Get Mystery Box with random crypto!

'ፊት'!!! ያፈቀርኩ እለት!!! ካሊድ (ሀበሺስታን) 3 አንድ ቀን ልክ በቁም ነገር | ሀበሻዊ ጥበባት

"ፊት"!!! ያፈቀርኩ እለት!!!




ካሊድ (ሀበሺስታን)


3

አንድ ቀን ልክ በቁም ነገር እንደሚማር እንደሚገባው ሰው በጠዋቱ መጥቶ ክፍል ውስጥ ገባ ።ስንማር ቆይተን በእረፍት ሰዐት ካለ ወትሮው <<ሀበሽ ና ፈልጌህ ነው>> ብሎ ከዘላለም ነጥሎ ይዞኝ ሄደ።

ብዙም አልገረመኝም። ይዞኝ ተማሪው ብዙም ብር ያለው ስለሌለ መምህራን ብቻ ወደሚጠቀሙበት ሻይ ክበብ ሄደ ።

ይሄ ክበብ ከሚገርመኝ የሚጠቀሙበት መምህራን ስሙ ግን የተማሪዎች ክበብ መባሉ ነው። <<ምን ልናደርግ ነው እዚህ የመጣነው?>> ስለው ዝም ብሎኝ መንገዳችንን ቀጠልን። ደርሰን ማን በላ ማን ቀረ እንደሚቆጣጠር ሰው ረጅም ደቂቃ ቆምን። መጨረሻውን ለማየት እኔም ምንም ሳልለው ቆሜ እየጠበቅኩት ከሚኒ ሚዲያ የጥላሁንን ውብ አይናማ ዘፈን ጆሮ በሚቆረቁር ማይክ ይሰማናል። ብዙም ልብ ብሎ የሚሰማው ተማሪ ግን የለም።
<<ውብ አይናማ ከእግር እስከ እራሷ
ውብ አይናማ…………>>


ትንሽ ቆይቶ <<ስማ ሀበሽ>> አለ ዙሪያ ገባውን በአይኑ እያማተረ። <<እኔ እዛ ጋር እጠብቅሀለሁ በዚህ ሳንቡሳ ገዝተህ ይዘህ ና>> ብሎ ከእጁ ሶስት የወረቀት ብር እጄ ላይ አስቀመጠልኝ።በጣም ደነገጥኩ የደነገጥኩ ሰርቆ እንደሚያመጣው ስለማውቅ ነው።

ፈራ ተባ እያልኩ ክበብ ገብቼ የሰጠኝን ሶስት ብር ከእጄ አውጥቼ ለአስተናጋጇ ሰጠኋት። ሄጄ ገዛሁ ማንም እንዳያየኝ እና ዘይቱ ልብሴን እንዳይነካኝ እየተጠነቀቅኩ ያለኝ ቦታ ደርሼ ሳንቡሳውን አቀበልኩትት እና የተመለሰልኝን ሀምሳ ሳንቲም <<እንካ>> ስለው ሳንቡሳውን ተቀብሎ ሳንቲሙን ቆይ ያዘው ብሎ ከመቀመጫው ተነስቶ መሄድ ጀመርን። ከላይ ያለውን ቅርፊት ሰጥቶኝ ሌላውን በላው።

የእረፍት ሰዐት አልቆ ወደ ክፍል ተመለስን። ከተወሰኑ ደቂቃ በኋላ ተጠራን እናቱ ነበረች። ሰረቁ ተብሎ መምህሩ ሁላ ጥርሱን ነከሰብን። << እኔ አልሰረቅኩም እሱ ነው የገዛው>> ሲል ድርቅ አልኩ። ካላመናችሁ ፈትሹት መልሱም ኪሱ ውስጥ ነው ብሎ አስፈተሸኝ። ሀምሳ ሳንቲሟ በመገኘቷ ሌባ ሲሉኝ መምህራን የአብዱልሀኪም እናት ግን <<ተው እሱ አይሰርቅም የእኔው ልጅ ነው ሌባ ቆይ ማታ እንገናኝ>> ብላ ዝታበት ሄደች። ከዚያ ቀን በኋላ ሳንቡሳ ሳይ አብዱልሀኪም ነው የሚመጣብኝ ሳንቡሳ እና አብዱልሀኪም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ነው የሚመስሉኝ።


ከእኔ እና ዘላለም ጐን ተግባር የሚባል ልጅ ይቀመጣል። ተግባርና ንፅህና ደግሞ የማይቀራረቡ ፀበኞች እንደሆኑ የምታውቁት ተግባርን ፀጐሩን በአምስት ጣቱ ሲያክ ሲያክ ከማለት ይልቅ ሲቆፍር ይቀርባል ከተመለከታችሁ ነው።የዮኒፎርሙ የሸሚዝ እጅጌ ንፍጡን ስለሚጠርግበት ሲደርቅ ያብለጨልጫል፤ አንድ ጊዜ እንደውም በእሱ እጅጌ በጠረገው እና ሲደርቅ በሚያብለጨልጨው ልብሱ ምክንያት አንፀባርቆብኝ አይኔን ለህመም ዳርጐኛል (ሲጋነን ነው)

ተግባር ምስኪን ልጅ ነበር። ከትምህርት ቤት ተለቀን ሁሉም ወደጨዋታው ሲያቀና እሱ ጫማ ተራ ገብቶ በትርፍ ሰዐቱ ሊስትሮ ይጠርጋል። ጫማ ይሰፋል። በገቢ ደረጃ ሐ ግብር ከፋይ ያህል ገቢ ያለው ብቸኛው የክፍላችን ተማሪ ነው። ከክፍላችን ውጪ ያለ አንድ ልጅ ብቻ ደረጃ ለ በመሆን በገቢ ደረጃ ይገዳደረዋል። ሳስበው የተግባር ህልም ሰርቶ ቢሊየነር መሆን ሳይሆን የሚበልጠውን ደረጃ ለ ልጅ መብለጥ ይመስለኛል።


ከእኛ በፊት ለፊት ያለ እረድፍ ላይ የሚቀመጥ መሀመድ የሚባል ልጅ ነው። መሀመድን ሁሉም የሚያውቀው በሁለት ነገር ነው አንደኛው በዛ እድሜው ፀጉሩ ገብቶ ገብቶ መሀል ላይ በመድረሱ ነው። መላጣ ሲባል ከሰማ ግን የትም ቢገባ መላጣ ያለውን ልጅ ከአቦ ሸማኔ በሚስተካከል እሩጫ አሳዶ ይዞ ዞማ ማለትም የእኔን የማለ ፀጉር ያለውን ልጅ መላጣ የሚያደርግ ጥፊ ይሰማል። አንድ አንድ ጊዜ ሳየው ትንሹ መለስ ዜናዊም ይመስለኝ ነበር። ከመለስ ጋር የሚያመሳስለው መላጠው ብቻ ነው። ልክ እንደፀጉሩ እውቀቱም መላጣ ነበር እንጥፍጣፊ እውቀት አልነበረውም።

ሁለተኛው በዮኒፎርም ሱሪው ኪሱ ሙሉ ይዞ በሚመጣው ቆሎ ነው። እረፍት ሰአት ስንወጣ አንድ ጥግ ሄዶ ቆሎ መፍጨት የዘወትር ተግባሩ ነበር። ግርም የሚለኝ <<ፈጣሪ ይሄን ልጅ በፀጉር እና በእውቀት ፋንታ ጥርስ መርቆ ነው እንዴ የሰጠው>> እላለሁ። ያልኩበት ምክንያት ሙሉ ከረጢት የሚያህል ኪስ የተወሸቀ ቆሎ በአስራ አምስት ደቂቃ ፈጭቶ አጠናቆ ምንም ሳይደክመው ሲመለስ ስለምመለከተው ነው። አድጌ ከረጅም ጊዜ በኋላ በስራ አለም የጠጠር መፍጫ ክሬቸር ስመለከት መጀመሪያ አዕምሮዬ ላይ የመጣው መሀመድ መላጣው ነበር።




ይቀጥላል……………





@Habeshistan