Get Mystery Box with random crypto!

'መረጃ ያላሟላ ደንበኛ የባንኩን አገልግሎት አያገኝም በሚል የሚሰራጨው መረጃ መሰረተ ቢስ ነው' ን | ኩሩ ሚዲያ ኔትዎርክ - Kuru Media Network

"መረጃ ያላሟላ ደንበኛ የባንኩን አገልግሎት አያገኝም በሚል የሚሰራጨው መረጃ መሰረተ ቢስ ነው" ንግድ ባንክ

በኢትዮጵያ ያሉ ኹሉም ባንኮች ነሐሴ 21/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት የደንበኞቻቸውን ወቅታዊ መረጃ እንዲሟሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

ትዕዛዙን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞቹን መረጃ የማሟላት ሥራ እያከናወነ እንደኾነ አስታውቋል፡፡ ምንም እንኳን ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ቢጠናቀቅም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለው የደንበኞች ብዛት አንጻር እስከ ዛሬ ማራዘሙን የባንኩ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር የአብሥራ ከበደ አብራርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምዝገባው ዛሬ የሚጠናቀቅ መኾኑን ተከትሎ መረጃ ያላሟላ ደንበኛ የባንኩን አገልግሎት አያገኝም በሚል የውዥንብር ወሬ እየተነዛ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም መሰረተ ቢስ መኾኑን ነው አቶ የአብሥራ የተናገሩት፡፡

የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ እንዳሉት መረጃ ያላሟላ ደንበኛ ማግኘት የማይችለው ኤሌክትሮኒክስ የባንክ አገልግሎቶችን ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ተጨማሪ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉባቸውን የባንኩን የሞባይል ባንኪንግ፣ የኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ሲቢኢ ብር እና የኤ ቲ ኤም አገልግሎቶች ማግኘት አይችሉም፡፡ ይሁን እንጂ በቅርንጫፍ በአካል በመገኘት ማንኛውንም አገልግሎት ማግኘት ይቻላሉ ብሏል ባንኩ፡፡

ደንበኞች በባንኩ በማንኛውም ጊዜ አገልግሎት ለማግኘት ሲያቀኑ ወቅታዊ መረጃዎቻቸውን እንዲያሟሉ በማድረግ ኤሌክትሮኒክስ የአገልግሎት አማራጮችን እንዲጠቀሙ ይደረጋል ብለዋል አቶ የአብሥራ፡፡

ሙሉ የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ወቅታዊ የደንበኛ መረጃን ማሟላት የግድ መኾኑን ያነሱት አቶ የአብሥራ መጨናነቅ እና ያለ አግባብ መሰለፍ አስፈላጊ እንዳልኾነ አስገንዝበዋል፡፡