2024-05-27 15:55:15
ከአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
**
እንደሚታወቀው የአማራ ፋኖ በተቆጣጠራቸው የአማራ ግዛቶች የራሱን ስቪል አስተዳደር ዘርግቶ ከእናት እና አባቶቹ በወረሰው ሐገር በቀል የስነ መንግስት ስርዓት እያስተዳደረ ይገኛል። በጎንደር ክፍለ ሐገር ውስጥ በሚገኙ አምስት ዞኖች ስር የሚጠቃለሉ ወረዳወች እና የወረዳ ከተሞችም በአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ ስር መሆናቸው ይታወቃል።
በእነዚህ ቀጠናዎች ያለው ማህበረሰብ እንደሚያውቀው የአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ ከዚህ በፊት ደም ምለሳ (በቀል) በሚባል ጎጅ ባህል የሚፈላለግን ባላንጣ ሳይቀር እያስታረቀ፣ እየዳኘ መቀጣት ያለበትን እየቀጣ ማህበረሰቡ ለዘመናት የናፈቀውን ማህበራዊ እረፍት ጭላጭል እያሳየ ይገኛል። ይህ እውነት ማህበረሰቡ እራሱ የሚመሰክረው ሐቅ ነው። በተለይ ጨለማን ተገን አድርገው ይሰርቁ የነበሩ ሌቦች ላይ በተወሰደ የማያዳግም እርምጃ ህብረተሰቡ ይናፈቀው የነበረውን የዘመናት እረፍት እንዲያገኝ ተደርጓል።
ይሁን እንጅ የህዝብ ጥግግታቸው ከፍተኛ የሆኑ ከተሞች ላይ ጦርነት ማድረግ የማህበረሰቡን ሶቀቃ መጨመረ እንደሆነ ከተሞክሯችን ስለተረዳን አስፈላጊ ግዳጅ ከሌለለ በስተቀር የዞን ከተሞችን እና ከፍተኛ የተሽከርካሪ ፍሰት ያለባቸውን ጎዳኖች ለጊዜው ከጦርነት ነፃ ቀጠና አድርገን እንደተውናቸው ይታወቃል። በመሆኑም እነዚህ ነፃ ቀጠናወች አራሱን የኢትዮጵያ መከላከያ ሐይል ብሎ በሚጠራ አሸባሪ ሐይል እና ሌሎች የስርዓቱ አገልጋይ ታጣቂዎች መሸሸጊያ ሆነዋል።
ነገር ግን ድሮውንም የአማራን ህዝብ ማህበራዊ እረፍት የማይፈልገው ይህ ገዳይ ቡድን ለጊዜው በእኛ ይሁንታ በተሸሸገባቸው አካባቢዎች በተለይ ጎንደር ከተማ ፣ ከባህርዳር -ጎንደር- ደብረታቦር መስመር፣ከድብረታቦር-ወልድያ መስመር፣ከጎንደር -መተማ መስመር፣ከጎንደር-ደባርቅ መስመሮች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ዘረፋ እየፈፀመ እንደሆነ ማረጋገጥ ችለናል።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው፦
በቅርቡ ወቅን ላይ በተሞከረ ዘረፉ ቆስሎ የተያዘ የቡድኑ አካል የመንግስት ሚሊሻ እንደነበረ እና ተልዕኮ ተሰጥቶት እንደሚሰራ መናገሩ፤ ከአሁን በፊት በቪዲኦ (Video) እንዳሳየነው ሲዘርፉ የተገኙት ሌቦች መንግስት የላከቸው እንደሆኑ መመስከራቸው፤ በኮማንድ ፖስት በሚመራው የጎንደር ከተማ ውስጥ ከመንግስት ተታጣቂወች ውጭ መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በማይቻልበት ሁኔታ የአድማ ብተና የሚሊሻ እና የመከላከያ ሐይል ካንፕ ዙሪያውን በታጠረ ከተማ ውስጥ መትረጊስ እና ሌሎች የቡድን መሳሪያዎችን የታጠቀ ዘራፊ ሐይል የግቢ በርን በሐይል ሰበሮ በመግባት በአንድ ቀን ብቻ ሰባት ሰዎችን ማገቱ፤ እራሱ የአካባቢው ማህበረሰብ እንዳረጋገጠው ተደራጅተው የሚዘርፉ አካሎች እና የመንግስት ሐይሎች በቅርብ እርቀት እየተያዩ ምንም አይነት እርምጃ የመውሰድ ፍላጎት አለማሳየታቸው፤ ማንም ግለሰብ በቅርብ ካለው የመንግስት አመራር ማረጋገጥ እንደሚችለው ሰሞኑን በነበሩ የካድሪ ውይይቶች ላይ "ፋኖ በቅርቡ ዘረፋ ይጀምራል ዘረፋው እንዲቆም ከፈለጋችሁ ከእኛ ጋር እበሩ የሚል ጫና ማህበረሰቡ ላይ ማሳደር አለብን" የሚል አጀንዳ ለውይይት ማቅረባቸው፤ ፋኖ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች መሰል ዝርፊያዎች አለመኖራቸው፤ ሁሉም ዝርፊያወች ከመንግስት ሐይል ካፕ ቅርብ እርቀት መፈፀማቸው፤ ስለ ጉዳዩ ሊያመለከቱ ለሔዱ አካላት እኛን ከደገፋችሁ ዝርፊያውን እናስቁምላችኋለን ካልሆነ ግን ፋኖ ያድናችሁ የሚል መልስ መስጠታቸው፣ ወዘተ. ዘረፋው መንግስት መር መሆኑን እና ዘራፊዎችን መንግስት እንደሚያውቃቸው ማሳያዎች ናቸው።
ህዝብ እንዲገነዘበው እና ለወደፊቱም እንዲያጤነው የምንፈልገው ጉዳይ በኮማንድ ፖስት በሚመራ ከተማ ውስጥ፣የፋኖ ሐይሎች በከተማው በሌሉበት ሁኔታ፣ያለ ምንም ውጊያ መትረጊስን ጨምሮ ሌሎቸ የቡድን መሳሪያዎችን ተጠቅሞ የሚዘርፍ ሐይል እራሱ የመንግስት ታጣቂ ወይም መንግስት ያቋቋመው ሐይል እነደሆነ ነው።
ዘረፋው በመንግስት ታጣቂዎች እና በከተማው ስቪል አስተዳደሮች በጥምረት የሚፈፀም ሲሆን በዋናነት ሁለት አብይት አላማዎች እንዳለው ከውስጥ መረጃዎች ለማረጋገጥ ችለናል። አንደኛው አላማቸው ዘረፋ የሚፈፅመው ፋኖ ነው በማለት ፋኖን ከማህበረሰቡ ጋር ማቃቃር ሲሆን ሁለተኛው የመንግስት ታጣቂዎች በደንብ እንዲያገለግሉ ማማለያ እንደሆነ ማረጋገጥ ችለናል።
በመሆኑም የአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ የሚከተለውን መልዕክት እና ማስጠንቀቂያ ለሚመለከታቸው አካላት ያስተላልፋል፦
1: የተከበርከው የጎንደር አማራ እኛ የአማራ ፋኖዎች የተደላደለ ኑሯችን ትተን በዱር በገደል እንደንኖር ያስገደደን የአማራ ህዝብ ስቃይ እና እንግልት ደካማ ጎናችን በመሆኑ እና ይህ ግፍና መከራ ያጎበጠው ህዝብ ሳይንገላታ ስርዓቱን የምናፈርስበትን ዘዴ ከከተማ ውጭ በሚደረግ ትግለ ነው ብለን ስለምናምን እንጅ የዞን ከተሞችን አይደለም የክልል ከተሞች ላይ ገብተን መዋጋት አቅሙ እንደማይገደን ከእናንተ የተደበቀ ሐቅ አይደለም። እኛ ለአጭር ሰዓት ለተልዕኮ ከተማ በምንገባበት ወቅት እንኳን በሰበባስባቡ የሚገደለውን ንፁሐን እናንተ ታውቁታላችሁ። በዚህም ምክንያት የቤት ስራችን እስክንጨርስ ድረስ ዱሩ ቤቴ ብለን ከወጣን ሰነባብተናል። ሐቁ ይህ ሆኖ እያለ በግድ ካልደገፋችሁኝ በሚል የበቀል ስሜት በመነሳሳት መንግስት ያሰማራው ዘራፊ ቡድን በፋኖ ስም ተደራጅቶ እንዲዘርፋችሁ መደረጉ ስንስማ በህዝባችን ጊዜና ዘመን የመይሽረው መከራ የቆሰለው ልባችን ክፉኛ መርቅዟል።
ይሁን እንጅ ሁላችንም በየ እድሜ ደረጃችን ልጅነታችን፣ጉልምስናችን እና የመጦሪያ ዘመናችን እያባከን በዱር በገደል የምንሰቃየው ይህን በበቀል ተወልዶ በበቀል ያደገ ስርዓት ግብዓተ መሬቱን ለመፈፀም ነውና እንባችሁ የሚታበስበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም። በመሆኑም ይህ እየተደረገባችሁ ያለው ዘረፋም ሆነ የቆየው ስርዓታዊ በደል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት የሚያገኘው ከስርዓቱ መቀበር ጋር በመሆኑ ለምናደርገው ዘርፈ ብዙ የሆነ የህልውና ተጋድሎም እንደተለመደው ከጎናችን እንድትሆኑ የዘወትር መልዕክታችን ነው።
2: በጥቅም ተሸውዳችሁም ሆነ ግላዊ ፍላጎታችሁ አስገድዷችሁ የምትዘርፉ የመንግስት ታጣቂዎች ከህዝብ ሰርቆ ማምለጥ እንመደማይቻል ሽንት ቤት ሲሔዱ ሳይቀር ከምትጠብቋቸው የቅርብ አለቆቻችሁ በላይ ሊያስተምራችሁ የሚችል ምሳሌ የለማ እና ብትማሩ መልካም ነበር። የምትጠብቁት አመራር በሙሉ ከአየር መንገድ ወደ ቢሮ ለመግባት በብረት ለበስ ታንክ ተሸከርካሪ የሚጓዘው እና በእናንተ እና በሌሎች ኋይሎች የሚጠበቀው የአባቱን ገዳይ ፈርቶ ሳይሆን ትናት እንደ እናንተ የዘረፈው እና የበደለው ህዝብ እንደሚበቀለው ስለሚያውቅ ነው። ይህንን እውነት ከአናንተ ውጭ የቀረበ የሚያረጋግጠው የለም። ይህ ወቅት ለእናንተ የንስሐ ጊዜ ነው።አውቃችሁም ሆነ ሳታውቁ የበደላችሁትን የአማራ ህዝብ የምትክሱበት የመጨረሻው ሰዓት ላይ ናችሁ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚህ እኩይ አላማ የምትቀጥሉ ከሆነ ግን የእናንተም እጣ ፋንታ ከአለቆቻችሁ የከፋ እንደሚሆን ማስታወስ እንወዳለን።
6.4K views12:55