2022-01-14 18:20:06
መፈጸም፤መጨረስ ያሉብንን ነገሮች እያስተላለፍን ከማስረፈድ ልማድ የምነወጣበት 11 አብይ መንገዶች።
ዴድላይናችሁ ደርሷል። ቢሆንም ስራችሁን እንደመፈጸም የማይረቡ ነገሮችን እያደረጋችሁ ነው። ፌስቡክ ትከፍታላችሁ፣ ፊልም ታያላችሁ፣ ኢንተርኔት ውስጥ ትዞራላቹ ወዘተ። መስራት ወይም ማጥናት እንዳለባችሁ እያወቃቹም አታቆሙም።
ሁላችንም ስለነገር ማዘግየት በራሳችን እናውቃለን። ስናዘገይ ነጻ ግዜአችንን በከንቱ እናጠፋለን፣ መፈጸም ያሉብንን ነገሮች እስኪረፍድ እንተዋለን። ከረፈድ በኋላ ደግሞ ጭንቀት ውስጥ እንገባለን። አስቀድመን ለምን አልጀመርንም እያልን እራሳችንን እንወቅሳለን። ይህ ችግር በከፍተኛ ደረጃ የተጠናወታቸው ለአመታት ይህን ልማድ እንደዙር ሲደጋግሙ ይቆያሉ። ነገሮችን የሚያስረፍድ፣ መከናወን ያለበትን የሚያቆይ፣ ስነፍ፣ ከስራ የሚደበቅ ሁሉ መገለጫችን ይሆናሉ። ይህ ችግር ውስጣችንን እየበላ በህይወታችን ማሳካት ከሚገቡን ነገሮች አርቆ ያስቀምጠናል።
ይህ ልማድ እድሜያችሁን እስኪጨርስ አጠብቁ። በዚህ ጽሁፍ ሰዎች ከዚህ ልማዳቸው የወጡባቸውን መንገዶች እናያለን።
1) ስራችሁን በትንንሹ ከፋፍሉ
ነገሮችን የምናዘገይበት አንዱ ምክንያት ጉዳዩን ለመፈጸም በጣም ከባድ መስሎ ስለሚታየን ነው። በዚህ ግዜ የመጀምርያው ክንውናችን መሆን ያለበት ስራውን በትንሹ መከፋፈል ነው። ከዛም በአንድ ግዜ አንዱን ብቻ መፈጸም ነው ያለብን። አሁንም እራሳችሁ ስትሰንፉ ካገኛቹት የሰራቹትን ክፍፍል ይበልጥ አስፉት። ስራዎቹ በጣም ሲያንሱ ለራሳችሁ “ይቺ ብቻ ናት የቀረችኝ” ብለው ማሰብ ይጀምራሉ።
2) በአካባቢያችሁ ያለውን ነገር ቀይሩ
የተለያዩ ቦታ እና ሁኔታዎች በምርታማነታችሁ ላይ ተጽእኖ ያደርጋሉ። የስራ ገበታችሁን ሆነ ክፍላችሁን አጢናችሁ ተመልከቱ። ስራ እንድትሰሩ ይገፋፍል ወይስ ጠቅልላችሁ ተኙ ነው የሚላችሁ? ለስራ ካልጋበዛችሁ የስራ አካባቢያችሁን መቀየር ይረዳችኋል። ከዚህ በፊት ይመቻችሁ የነበረው የመስሪያ ስፔስ ወይም ቦታ ከግዜ በኋላ ሊሰለቻችሁ ስለሚችል አከባቢውን መለዋወጥ ይረዳችኋል።
3) ምን መቼ ማለቅ እንዳለበት እቅድ አውጡ
አንድ ዴድላይን ለሟሟላት መጣር ለእራሳችሁ የስንፍና ፈቃድ የመስጠት ያህል ነው። ምክንያቱም ግዜ ያለን ይመስለንና ግዜውን ዝም ብሎ ለማሳለፍ ምክንያት ይሆነናል። መስራት ያለባችሁን ፕሮጀክት ከከፋፈላችሁ በኋላ ለእያንዳንዱ ዴድላይን(መጨረሻ ጊዜ) አዘጋጁ። ግዜ አከፋፈላችሁን አጢናችሁ አውጡ። አንዱን አለማሳካት ማለት የሌላኛውን እቅድ የሚያስተጓጉል እንዲሆን አድርገው። የዛኔ የግዜ ግምታችሁ ስራችሁ ከሚያስፈልገው ግዜ ጋር እንዲጣጣም አደረጋችሁ ማለት ነው። በፍጥነት ስራ እንድትጀምሩ ይረዳችኋል ። ከቻላችሁ ወርሃዊ፣ ሳምንታዊ እና ቀናዊ የስራ ክፍፍል አውጥታችሁ ብትንቀሳቀሱ ይበልጥ ይረዳችኋል ።
4) የስንፍና ማቆሚያዎችዎን አጥፉ
ስንፍና ከተጠናወታችሁ አንዱ ምክንያት ለመስነፍ ስለቀለላችሁ ነው። ስልካችሁ ላይ የሚያዘናጉ አፕሊኬሽኖች ካሉ አጥፏቸው። በተደጋጋሚ የምታዩት ቪድዩ ካለ ጨክናችሁ አጥፉት። ቻት ማድረግ ከሆነ ችግራችሁ መልእክት በደረሳችሁ ቁጥር እንዳይጮህ አድርጉ። በአካባቢያችሁ ያሉ መዘናጊያዎችን አስወግዱ። የማህበራዊ ሚድያ የምትከፍቱበት የተወሰነ ሰአት አዘጋጁ። ከዛ ሰአት ውጪ አትክፈቱ።
5) ስራ እንድትሰሩ ከሚገፋፉ ሰዎች ጋር ለመዋል ሞክሩ
እንደው እንበልና ለ10 ደቂቃ ብቻ ቢል-ጌትስ ወይም ኢሎን-ማስክን የመሰሉ አይነት ሰዎችን ብታነጋግሩ የስራ መነቃቃታችሁ በብዙ እጥፍ ይጨምራል። አብረናቸው ግዜ የምናሳልፋቸው ሰዎች ባህሪያችን ላይ ተጽእኖ አላቸው። እነ ቢል ጌትስን አግኝቶ ማውራት የሚቻል ባይሆንም በአቅራቢያችን ለስራ ከፍተኛ መነቃቃት ያላቸው ሰዎች ይኖራሉ። ከነሱ ጋር አብሮ መዋል የነሱን ባህሪ እንድንላበስ ይረዳናል።
6) እቅድ ያለው ጓደኛ ይኑራችሁ
የራሱ እቅድ ያለው ጓደኛ ቢኖራችሁ እቅዳችሁን ለማሳካት ሁለታችሁም ትተጋገዛላቹህ። አንዱ ሲሰንፍ ሌላኛው በመናገር እንዲቆጣጠር በማድረግ ሁለታችሁም እቅዳችሁን ለማሳካት አብራቹህ ትጥራላቹ። ሁለታችሁም ተመሳሳይ እቅድ ሊኖራቹህ አይገባም። ተመሳሳይ ቢሆን ይበልጥ ልትረዳዱ ትችላላቹህ። ከስህተቶቻችሁ ይበልጥ ትማራላቹ። ባይሆንም ግን በየግዜው ስለ አላማችሁ እና ስራችሁ በግልጽ የምታወሩት ሰው ማግኘት በጣም ጠቃሚ ነው።
7) ስለ እቅዳችሁ ለሌላ ሰው ንገሩ
አንዳንዴ ስለ እቅድዎ ለሚያቁት ሰው ሁሉ መናገር ተጠያቂነት ስሜት ያሳድርባችኋል። የቅርብ ዘመዶች እና ጓደኞቻችሁ “እንዴት ሆነልህ/ሽ” ብለው መጠየቃቸው ስለማይቀር ላለመሸማቀቅ ስትሉ ቢሆን የተወሰነ ክንውን ለመፈጸም ትበረታታላችሁ። በፌስቡክ ገጻችሁ ሆነ ባላችሁ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያችሁ ላይ ስለ እቅዳችሁ በመጠኑ ለጓደኞቻችሁ በሙሉ መግለጽ እቅዳቹን ለማከናዎን ይበልጥ ይገፋችኋል።
8) እቅዶቻችሁን ያሳካ ሰው ፈልጉ
ምንድን ነው ማሳካት የምትፈልጉት? እሱን ያሳኩ ሰዎች እነማን ናችው? ፈልጋችሁ አግኟቸው። ግንኙነት ፍጠሩ። የእቅዳቹን ስኬት ፍሬ የሚያጣጥሙ ሰዎች ማወቅ ለራሳችሁ ከፍተኛ መነቃቃት ይሰጣችኋል።
9) ግባችሁን ሳይሆን እቅዳችሁን በየግዜው አሻሽሉ
አንዳንድ ግዜ የስንፍና መነሻው እቅድ ሲያወጡ የፈጠሩት ስህተት ነው። እቅዳቹን ለማሳካት መፈጸም አለብኝ ብላችሁ ያስቀመጣቹት ክንውን እቅዳቹን ለማሳካት ላይረዳቹ ይችላል። እሱን ስትረዱ ክንውኑን ለመቀየር እንዳትፈሩ። የመጨረሻ እቅዳቹን በተለያየ ምክንያት መቀየር ከፈለጋቹ ጊዜ ሰታችሁ አስቡ። ከግዜ በኋላ በሃሳባችሁ ከጸናችሁ እንዲሁም ለእቅዳቹ መቀየር አሳማኝ ምክንያት ካላችሁ በፍጥነት ቀይራቹ አዲሱን እቅድ ለማሳካት በፍጥነት ተንቀሳቀሱ። አዲሱ እቅዳቹን ለማሳካት የሚያስፈልጋቹን ክንውኖች አውጥታቹ ተንቀሳቀሱ።
10) ነገሮችን አታወሳስቡ
እቅዳቹን ለማሳካት ትክክለኛውን ግዜ እየጠበቃችሁ ነው? በዚህም በዛም ምክንያት ጥሩ ግዜ አይደለም ብላችሁ ታስባላቹ? ከሆነ ይህንን ሃሳብ በፍጥነት ጣሉት። ሁሌም ወደ እቅዳቹ ላለማምራት የሆነ ምክንያት ይኖራል። ትክክለኛው ግዜ እስኪመጣ ብላችሁ የምጠብቁ ከሆነ እቅዳቹን መቼም አታሳኩትም። አንድን ነገር ችግር በሌለበት ግዜ እፈጽማለሁ ብሎ ማሰብ እንዲሁም የምፈጽመው ነገር ችግር ሊኖረው አይገባም ብሎ ማሰብ ቀንደኛ ላለመጀመር የምንጠቀምባቸው ምክንያቶች ናቸው።
11) ዝም ብላችሁ አከናውኑት
መጨረሻ ላይ ዝም ብላችሁ መስራት ያስፈልጋችኋል። ምንም ያህል እቅድ ብታወጡ፣ ብታስቡ፣ ብታወጡ ብታወርዱ ከስራው የሚታደጋቹ ነገር የለም። ምንም ክንውን መፈጸም ካልጀመራቹ ወደ እቅዳቹ አንድ እርምጃም አትንቀሳቀሱም። ምንም አይፈጠርም። ሁሌ ሰዎች በሁኔታቸው ይማረራሉ። ግን በዛውም ልክ ምንም ወደ እቅዳቸው የሚወስዳቸው ስራ ሲሰሩ አይታዩም። በስንፍና ወደ ስኬት መሄድ እንደማይቻል ህይወት ትነግረናለች። ምንም ሆነ ምን መፈጸም የምትፈልጉት ነገር ተነስቶ ማድረግ አሁኑኑ መጀመር ነው።
ለህይወት ጠቃሚ ነገር እንደምታገኙበትና በተግባርም እንደምታውሉት ሙሉ ተስፋ አደርጋለሁ ሰናይ ጊዜ
(Lij- ናol )
ከዶ/ር ኢዮብ መፅሀፍ እንደቀነጨብኩላችሁ...
#ሼር ያድርጉ
የህይወት ቁልፍ
Join: @yehiywetqulfoch
Join: @yehiywetqulfoch
1.7K viewsLij Nåol , 15:20