2022-07-08 21:25:47
የኢትዮጵያ እና የጂቡቲ መሪዎች በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔ አሳለፉ
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ እና የጂቡቲው ፕሬዝደንት ክቡር ኢስማኤል ዑማር ጌሌ ቀደም ብለው ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ በኢፌዲሪ ፋይናንስ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ የሚመራ የልዑካን ቡድን ከሰኔ 29-30 ቀን 2014ዓ.ም ድረስ በጂቡቲ ይፋዊ ጉብኝት አካሂዷል፡፡
የልዑካን ቡድኑ ክቡር ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑማር ጌሌን አግኝቶ የክቡር ጠ/ሚኒስትራችንን መልዕክት ባስተላለፈበት ወቅት በጋራ ማንነት የተጋመደው እና ልዩ የሆነው የሁለቱ አገራት ሁሉን-አቀፍ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት (Unique and Comprehensive Strategic Cooperation) ከመቼውም ጊዜ በላይ እያደገ የመጣ መሆኑን አውስቷል፡፡
በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ትስስር ብቻ ከ10 ቢሊየን ዶላር በላይ በጋራ ኢንቨስት ያደረጉት ሁለቱ ወዳጅ አገራት ቀደም ብሎ በኮቪድ፣ ቀጥሎም በሌሎች የውጭ እና የውስጥ ሁኔታዎች ሲቆራረጥ የቆየውን የሁለትዮሽ ውይይት ከቀድሞው የበለጠ በማጠናከር የጋራ የምጣኔ-ሃብት ትስስሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ለመለወጥ በሁለቱም በኩል የታየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
በመሆኑም የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ፣ ተምሳሌታዊና ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአገራት መሪዎች ቀደም ብለው በተወያዩት አግባብ መሰረት ሶስት ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ተደርሷል።
የአትክልት እና ፍራፍሬ የዋጋ ተመንን በተመለከተ የሁለቱ አገራት መንግስታት በሚያቋቁሙት የጋራ ኮሚቴ አማካኝነት የጂቡቲን ነባራዊ አሁናዊ ገበያ እና የሰፊውን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ የዋጋ ማሻሻያ እስከሚደረግ ድረስ ለጂቡቲ ብቻ ቀድሞ በነበረው ዋጋ እንዲቀጥል ተወስኗል።
በተጨማሪም ለ40 ዓመታት ሲሰራበት የቆየው ወደ ጂቡቲ የሚላከውን የጫት ምርት ታሪፍ ከፍ ለማድረግ ቀደም ብለው መሪዎቹ በተስማሙት መሰረት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን የጂቡቲ አስመጪዎች የጫት ምርት የውጪ ሽያጭ ውል ምዝገባ መፈፀም ሳይጠበቅባቸው ምርቱን ማስገባት እንዲችሉ እንዲሁም የባህር አገልግሎት ክፍያዎች (Maritime Charges) በሁለቱ አገራት መንግስታት የሚመለከታችው አካላት በጋራ ምክክር ተደርጎበት ውሳኔ ላይ እስኪደርስ ማስተካከያው ሳይደረግ በነበረው ዋጋ እንዲቀጥል ከስምምነት ተደርሷል።
የልዑካን ቡድኑ በክቡር ፕሬዝደንቱ ቤተ-መንግስት በመገኘት የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት ከማስተላለፉ በፊት የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የንግድ እና ቱሪዝም ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ ዋርሳማ ዲሬህ፣
የንግድ ም/ቤት ሊቀ-መንበር ክቡር አቶ ዮሱፍ ሙሳ ደዋሌህ እንዲሁም የጂቡቲ ወደቦች እና ነጻ የንግድ ቀጠና ባለስልጣን ሊቀ-መንበር ክቡር አቶ አቡበከር ዑመር ሐዲን አግኝቶ በሁለቱ አገራት መካከል ስላለው የዲፕሎማሲ፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ወደብ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
የልዑካን ቡድኑ በቆይታው ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የተጣራ እና ድፍድፍ የምግብ ዘይት ምርቶች ዋነኛ አቅራቢ ድርጅት Golden Africa ተገኝቶ ጉብኝት እንዲሁም ከድርጅቱ ኃላፊዎች ጋር ውይይቶችን አድርጓል።
1.5K views18:25