።
6፤ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ በሙስና ተጠርጣሪው የቀድሞው የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ላይ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰርት ዛሬ ማዘዙን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል። ችሎቱ ትዕዛዙን የሰጠው፣ መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ማስተላለፉን በገለጸውና ዓቃቤ ሕግም ለክስ መመስረቻ 15 ቀናት እንዲሰጠው በጠየቀው መሠረት ነው። ጠበቆች ደንበኛቸው የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡትን አቤቱታ ችሎቱ አልተቀበለውም።
7፤ ንግድ ባንክ ለሠራተኞቹ እና ከባንኩ ጋር ለሚሠሩት የኮመርሻል ኖሚኒስ ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉን እና ቦነስ መስጠቱን በድረገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል። ባንኩ የደመወዝ ጭማሪውን የፈቀደው፣ በሰኔ ወር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቡ እንደሆነ ገልጧል። ባንኩ ባለቀው በጀት ዓመት ከዕቅዱ የ114.4 በመቶ አፈጻጸም በስመዝገብ 27.5 ቢልዮን በላይ ብር ትርፍ አግኝቻለሁ ማለቱ ይታወሳል።
8፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 52 ብር ከ2795 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 53 ብር ከ3251 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 60 ብር ከ9208 ሳንቲም፣ መሸጫው 62 ብር ከ1392 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ53 ብር ከ 9681ሳንቲም ሲገዛ እና በ55 ብር ከ0475 ሳንቲም ሲሸጥ ውሏል። አንድ የቻይና ዩዋን ደሞ በ7 ብር ከ0204 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ7 ብር ከ1608 ሳንቲም ተሽጧል።
1.3K viewsMAK story, 18:48