Get Mystery Box with random crypto!

ኢትዮጵያ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት 2 ቢሊየን ዶላር ብድር ለማግኘት መጠየቋ ተዘገበ ኢትዮጵያ ከዓ | FastMereja.com

ኢትዮጵያ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት 2 ቢሊየን ዶላር ብድር ለማግኘት መጠየቋ ተዘገበ

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ቢያንስ የ2 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ከተቋሙ ጋር እየተነጋገረች መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ።

በጦርነት እና በዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የተዳከመውን ምጣኔ ሃብቷን ለማነቃቃት ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ ከፍተኛ መጠን ያለውን ብድር ለማግኘት እየሞከረች መሆኑን የዜና ወኪሉ ጉዳዩን የሚያውቁ አራት ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

ባለፉት ሳምንታት ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሥልጣናት በአዲስ አበባ እና ዋሽንግተን ውስጥ ውይይት ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል።

አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ በሚችለው ድጋፍ ዙሪያ አስፈላጊውን “ቴክኒካዊ ሥራ ለማከናወን” የድርጅቱ ባለሥልጣናት አዲስ አበባ ውስጥ ከአንድ ሳምንት በላይ መቆየታቸውን ብሉምበርግ ዘግቦ ነበር።

ይህ የተቋሙ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ያደርጉት ቆይታ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት ካበቃ ከወራት በኋላ ሲሆን፣ አገሪቱም በግጭት እና በድርቅ የተጎዳውን ምጣኔ ሃብቷን እንዲያገግም ለማድረግ ጥረት በጀመረችበት ወቅት ነው።

ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ አይኤምኤፍን ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር የነበራት ግንኙነት ተቀዛቅዞ መቆየቱ ይታወቃል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ከኢትዮጵያ የቀረበለትን ከፍተኛ መጠን ያለውን የብድር ጥያቄን በተመለከተ አገሪቱ ካለባት ዕዳ አንጻር እየገመገመው መሆኑን፣ ንግግሩ በአይኤምኤፍ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ብቻ እየተካሄደ በመሆኑ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ንግግሩ አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ የጋራ ስብሰባ በሚደረግበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከተቋሙ ጋር የምታደርገው ንግግር አሁንም ዋሽንግትን ውስጥ በመካሄድ ላይ ነው።

“ኢትዮጵያ ከተቋሙ የምታገኘው ድጋፍን በተመለከተ እስካሁን የተወሰነ ነገር የለም፤ ሁለቱም ወገኖች የብድር ዘላቂነት ላይ የበኩላቸውን እየሰሩ ይገኛሉ” ብሏል አንድ የሮይተርስ ምንጭ።

የዜና ወኪሉ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ከአይኤምኤፍ፣ ከኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ከብሔራዊ ባንክ ባለሥልጣናት ተጨማሪ መረጃ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኝም።

ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገራት አይኤምኤፍ ባለው አሰራር መሠረት ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምራ የዕዳ ማሸጋሸግ እንዲደረግላት ስትጠይቅ ቆይታለች። ነገር ግን በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነት ሂደቱን አወሳስቦት ቆይቷል።

በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መካከል ሲካሄድ የነበረው የድጋፍ፣ የብድር ስረዛ እና ሽግሽግ ንግግር በከፊል በትግራይ ሲካሄድ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ ምላሽ ሳያገኝ ቆይቶ ነበር።

ከአንድ ሳምንት በፊት የአይኤምኤፍ ልዑካን ወደ አዲስ አበባ በተጓዙበት ጊዜ የተቋሙ ቃል አቀባይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላት መጠየቋን አመልከተው ነበር።

“ሊሰጥ የሚችለው ድጋፍ አገሪቱ ለምታካሂደው አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ እና ምጣኔ ሀብቷን በማረጋጋት ለሰብአዊ ድጋፍ፣ ለሥራ ፈጠራ እና ለድህነት ቅነሳ የሚውል ይሆናል” ብለዋል ቃል አቀባዩ።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ቡድን፣ በአዲስ አበባ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ተቋሙ ለአገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ የሚሰጠውን ድጋፍ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር የተደረገው ውይይት አዎንታዊ ሂደት የታየበት መሆኑን ገልጾ ነበር።

“የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በአገር በቀል ማሻሻያው ድጋፍ ላይ ስለሚኖረው ሽፋን ባደረግነው ውይይት አዎንታዊ ሂደቶችን አይተናል” በማለት የአይኤምኤፍ ልዑክ ቡድን መሪ አልቫሮ ፒሪስ መናገራቸው ተጠቅሷል።

በመቶሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት እና በቢሊዮን ዶላሮች የሚያወጣ ውድመትን ያስከተለው የእርስ በርስ ጦርነት ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ተቋማት እና አገራት ታገኝ በነበረው ምጣኔ ሀብታዊ ድጋፍ ላይ ከፍተኛ ጫናን አስከትሎ ነበር።

ብሉምበርግ እንዳለው ኢትዮጵያ ጦርነቱ ያስከተለውን ውድመት መልሶ ለመገንባት እና የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመሸፈን አስፈላጊ ለሆኑ የገቢ ምርቶች ክፍያ ለመፈጸም ድጋፍ ያስፈልጋታል።

ጦርነቱ ካስከተለው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት ባሻገር በአፍሪካ ካሉ የመዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች መዳረሻ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን እና ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተነሳ ከዓለም ባንክ አንዲሁም ከአይኤምኤፍ የምታገኘውን ድጋፍ ገትቶት መቆየቱን ብሉምበርግ ዘግቧል።

በጦርነቱ እና በዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር የገጠማት ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ከመመዝገቡ በላይ እጥረትም ተከስቷል።

ጥቅምት መጨረሻ ላይ ደቡብ አፍሪካ ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈረመውን ዘላቂ ግጭትን የማቆም ስምምነትን ተከትሎ ጦርነቱ ቆሞ በሰሜን ኢትዮጵያ የሕዝቡን ሕይወት ወደ መደበኛው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው።

በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት 20 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፍልግ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በቅርቡ ተናግረዋል።

መረጃው የቢቢሲ አማርኛ ነው!!

@fastmereja