2022-08-25 20:06:43
ዐበይት ዜናዎች
1፤ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ዛሬ የሥራ ማቆምና ከቤት ያለመውጣት አድማ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ እንደተመታ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል። በከተማዋ የንግድ መደብሮች እና ባንኮች ተዘግተው እና የትራንስፖርት አገልግሎትም ተቋርጦ መዋሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል። የከተማዋ ሕዝብ አድማ የመታበት ምክንያት፣ የጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄ ምላሽ ካለማግኘቱ ጋር የተያይዘ እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል። የደቡብ ክልል ጸጥታ ዕዝ የንግድ መደብሮችንና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ማቋረጥ ክልክል መሆኑን ትናንት አስጠንቅቆ ነበር።
2፤ መንግሥት ሕወሃት ትናንት በመቀሌ የዘረፈውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ነዳጅ እንዲመልስ ዛሬ በቃል አቀባይ ቢሮው በኩል ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። መንግሥት ዓለማቀፍ ድርጅቶች ለነዳጅ ዝርፊያው ቡድኑን ተጠያቂ እንዲያደርጉና ሕወሃትም ሰብዓዊ ዕርዳታ ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንደሚውል ማስተማመኛ እንዲሰጥ ጠይቋል። የነዳጅ ዝርፊያው የጦር ወንጀልና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን የጠቀሰው መንግሥት፣ ሕወሃት ዝርፊያውን ለማስቆም የሞከሩ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞችን አስሯል በማለት ከሷል። ዝርፊያው ሕወሃት ዕርዳታን ለጦርነት ዓላማ ሲጠቀም እንደቆየ ማረጋገጫ መሆኑን መንግሥት ገልጧል።
3፤ የሱዳን ጦር ሠራዊት ኢትዮጵያ በሱዳን በኩል ጦር መሳሪያ ጭኖ ወደ ትግራይ ሲገባ መትቼ ጣልኩ ካለችው ክስተት ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም ሲል በቃል አቀባዩ በኩል በሰጠው ቃል ማስተባበሉን ብሉምበርግ ዘግቧል። ዜና ምንጩ አንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የጸጥታ ሹም፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጦር መሳሪያ ጭኖ ወደ ትግራይ የገባ አውሮፕላን መትቶ ጥሏል በማለት እንደነገሩት ጠቅሷል። የሕወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፣ የመንግሥት መረጃ "ሐሰት ነው" ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል። መንግሥት መትቼ ጥያለሁ ስላለው አውሮፕላን ከትናንት ወዲህ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጠም።
4፤ በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራዩ ሕወሃት መካከል ድጋሚ ግጭት ማገርሸቱ አሳስቦናል ሲሉ አሜሪካ እና ቱርክ በየፊናቸው ስጋታቸውን ገልጸዋል። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ መንግሥትና ሕወሃት ለሰላም መስፈን ከፍተኛ ጥረቶችን እንዲያደርጉ በትዊተር ገጻቸው አሳስበዋል። የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ ደሞ፣ መንግሥት እና ሕወሃት ወደ ሰላማዊ ንግግር እንዲመለሱና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጠይቋል።
5፤ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ክስ ላይ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን ሰነዶች መርምሮና የተከሳሹን ጠበቆች አስተያየት ምርምሮ ብይን ለመስጠት ለነሐሴ 27 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ቤተሰቦቹ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል። ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸው ማስረጃዎች ጋዜጠኛው ማኔጅንግ ኤዲተርና ባለቤት በሆነባት "ፍትህ" መጽሄት ላይ የታተሙ 17 ጽሁፎችን ነው። ፍርድ ቤቱ በዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎች ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ የነበረው ለዛሬ ሲሆን፣ ሆኖም ሰነዶቹ ብዙ በመሆናቸው ተለዋጭ ቀጠሮ ለመስጠት እንደተገደደ ገልጧል።
6፤ የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን አግተው ለኦነግ ሸኔ አሳልፈው ሰጥተዋል በተባሉ አምስት ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ በማሳለፍ ለነሐሴ 30 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን አዲስ ማለዳ ዘግቧል። ዛሬ የጥፋተኛነት ውሳኔ የተላለፈባቸው፣ ጋዲሳ ገለቱ፣ ናስር መሐመድ፣ ነብዩ በባክር፣ ከሊፋ አብዱራህማንና ዮሴፍ ጃረታ ናቸው። ጥፋተኞቹ የኦነግ ሸኔን ዓላማ ለማራመድና የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎች ለማገት ከቡድኑ ጋር ተስማምተው እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል። ተማሪዎቹ ኅዳር 24፣ 2012 ዓ፣ም የታገቱት፣ ከደምቢዶሎ ወደ አማራ ክልል በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ሲጓዙ ነበር።
7፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን መሐመድ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ወደ ፑንትላንድ ራስ ገዝ ማቅናታቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ከውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸው አብሺር ሁርሴ ጋር ብቻ ፑንትላንድ የገቡት ፕሬዝዳንቱ፣ ከፑንትላንዱ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ደኒ ጋር ተወያይተዋል ተብሏል። ደኒ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው የፕሬዝዳንት ሞሐመድ ተቀናቃኝ ነበሩ። ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ፑንትላንድ የሄዱት፣ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በራስ ገዟ ጉብኝት ባደረገና ከፕሬዝዳንት ደኒ ጋር በተወያየ ማግስት ነው።
8፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 52 ብር ከ4077 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 53 ብር ከ4559 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 59 ብር ከ0182 ሳንቲም፣ መሸጫው 60 ብር ከ1986 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ52 ብር ከ1142 ሳንቲም ሲገዛ እና በ53 ብር ከ1565 ሳንቲም ሲሸጥ ውሏል።
713 viewsMAK story, 17:06