2022-07-07 07:33:43
የማይጠገበው ርዕስ ፍቅርርር
“ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤”
— 1ኛ ቆሮንቶስ 13፥4
ፍቅር አካል የለውም ግን ተገልጦ ይታያል፤ ፍቅር አይዳሰሰም ግን ብዙዎችን ይዳስሳል፤ ፍቅር ኪሎው ስንት ነው አይባልም ከልክ ያለፈ ነው። ፍቅር በሰውነታችን ውስጥ እንደ ኩላሊት፣ እንደ ልብ፣ እንደ ጨጓራ አንድ ስፍራ ይዞ እዚህ ጋር ነው የተቀመጥ አይባልለትም በመላ ማንነታችን ውስጥ የፈሰሰና የተሰራጨ ነው። ፍቅር በዓይኖቻችን ሆኖ ሰው የረሳቸውን ይመለከታል፤ ፍቅር በእጃችን ሆኖ የወደቁትን ያነሳል፤ ፍቅር በእግራችን ሆኖ ወዳጅ ወደሌላቸው ሰዎች ይገሰግሳል፤ ፍቅር በልባችን ሆኖ ሰውን ሁሉ ያፈቅራል።
ፍቅር ስሜት አይደለም እውነት ነው። ስሜት ተለዋዋጭ ነው ፍቅር ግን የጸና ነው። ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅርን ከስሜት ጋር ብቻ
አያይዞ የማይጠቅሰው። ፍቅር ሰፊ የትዕግስት ትከሻ አለው፤ ፍቅር ለሌሎች የሚተርፍ ቸርነት አለው፤ ፍቅር በሰዎች ደስ ይሰኛል እንጂ አይቀናም፤ ፍቅር ዝቅ ብሎ የሚያከብር እንጂ ከፍ ብሎ የሚያዋርድ አይደለም።
ወዳጆቼ እኛ ፍቅር የምንለው አለመተዋወቅን ነው። ይህ ማለት አንድን ሰው ያወቅነው መስሎን በጣም መልካም፣ ደግ፣ ጨዋ፣ ሩህሩህ ነው ብለን እንወደዋለን። ልክ እንድ የማንጠብቀውን ነገር ሲያደርግ ስናይ እንዲህ አይነት ሰው መሆኑን አላውቅም ነበር፣ እንዲህ አይነት መልኩን በፍፁም አላስተዋልኩም ብለን ስናውቀው እንጠላዋለን። ፍቅር ግን እንዲህ አይደለም። እውነተኛ ፍቅር የሚመጣው ስለ አንድ ሰው ጥንካሬና ድክመት በሚገባ ስናውቅ ነው።
እውነተኛ ፍቅር የያዘው ሰው እነዚህን ነገሮች
የሚያደርገው ጭፍን ስለሆነ ወይም ስለሚወደው ሰው ምንም ስለማያውቅ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ግለሰቡ ማንነት የተሟላ እውቀት ስላለው ነው።
የፍቅር ሚዛኑ ካፍቴርያ ውስጥ መሳሳቅ መቻል አይደለም ትዕግስትን የሚፈታተኑ ድክመቶቹን ሳይሰለቹ በልበ ሰፊነት እያረቁ በትዕግስት መሸከም ሲቻል። በቸገረው ሰዓት፣ እጁ ባዶ በሆነበት ሰዓት እኔን ላንተ እግዚአብሔር የሰጠኝ ባዶ በሆንክበት ጊዜ ድክመትህን ሸፍኜ መቆም እንድችል ነው ብሎ ቸርነትን ማድረግ ነው።
ሀበሻ በሰው ማጣት ይደሰታል በሰው መሳካት ግን ይከፋል። ክርስቲያን ግን የሰውን ስኬት ሲመለከት ከልቡ የእውነት መደሰት መቻል አለበት። ከደስታው ባለፈ በቻለው መጠን ለስኬቱ አስተዋጽዖ ማድረግ ይኖርበታል። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ የልብ ወዳጅ ሳይሆን የጥርስ ብቻ ወዳጅ ስለሆንን እንስቃለን ልባችን ግን ጥላቻን ያመረቅዛል። ይህ ማንነታችን ብዙ አጠገባችን ያሉ ለብዙ ነገር መትረፍ የሚችል ራዕይ ተሸክመው ቁጭ ያሉ ሰዎችን በድካማቸው ገብቶ የሚረዳቸው የሚደግፋቸው ሰው ባለመኖሩ ከነራዕያቸው ያረጃሉ ያልፋሉ ።
ወዳጆቼ አጠገባችሁ ያለውን የምታውቁትን፣ ወዳጄ የምትሉትን ሰው ራዕይህ ምንድነው? በቀጣይ ምን ለማድረግ አስበሃል? በአንተ ራዕይ ውስጥ የኔ ተሳትፎ ምን መሆን ይችላል? ብላችሁ ጠይቋቸው። የምትችሉትን ያህል ተዘርጉላቸው እናንተም እነርሱም ደስተኛ ትሆናላችሁ። እግዚአብሔር ፍቅርን ያብዛላችሁ።
አዶኒ
ሰኔ 30/2014
@adonigospel
@adonigospel
1.5K views@doni, edited 04:33