Get Mystery Box with random crypto!

'ፊት'!!! ያፈቀርኩ እለት ርዕሱ ቅኔ ነው!!! ክፍል 1 እንተዋወቅ ሀበሽ እባ | ሀበሻዊ ጥበባት

"ፊት"!!! ያፈቀርኩ እለት


ርዕሱ ቅኔ ነው!!!


ክፍል 1



እንተዋወቅ ሀበሽ እባላለሁ የስድስተኛ ቢ ክፍል ተማሪ ነኝ።ሲጋነን ወፍ ሳይንጫጫ፣ ለማኝ ሳይፀዳዳ እኔ የትምህርት ቤታችን አጥር የምትገኝ አንዲት ድንጋይ ላይ ተቀምጬ የትምህርት ቤቱ በር መከፈቱን የምጠባበቅ ተማሪ ነበርኩ። በአካባቢው ድቡልቡል እና ሸካራ ድንጋይ በበዛበት ይህቺ ጥቁር ጠፍጣፋ ድንጋይ ማን እንዳመጣት አላውቅም። ከሁሉም የሚገርመኝ ለሀበሽ ተብላ ከሰማይ የወረደች ይመስል ከእኔ ውጪ ማንም አይቀመጥባትም።

አንድ ቀን እንደለመድኩት በጠዋት በሌሊት ብለው ይቀላል ወደ ትምህርት ቤታችን ገሰገስኩ። ልጅ እና ፊት አይበርደውም እንዲሉት ሀሩር የሆነ ያህል ነፋሱን እየቀዘፍኩት ስሄድ እንዲች ብሎ አይበርደኝም ነበር።ትምህርት ቤታችን በር ጋር ስደርስ እና የትምህርት ቤታችን ጥበቃ መብረቅ እንደመታው ሰው ድርቅ አሉ። ምን አስደነገጣቸው ብዬ ስፈላሰም ብድግ ብለው <<አሀ ጌታው ፍርድ ቤት ጉዳይ እንዳለው ከሳሽ በጠዋት ለመምጣት ማንም እይቀድምህም አይደል! ይሄው ወንበርህ>> አለኝ ድንኳን የሚያህለውን ፎጣውን እየጐተተ ወደ ሌላ ድንጋይ እየተሸጋገረ።


ለካ የደነገጠ ድንጋዬ ላይ ስለተቀመጠ እና ስለመጣሁበት ነበር። ጥበቃው ጥርሱን እየፋቀ አላፊ አግዳሚውን የተቀደደች ኮፍያውን ቀና እያደረገ ቁጭ ብድግ እያለ ሰላም ይላል። ዞር ሲሉ <<ሰው መስሎሀል>> ይለኛል። አልሰማውም.... እንደማልሰማው ሲያውቅ <<ጋግርታም ምን ትለጐማለህ አታወራም እንዴ?>> ብሎ እየተበሰጫጨ ገባ። ምን እንዳበሳጨው ባይገባኝም ሀሜቱን ባለመጋራቴ መሰለኝ። ወይም የድንጋይ መቀመጫ እና የእናት ሞት እየቆየ ይቆረቁራል እንዲሉት የተቀመጠበት ድንጋይ ቆርቁሮት ይሆናል።

ፀጉሬን ሙልጭ አድርጌ በምላጭ የምላጭ፤ እየዘመንኩ ሄጄ በማሽን መስተካከል የጀመርኩ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው። እንደውም ከቤተሰብ መላምት ተነስቼ ስገምት ፀጉሬ አሁን ዞማ የሆነው ዞማ ስል የሚቃወሙ ቢኖሩም እደግመዋለሁ ዞማ የሆነው እስከዛ እድሜዬ በማሽን ስላልተነካሁ ነው ይባላል አሉ ነው አሉባልታ ከግነት ጋር ተቀላቅሎበት ቂ ቂ ቂ ቂ ።


በንፅህናዬ አልደራደርም። ጥንቅቅ ብዮ ኖርማል ፀጉሬን ተጣጥቤ ቅባት ተቀብቼ ነው ከቤቴ የምወጣው ። የግል ንፅህና ጠብቁ እየተባለ ሲነዛ ምሳሌ ነበርኩ። አንድ ጊዜ እንደውም የጥፍር ንፅህና ተብሎ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የዚያን ሁሉ ተማሪ ጥፍር እየተመለከቱ ግማሹን << ምን ያዝረከርክሀል>> እያሉ ሲማቱ የእኔ ተራ ደርሶ ጥፍሬን ሲያዮ ቀና ብለው ፊቴን ተመለከቱና <<ማን ነው ስምህ>> አሉኝ ። <<ሀበሽ>> አልኩ <<ጥፍርህን ወደ ውስጥ በጣም ስለቆረጥከው ትንሽ አሳድገው>> ብለውኛል። እኔን የገረመኝ ግን ምን ያህል ስራ ቢፈቱ ነው ጥፍሩን ሲበላ የሚውል ውሪ ሁላ ጥፍር የሚያዮ የሚለው ነበር ወይስ ደሞዛቸው ጥፍር ከማየት ጋር ተያያዥነት አለው?


የምለብሰው የደንብ ልብስ ሸሚዙ ወደ ቀይ የሚያደላ እና ብሉ ብላክ ሱሪ ዮኒፎርሜ ባያምርብኝም አያስጠላብኝም። ረጅም ስለነበርኩ ሱሪውን እንደ ረጅም ቁምጣ ነበር የምጠቀመው ብል ግነት አይሆንም። ሸሚዙም ቢሆን ለጉራ ወደ ክንዴ ሰብሰብ ያደረግኩት እንጂ ያጠረኝ አይመስልም ። እንደዚህ አጥሮኝ ሌላ የማላሰፋበት ምክንያት አይገባኝም የእኔስ ይሁን ቤተሰቦቼ ግን አያዮኝም ነበር ወይስ አሰፉልኝ ያላለ ቢመቸው ነው ብለው ይሆን?

የምለብሰው የደንብ ልብስ ሸሚዙ ክፍት ስለነበር እንደ ጃኬት እጠቀመዋለሁ። ቲሸርት የፈለግነውን እንለብስ ስለነበር ልብሶቼ ሁሉ ቲሸርት ቢሆኑ እመኝ ነበር።ምክንያቱም ባለሀብትነታችንም ድህነታችንም የሚመዘነው እና የምናሳየው በቲሸርት ብቻ ነው። ቅዳሜ እና እሁድም ዮኒፎርሙን ሳያወልቅ ሰኞ የሚደርስባቸው ተማሪዎች ስለነበሩ የምንታወቅ የምንመዘን በቲሸርት ነበር።

ያ ቀይ ቲሸርት የሚለብሰው ሲባል ሁልጊዜም ከዮኒፎርሙ ውስጥ ቀይ ቲሸርት የሚለብሰው ዮሀንስ ነው። በሁሉም ተማሪ አዕምሮ የሚከሰት ሌላ ቀይ የሚለብስ ካለ ደግሞ ለመለያ አንድ ነገር አይጠፋም ያ ንፍጣሙ ይባላል የዛኔ ይፀድቃል።

ከተማሪው ብዙ ለየት የሚያደርጉኝ ነገሮች አሉ ከእነሱም አንዱ ፅዳት እና በዋናነት ዝምተኛነቴ ነው ። በሰፈሩ የምለይበት ደግሞ ከትልልቅ ሰው ጋር ብቻ ነበር የምግባባ። እኩዮቼ ጋር ብውልም የሚጫወቱት ጨዋታ ያስገርመኝ ነበር ምኑ ደስ ብሏቸው ነው እል ነበር። እግር ኳስ እንጫወት ብለው እስከ ሜዳ ሲሯሯጡ እኔ ቀስ ብዬ ስለምሄድ ዘግይቼ ነበር የሚጫወቱበት ሜዳ ላይ የምደርስ። ደርሼም ራቅ ብዬ ከሜዳ ውጪ ስለምቀመጥ አጠገቤ የልብስ መዐት ተደርድሮ ነበር የሚታይ የዚያ ሁሉ ልብስ ጠባቂ ነበርኩ።




ይቀጥላል……………




@Habeshistan