Get Mystery Box with random crypto!

1ኛ የጾሙ መጠሪያ ስያሜዎች ሀ.ዐቢይ ጾም የባሕርይ አምላክ በሆነዉ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ | የኤፍሬም እይታዎች (መ/ር)

1ኛ የጾሙ መጠሪያ ስያሜዎች

ሀ.ዐቢይ ጾም
የባሕርይ አምላክ በሆነዉ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ በመሆኑ ዐቢይ ወይም ታላቅ ጾም ይባላል፡፡

ለ.ጾመ ሁዳዴ

በጥንት ጊዜ ገባሮች ለባለ ርስት የሚያርሱት መሬት ሁዳዴ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ እኛም ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰብን የምንጾመው በመሆኑ ጾመ ሁዳዴ ተብሏል፡፡

ሐ.የካሳ ጾም

አዳምና ሔዋን ከገነት የተባረሩት ለውርደት ሞት ለሲዖል ባርነት የበቁት በመብል ምክንያት ነው፡፡ በመብል ምክንያት የሞተውን የሰው ልጅ ጌታችን በፈቃዱ በፈጸመው ጾም ካሰው፤ መንፈሳዊ ረሃብን በረሃቡ ካሰለት፡፡ ስለዚህም የካሳ ጾም ተባለ፡፡

መ.ጾመ ኢየሱስ

ጾመ ኢየሱስ ይባላል ይህም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ጾሞ ጹሙ ብሎ ስላዘዘን።

ሠ.የቀድሶተ ገዳም ጾም

ጌታችን ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በመጾም ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በብሕትውና መኖርን ቀድሶ የሰጠበት፣ የመጥምቁ ዮሐንስና የነቢዩ ኤልያስን ገዳማዊነት የባረከበት በመሆኑ የቀድሶተ ገዳም ጾም ተብሏል፡፡

ረ.የመዘጋጃ ጾም

ሕዝበ እሥራኤል የፋሲካውን በግ ከመመገባቸው በፊት ዝግጅት ያደርጉ ነበር፡፡ እኛም ትንሣኤን ከማክበራችን፣ ሥጋና ደሙን ከመቀበላችን በፊት በጾምና በጸሎት ዝግጅት የምናደርግበት በመሆኑ የመዘጋጃ ጾም ተብሏል፡፡

2ኛ የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜዎች

፩ኛ)የመጀመሪያው እሑድ(ሳምንት)፥ ዘወረደ (ሙሴኒ፣ ጾመ ሕርቃል) ይባላል፡፡  አምላክ ከሰማይ መውረዱን፣ ሰው መሆኑንና መስቀሉን ስለሚያወሳ ነው፡፡

፪ኛ. የሁለተኛው እሑድ፥ ቅድስት ይባላል፤ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ነው።

፫ኛ. የሦስተኛው እሑድ፥ ምኲራብ ይባላል፤ በዚህ ሰንበት ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ በምኲራብ ገብቶ ማስተማሩ ይነገራል፡፡

፬ኛ. ዐራተኛው እሑድ፥ መፃጉዕ ይባላል፤ ድውያንን መፈወሱን፣ ዕውራንን ማብራቱን፣ የሚያነሣ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡

፭. አምስተኛው እሑድ፥ ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሁኖ ያስተማረው ትምህርት፥ የዳግም ምጽአትን ነገር የሚያስታውስ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡

፮. ስድስተኛው እሑድ፥ ገብርኄር ይባላል፡፡ የጌታውን ብር ተቀብሎ ያተረፈበት፣ በጌታውም ፊት ምስጋናን ያገኘው ሰው ታሪክ ይዘመርበታል፡፡

፯. ሰባተኛው እሑድ፥ ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ በሌሊት ወደ ጌታ እየመጣ ይማር የነበረውን የኒቆዲሞስን ታሪክ የሚያስታውስ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡

፰. ስምንተኛው እሑድ፥ ሆሣዕና ነው፡፡ ጌታ በአሕያ ውርንጭላ ሆኖ ሆሣዕና በአርያም እየተባለ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡
 ከሠርክ ሆሣዕና እስከ ትንሣኤ ያለው ሰባት ቀን ሕማማት ይባላል፡፡- የጌታን መከራና ስቃይ እንዲሁም ሞት የምናስታውስበት ሳምንት ነው ፡፡

ጾሙን የበረከት ጾም ያድርግልን

#አተማሩበት Share ያድርጉ
የኤፍሬም እይታዎች