Get Mystery Box with random crypto!

'ፊት'!!! ያፈቀርኩ እለት ካሊድ (ሀበሺስታን) 2 የምንታወቀው በምንለብሰው ቲሸ | ሀበሻዊ ጥበባት

"ፊት"!!! ያፈቀርኩ እለት




ካሊድ (ሀበሺስታን)



2


የምንታወቀው በምንለብሰው ቲሸርት አይደለም። እኔ የምታወቀው << ያ እንደ ሽማግሌ የሚያደርገው ልጅ>> በሚለው ነው። በቲሸርት የማልታወቅበት ምክንያት ቲሸርት ስለምሸያይር ነበር ሀብታም እንደነበርን በዚህ ተረዱኝ የልብስ ሀብታም ማለቴ ነው።

እንደውም አንድ ጊዜ ነጭ ቲሸርት ሆና እላይዋ ላይ በፊት ለፊት በትልቁ ቀይ የልብ ቅርፅ ምስል እና ከስሩ ''I LOVE MAMA"" የሚል ቲሸርት ከውጭ መጥቶልኝ ሰኞ ቀን ለብሼው ሄድኩ። የሰው ሁሉ አይን ሲያርፍብኝ ልቤ ጮቤ እረገጠች። ነገር ግን ፅሁፉን ያነበበው ጥቂቱ ስለነበር በቀዯ ልብ ቅርፅ ምክንያት ብዙ ተወራብኝ ፤ከተወሩት መሀል:-

<<አፍቅሮ ነው እኮ፣ በዚህ እድሜው ምነው ተንቀዠቀዠ፣ እዮኝ እዮኝ አበዛ>> ከዚህ መሀል ያምራል ያለኝ መኖሩን እጠራጠራለሁ።


የክፍሉ ጭምት ተማሪ ነኝ። አላወራም ግን፤ ፈዛዛ አይደለሁም። ሁሉም ተማሪ የሚያደርገው ነገር ያስገርመኝ ነበር እናም ከእራሴ ጋር እያወራሁ በሰው ሁኔታ እስቅ ነበር ። ለምሳሌ ማትስ መምህራችን መነፅር የሚያደርጉ አጭር መምህር ነበሩ። አጥረው ቦርዱ ላይ ከግማሽ ዝቅ በሚለው ቦታ ላይ ከማስተማራቸው ይልቅ ከአፍንጫቸው ዝቅ አድርገው በሚያደርጉት መነፅር መፅሀፋቸውን ከላይ በአይናቸው እኛን የሚያዮን ነገር ያስገርመኝ ነበር።

አንድ ጊዜ ከክፍሉ ተማሪ እያስወጡ እንዲያስረዳ ሲጠይቁ እኔን እንዳይጠይቁኝ ስፀልይ ፀሎቴ አልሰመረ ኖሯል፤ <<አንተ ጋግርታም ና ውጣ እስኪ አስረዳ>> አሉኝ። ወጣሁ ቾክ ያዝኩ የገረመኝ ልክ እንደሚያስረዳ ሰው ትልቅ ቾክ መያዜ። ለነገሩ ከተሳካልኝ ለመስረቅ ነበር ምንም ለማልፅፍበት ለምን ቾክ መውሰድ እንደሚያስደስተኝ አይገባኝም።

ቦርዱ ላይ የተፃፉት ቁጥሮች አፈጠጡብኝ። እጄን ቦርዱ ላይ ሰቅዬ መልሱ ከሰማይ ይወርድ ይመስል መጠባበቅ ያዝኩ። ቄሱም ዝም መፅሀፉም ዝም ሆነ ነገሩ። መምህሩ ዝም አሉኝ። አሁን ማን ይሙት ካላጡት ተማሪ እኔን ማስወጣት ምን ይሉታል! በቃ እኔ ችሎታዬ አንደኛ መውጣት ብቻ ነው። ለምን አይተውኝም እያልኩ በሀሳብ ስሰምጥ <<ና ተቀመጥ ሰዐት አታቃጥል ያቃጥልህ የሚያቃጥል ነገር>> አሉኝ ። ወደ እኔ እየመጡ እንዳልመታ ሸሸት ብዬ ወንበሬ ላይ ተቀመጥኩ÷ ደንግጬ ቾኩን የት እንደጣልኩትም አላስታውስም። ቀና ብዬ ቦርዱን ስመለከት የእጄ ላብ ዱካ መስሎ ታግሟል።


ጐበዝ ተማሪ ከሚባሉት ጐራ አልመደብም። ወይም እዮኝ እዮኝ ባይ ተማሪም አይደለሁ። በፈተና ወቅትም ከሚኮርጁት እንዝላል ተማሪዎችም አልመደብም። የግሩፕ ስራ ሲሰጥም የበኩሌን አደርጋለሁ። ብቻ ግን በፈተና ወቅት ከማንም በላይ ጥሩ ውጤት የማመጣ እኔ ነበርኩ ።

ከክፍላችንም አንደኛ ወይ ሁለተኛ ደረጃ ለመውጣት የሚገዳደረኝ አልነበረም። አስማት ሊመስላችሁ ይችላል ግን እኔም እንዴት እንደሆነ አላውቅም።

የምቀመጠው ከክፍሉ መግቢያ በር አጠገብ ነበር። እዚህ ቦታ ላይ በምርጫዬ ባልቀመጥም ወድጄው የምቀመጥበት ቦታ ነው። የወደድኩት ደግሞ ክፍል ውስጥ ብሆንም ካለማንም ከልካይ ውጪ ያለውን ነገር መኮምኮሜ ነው መምህሩ ሲያስተምር ልቤም አይኔም ውጩን ያማትራል።

ከኋላዬ አብዱልሀኪም አለ፤ አብዱልሀኪም እናቱም አባቱም መመህር ሲሆኑ እሱ ግን የአቦጊዳ ሽፍታ ነበር። እውቀት በዞረበት ያልዞረ እንደውም ማጋነን ካልሆነ ደደብ ከማለት አንተ አብዱል ሀኪም ነገር ነህ ብባል እበሳጫለሁ።

ደደብነት እራሱ አብዱልሀኪምን ደደብ ብሎ ነው የሚሰድበው። ታዲያ ድድብናው ትምህርት ላይ ነው እንጂ እሳት የላሰ ሌባ ነው!! እንደውም አባቱ ብር እየቆጠሩ ሲያዮት ፈርተው ወደ ኪሳቸው ይመልሱ ነበር። ሁሌም ማታ ይገረፋል ምክንያቱም ሁሌም ይሰርቃል። አባቱ ከውጭ እንደመጡ ቅድሚያ ስራቸው መታጠብ ወይ መመገብ አይደለም <<ስማ አብዱልሀኪም ያንን የቆዳ አለንጋ አምጣ >>ይባላል ባመጣው አለንጋ ይገረፋል።

ታዲያ ሁልጊዜም ከመገረፉ የተነሳ አባቱ አንድ አንድ ጊዜ እንደገቡ ይገርፉታል። <<አባዬ ምን አደርግኩ>> ይላቸዋል <<አልሰረቅክም እንዴ>> ይሉታል << አዎ>> ይላል <<እንዴት ሌላ ዘዴ አመጣሽ ማለት ነው>> ብለው ይገርፉታል። አባቱን ከሚሰርቀው በላይ የሚያናድዳቸው ታዲያ ሲገረፍ ድምፅ እውጥቶ አለማልቀሱ አይደለም አንዲት የእንባ ጠብታ አለመውጣቷ ነው። የሆነ ቀን ለምን አታለቅስም ብለው እንደገረፉት ነግሮኛል። የሆነ ቀን ቤታቸው ሄጄ ሲገረፍ ደረስኩ። እስኪጨርስ ቆሜ እየጠበቅኩት አለማልቀሱ አስገርሞኝ አንገቴን አስገብቼ ስመለከት ፊት ለፊት ከተከፈተው ቴሌቪዥናቸው ላይ የህንድ ፊልም እያየ ስመለከተው <<እኚህ ሰውዬ ፀበል እያጠመቁት ነው ወይስ መሳጅ እያደረግኩት>> ብዬ ግራ ገብቶኝ ነበር።

ከዚህ በላይ ግራ ያጋባኝ ተገርፎ ሲጨርስ <<ሀበሽ እንሂድ>> ብሎኝ ምንም እንዳልተፈጠረ ይስቃል። <<ምን ሆነሀል የምትስቅ ቀልድ ሲነግሩህ የቆየህ ነው እኮ የምትመስል>> ስለው ቆም ብሎ ኪሱን ዳብሶ የወረቀቷን አንድ ብር አውጥቶ አሳየኝ። <<ምንድን ነው>> ስለው <<እየገረፈኝ ሲዘናጋ ሰረቅኩት>> ብሎኝ ሳይጨርስ አባቱ ና አንተ ሌባ እያሉ ወደ እኛ ሲመጡ ተመለከትኩ። ዞር ስል አብዱልሀኪም አጠገቤ የለም መኪና እራሱ እንደሱ መሮጡን የተጠራጠርኩት የዛን ቀን ነው። ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ነውና እኔንም እንዳይመቱኝ እግሬ አውጭኝ አልኩ ብዙ ተከትለውን ሲደክማቸው ቆይ ማታ ትመጣ የለ ብለው ዝተው ተመለሱ።




ይቀጥላል…………





@Habeshistan