2022-05-09 08:49:47
#ይነበብ
የህይወት ሚዛን
ከዶ/ር ኢዮብ ማሞ
አንድ ሰው በጣም የሚወደው ልጅ ነበረው፡፡ ለዚህ ልጁ ሕይወትን በብልሃትና በሚዛናዊነት እንዴት መኖር እንደሚችል ሊያስተምረው ይጣጣር ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙም የተሳካለት አልመሰለውም፡፡ ልጁ በፊቱ የመጣለትን ነገር በማድረግ የሚነዳና ምንም አይነት እቅድ የሞላው ሕይወት እንዳላዳበረ ገባው፡፡ በአካባቢው በጥበቡ የታወቀ አንድ ሰው ነበረና የሕይወትን ስልትና ብልሃት እንዲማር ወደዚያ ጠቢብ ሰው ላከው፡፡
ልጁ ወደጠቢቡ በመሄድ እንዲህ አለው፣ “ሕይወቴን ስልት በተሞላው ሁኔታ እንዴት መምራት እንዳለብኝ ለመማር ነው የመጣሁት”፡፡ ጠቢቡ፣ “አሁን ትንሽ ስራ አለብኝ፣ ከሁለት ሰዓታት በኋላ ቆይተህ ተመለስ፡፡ እስከዚያው ግን አንድን ነገር እንድታደርግ ስራ ልስጥህ” በማለት፣ በእጁ አንድን የሻይ ማንኪያ ሰጠውና በማንኪያው ላይ ዘይትን ሞላበት፡፡ ከዚያም እንዲህ አለው፣ “በህንጻው ውስጥ እየተዘዋወርክ ያሉትን ድንቅ ቅርሶች በመመልከት ሁለት መጠበቅ ያለብህን ሰዓታት አሳልፍ፡፡ አንድ ነገር ግን ተጠንቀቅ፣ በፍጹም ይህ በማንኪያው ላይ ያለው ዘይት መፍሰስ የለበትም”፡፡ ልጁ አደራውን ተቀብሎ፣ ስንት ሰዓት እንደሆነ ከቃኘ በኋላ ህንጻውን ለመጎብኘት በእጁ ዘይት የሞላበትን ማንኪያ ይዞ በቀስታ በመራመድ ወጣ፡፡
ልጁ ከሁለት ሰዓት በኋላ ወደ ጠቢቡ ተመለሰ፡፡ ጠቢቡ ካስገባው በኋላ፣ “በምግብ አዳራሽ ውስጥ በግድግዳው ላይ የተሰቀለውን የጥንት ስእል አየኸው? የታወቁ አትክልተኞች አስር አመት የፈጀባቸውን የአትክልት ስፍራ አየኸው? የአለምን እውቀት በሙሉ የያዘውንስ የመጽሐፍት ቤት አየኸው?” ልጁ አፍሮ አንገቱን አቀረቀረ፡፡ ለካ ለሁለት ሰዓታት ሲዘዋወር ትኩረቱ ሁሉ በእጁ የያዘው ማንኪያ ላይ የተቀመጠው ዘይት እንዳይፈስ ነበር፡፡ ጠቢቡ ሊያስተምረው የፈለገው ነገር እንደተሳካለት ገባውና፣ “እደገና በማንኪያ ያለውን ዘይት ይዘህ ሂድና እነዚህ የነገርኩህንና ሌሎችም አስገራሚ ቅርሶች እንደገና ተመልክተህ ተመለስ” አለው፡፡
ሁለተኛ እድል ስላገኘ ትንሽ ተንፈስ ያለው ወጣት ተመልሶ ወጣ፡፡ ለሁለት ሰዓታት ጉብኙቱን ካጧጧፈ በኋላ በፈገግታ ተመለሰና ያየውን ሁሉ ለጠቢቡ ነገረው፡፡ እስኪጨርስ ጠብቆ ጠቢቡ፣ “እንዳይፈስስ ያልኩህ ዘይት የት አለ?” አለው፡፡ ልጁ፣ ጎንበስ ብሎ በእጁ የያዘውን ማንኪያ ሲያየው ለካ ዙሪያውን በመመልከት ሲዝናና ዘይቱን እላ ስላለው ዘይቱ ሙልጭ ብሎ ፈስሷል፡፡ ጠቢቡም እንዲህ አለው፣ “ስኬታማ ሕይወት ማለት ሚዛዊነትና ስልት የተሞላውን ሕይወት መኖር ማለት ነው፡፡ ሚዛናዊነትና ስልታማ ሕይወት ማለት ዙሪያህን እያየህ በማድነቅ ስትኖር በእጅህ ላይ ያለውን አደራ አለመዘንጋት ነው”፡፡
በሕይወታችን ልክ እንደ ዘይቱ በጥንቃቄ መያዝ ያለብን አደራዎች አሉን፡፡ ከዚያው ጋር ደግሞ ልክ በአዳራሽ ውስጥ እንዳሉት መዝናኛ ቦታዎች የመጫወት እድል የሚሰጡን ሁኔታዎች አሉ፡፡ ስኬታማ ሰው እነዚህን ሁለቱን በሚዛናዊነት የያዘ ሰው ነው፡፡
ስንጫወት፣ ስንዝናና፣ ስንደሰትና በማሕበራዊው ግንኙነታችን ውስጥ ያለውን ደስ የሚያሰኝ ሁኔታ ስንፈነድቅበት፣ ከዚያ የተነሳ በእጃችን ላይ ያለው አደራ ችላ እንዳይባልና ዘይቱ እንዳይፈስ መጠንቀቅ የጥበብ ሁሉ ጥበብ ነው፡፡ ልክ ይህ ወጣት በእጁ ያለውን ዘይት በዙሪያው ካለው ታላላቅ ነገርን የማየት እድል ጋር አስታርቆና ሚዛናዊ አድርጎ መውጣትና መግባት እንደነበረበት እኛም እንዲሁ!
ሰናይ ጊዜ
#Share
Join: @yehiywetqulfoch
Join: @yehiywetqulfoch
1.4K viewsLij Nåol , 05:49