2022-06-28 09:51:31
የማታልፍ ጽዋ
“ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፦ አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ።” — ማቴዎስ 26፥39
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ነበር። በሁሉን አዋቂ ማንነቱ መከዳት ሊደርስበት፤ ሁሉም በአንድ ልብ ተስማምተው ሊሰቀል እንደሆነ፤ የዓለም ሁሉ ኃጢአት በእርሱ ላይ ሊሆን እንደሆነ ያውቃል።
ወዳጆቼ እስቲ ለአንድ ደቂቃ ራሳችንን ጌታ ኢየሱስ በነበረበት ቦታ ላይ አስቀምጠን እናስብ። እኛ ነገ ሊሆንብን ያለውን ነገር ብናውቅ እንሸሽ ነበር፤ ራሳችንን እንሰውር ነበር። ጌታ ግን የሚደርስበትን ሁሉ እያወቀ ተዘጋጀ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም ኃይል አለው። ፕላኔቶችን ከዋክብትንና ሁሉንም ፍጥረት በቃሉ የፈጠረ ጌታ ነው። ይህ ጌታ በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር አብ ላይ ምንም ስህተት አላደረገም ግን ሊሰቀል ነው። ከመሰቀልም አልፎ ለዘላለም አብሮት የነበረው አባቱ ፊቱን ሊመልስበት ነው። ልመናው የማይሰማበት ጸሎቱ የማይመለስበት ጊዜ ሊመጣ ነው።
ጌታችን ሞትን መቅመስ ሳይሆን ፍርሀት የገባው ለባህሪው የማይስማማውን ኃጢአት ሊሸከም መሆኑን ሲያስብ ይህች ጽዋ ከኔ ትለፍ ብሎ ጸለየ። ጌታችን እንዲህ ብሎ በመጸለዩ ላይ ምንም ስህተት የለም። ነገር ግን እግዚአብሔር አብ ሃሳቡን አይለውጥም፤ መልሱንም አይቀይርም። የእግዚአብሔር ፍቃድ ጌታችን ኢየሱስ እንዲሰቀል ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለመሰቀል፣ መከራ ያለመቀበል ሙሉ ኃይልና ስልጣን ቢኖረውም ያንን ስልጣኑን ወደጎን በማስቀመጥ የአብን ፍቃድ ለመፈፀም ወስኗል።
እግዚአብሔር ፈቃዱ ዛሬም በእኛ ሕይወት እንዲፈፀም ይፈልጋል። ግን ፍቃዱን ለማድረግ ፍቃደኛ ነን? ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር አንድን ነገር እንድናደርግ በግልፅ ሲናገረን እንሰማለን ነገር ግን ይህንን ላለማድረግ እንወስናለን። እግዚአብሔርን እንጠይቃለን ግን መልሰን የራሳችንን መንገድ እንወስናለን።
እግዚአብሔር እንድንሞት እየጠየቀን ላይሆን ይችላል ነገር ግን ራሳችንን ወደ ጎን እንድንተውና አንድ ነገር እንድናደርግ እየጠየቀን ነው። ያ ነገር ምንም ቢሆን ለእኛ ጥቅም፣ ለሎሎች ጥቅም፣ ለእግዚአብሔር ክብር ነው።
ጌታችን ጽዋዋ እንድታልፍ ቢፈልግም የራሱ ፍላጎት ሳይሆን የአባቱ ፍቃድ እንዲፈፀም ፈለገ። እኛም በሕይወታችን በየዕለት ተዕለት ጉዟችን የኛ ፍላጎት ሳይሆን የእግዚአብሔር ፍቃድ እንዲፈጸም መፈለግ አለብን። የአጭር ጊዜ ምኞቶቻችንን ወደ ጎን አስቀምጠን እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ መከተል አለብን። ይህ ሲሆን መጨረሻችን ዋጋ ያለው ይሆናል።
ብዙ ሰው በራሱ ምኞትና ሀሳብ ለብዙ ኪሳራና እንግልት ተዳርጓል የእግዚአብሔር ፍቃድ ግን ከአጉል ውሳኔና ሕይወት ይጠብቀናል። መልስ ከሌለው ጥያቄ ይጋርደናል። ፍቃዱ ከፊታችን ያለውን ጭጋግ ወጋገን ሆኖ ይመራናል።
ጸሎት
አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ እስከ ዛሬ እንደልባችን ተጉዘናል እንደልባችን ሆነናል ዛሬ ግን አንደ ልብህ መሆን ይሁንልን። ለፍላጎታችን ተሸንፈን ለምኞቶቻችን ተታለን አንተን አሳዝነናል ዛሬ ግን ለፍቃድህ መሸነፍ እንዲሆንልን ባየህልን ጎዳና መጓዝ እንዲሆንልን መንፈስህ ያግዘን። ለሕይወታችን ፍላጎት ስንል ከአንተ ፍቃድና ዓላማ እንዳንመለስ በጸጋህ እርዳን። አሜን
አዶኒ
ሰኔ 21/2014
ቤተሰብ ይሁኑ
@adonigospel
@adonigospel
1.5K views@doni, 06:51