Get Mystery Box with random crypto!

ችግርህን ሳይሆን አምላክህን ተመልከት! ✞.......................✞............ | የኤፍሬም እይታዎች (መ/ር)

ችግርህን ሳይሆን አምላክህን ተመልከት!
✞.......................✞..................✞

#ከተራራ_ለገዘፈ_ችግርህ_እግዚአብሔር_መልስ_አለው፡፡
................................................
የተወደዳችሁ ወዳጆቼ እንደምን ከረማችሁ፡፡ሰሞኑን በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ በደረሰው ፈተና ብዙዎቻችን በሀዘን ተውጠን ነበር፡፡ ይኼንን ድርጊት በዘመናችን በመከሰቱ የተወለድንባትን ቀን እስከ መርገም ደርሰን ነበር፡፡ ችግሩ እንደ ተራራ ገዝፎ ሲያይ ጠላት ተዋህዶ ያበቃላት ቤ/ክንም የምትጠፋ መስሎት የደስታ ፉከራ ለመፎከር የደስታ ነጋሪትም ለመጎሰም ሲዘጋጅ አባቶቻችን እንዲህ አሉን " ሥስት ቀን ማቅ ልበሱ ጹሙ ጸልዩ" መልሳችን ከአምላክ ዘንድ ነው፡፡ በማለት ተናገሩን እኛም በአንድ ልብ ሆነን "የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ" ብለን እየዘመርን ወደ አምላካችን አለቀስን አምላካችንም መልስ ሰጠን፡፡ ፈጣን መልስ ለምን ያገኘን ይመስላችሗል ? መልሱ አጭር ነው፡፡ ችግራችን ሳይሆን አምላክችንን ስለተመለከትን ነው፡፡በጉልበታቸው የተመኩ የተሸነፉት እኛ ጉልበታችንን እግዚአብሔርን ስላደረግን ነው፡፡ የጠፋን የመሰላቸው በዝተን፤ የወደቅን የመሰልናቸው ቆመን የተመለከቱን ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታችን ራሳችንን ስላዋረድን ነው፡፡ ጠላት በአራት አቅጣጫ ሊውጠን ቢያሰፈስፍ ሰልፉ የእግዚአብሔር ከሆነ አሸናፊዎች እኛ ነን፡፡ ለዚህ ታሪክ በደንብ ማስረጃ የሚሆነን ቀጣዩ ምሳሌ ነው:-
"በአንድ ወቅት ለመውለድ ቀኗ የደረሰ አንዲት ነፍሰ ጡር አጋዘን ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ ከሚገኝ አንድ ምቹ ቦታ ጠጋ አለች ።ቦታው ዙሪያውን በሳር ተሸፍኗል። በቅርብ ርቀት እየተምዘገዘገ የሚፈስ ዥረት አለ ።
ያለችበት ቦታ ምቹና ነፃ ይመስላል ። በስቃይ የታጀበው ምጥ ድንገት ጀመራት ። ደመናው በቅፅበት መልኩን ቀይሮ የአካባቢውን ድባብ ለወጠው ። በመብረቅ የተመታው ደን በእሳት ተያያዘ ። ሰማዩ በነጎድጓዳማ መብረቅ እየታረሰ ነው ።

አጋዘኗ ወደ ግራ ስትመለከት ፣ ግራ እጁን ከደጋኑ እምብርት ላይ አኑሮ በቀኝ እጁ ቀስቱን ወጥሮ ወደርሷ ያነጣጠረ አንድ #አዳኝ ተመለከተች ።
ወደ ቀኝ ስታማትር ርሃብ ያሰከረው አንበሳ በቅርብ ርቀት ወደ እርሷ እየተጠጋ መሆኑን
አስተዋለች ። ይህች ነፍሰ ጡር አጋዘን ማድረግ የምትችለው ምንድን ነው ?

ከዚህ አጣብቂኝ ለመውጣት ምን አይነት ብልሃት መዘየድ ይጠበቅባታል ? አደገኛ ምጥ ላይ ነው ያለችው ! ልጇን በሰላም ትገላገል ይሆን ?
ነው ወይስ በእሳት የሚንቀለቀለው ደን ሁሉንም ያጠፋቸው ይሆን ? አዳኙ የወጠረው ቀስት ህይወቷን ይነጥቃት ይሆን ? ከአንበሳው መንጋጋ ውስጥ ገብታ ህይወቷ አሰቃቂ በሆነ መልኩ ይቀጠፍ ይሆን ?
.
በእሳት እየተንቀለቀለ ያለው ደን እንቅስቃሴዋን አገተው ፤ እየተወረወረ የሚፈሰው ወንዝ መራመድ እንዳትችል ገደባት ። የአንበሳው እጣ ላለመሆን መስዋዕትነት መክፈል እንዳለባት ደመ ነፍሷ ነገራት ። ከተወጠረው ቀስት መሸሽ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን አመነች ።
ልጇን በሰላም የመገላገል ጉጉቷ ቅስሟን ሰበርው

ነገር ግን ከተደቀኑባት ዘርፈ ብዙ አደጋዎች ለመዳን የሚያስችል ብልሃት አጣች ።የእርሷንም ሆነ የልጇን ውድ ህይወት በሚቀጥፉ አደጋዎች መከበቧ መላ ለመዘየድ ፋታ አሳጣት ። ታዲያ ከዚህ ሁሉ ውስብስብ ፈተና ለማምለጥ መንገዱ ምን ይሆን ???

አማራጭ እንደሌላት ስተረዳ ትኩረቷ ልጇን መገላገል ላይ ብቻ ሆነ ። ከህልፈቷ በፊት
ህይወት መስጠት የምትችልበትን እድል መጠቀም መረጠች ። ምጧ እጅግ ተፋፋመ ።
ስቃይዋ በረታ ። ሰውነቷ ተርገፈገፈ ።እግሮቿ ተለጠጡ ። በፈተናዎች ተከባ በሞት ወጥመድም ተከባ ሳለ ፈጣሪዋ ትዝ አላት #ቋንቋዋን ወደ ሚሰማ አምላክ ጮኸች፡፡ እግዚአብሔርም ተዓምራትን ገለጠ ።

መብረቁ ቀስቱን ከወጠረው አዳኙ አይኖች ላይ ተንፀባረቀ ። ቀስቱ ኢላማውን ስቶ ስጋ ካማረው አንበሳ ጉሮሮ ላይ ተሰካ ። እፎይ !

ካረገዙት ዳመናዎች የሚንቧቧ ውሃ ወረደ ። በእሳት የሚነደው ጫካ ረጠበ ። እፎይ !

ከለምለማማው መስክ ላይ አንድ ድምፅ ተሰማ ።
ጫካው አዲሱን ድምፅ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀብሎትእንደ #ገደል__ማሚቶ አስተጋባው ።
የዥረቱ ሃይል ጨመረ ።አንበሳውም ተዘረረ ።
ዳመናዎች ተቀደዱ ። የወንዙ ሙላት አዳኙን በስጋት ናጠው ። በመብረቅ ታጅቦ የሚዘንበው ዝናብ አስጨነቀው ። ጫካውን ጥሎ እግሬ አውጪኝ አለ ። ከለምለሙ መስክ ላይ የሚሰማው ቀጭን ድምፅ ማስተጋባቱን #ቀጠለ

ያ ድምፅ የወጣው እናቷ ከተፈጥሯዊ ምጥ የበለጠ አስቸጋሪ ፈተና ውስጥ መግባቷን
ሳትመለከት ውቡ መስክ ላይ ከተወለደችው ግልገል አጋዘን አንደበት ነበር #እናት የአብራኳን ክፋይ በእቅፏ አስገባች ። ጠረኗን ከልጇ ጠረን አጋባች ።

ገላዋን በፍቅር # ላሰች ። የህይወትን ሀሁ ማስተማር ጀመረች ።
⚂ ከአንበሳ መንጋጋ ልትገባ የነበረችው ሚስኪን ነፍስ በፈጣሪዋ እገዛ #አርነት ወጣች ።
በሚንቀለቀል የደን እሳት አመድ ለመሆን ቋፍ ላይ የነበረችው ነፍሰ- ጡር ነፍስ በፈጣሪዋ እርዳታ ሌላ ነፍስ ሰጠች ።
የቀስት ኢላማ ውስጥ ገብታ የነበረችው የዋህ ነፍስ በፈጣሪዋ ወሰን የለሽ ጥበብ
ታግዛ እድሜዋ ቀጠለ ።
⚂አሰፍስፈው የነበሩት አዳኞች ድምጥማጣቸው ጠፋ ።
⚂የጦርነት ቀጠና የነበረው አካባቢ የሰላም አየር ተነፈሰ ጫካው አዲስ በመጣችው ግልገል አጋዘን ድምፅ ደምቋል ። እናትና ልጅ ለዘመናት
ተጠፋፍተው የተገናኙ ይመስል በሃሴት እየተፍለቀለቁ አካባቢውን ነግሰውበታል ።
አንበሳው ከጎናቸው ተዘርሯል ። የአንበሳውን ስልጣን አጋዘኖቹ ወረሱት ።

ከዙፋኑ ላይ ተሰየሙ ። የጫካ ንግስናውን ነጠቁ ። አክሊሉን ደፉ ። ኢላማዋን ስታ ጉሮሮው
ውስጥ በተሰነቀረች ቀስት የአንበሳው ስልጣን አከተመ ። አዳኙም ሆነ አንበሳው የአጋዘኗን
ስጋ ቢጎመዡም ያልታሰበው ተከሰተ ።
በላተኞች #እርስ__በርስ ተባሉ ። እናት እና ልጅ ለምለሙ መስክ ላይ በሰላም ተንጎማለሉ

ንግስናን የሚሰጠውና የሚነሳው ፈጣሪ ነው ።
የእርሱ ስራ እንዲህ ነው ። ፈጣሪህ በጉልበታቸው ተማምነው ሊበሉህ የተነሱ አካላትን መንጋጋ ያራግፋል ። ከተራራ የገዘፈ ችግርህን ያንኮታኩታል ። ወዳንተ የሚወደሩ አጥፊ ቀስቶችን ያኮላሻል ። በራስህ አስቸጋሪ የህይወት ውጣ ውረድ ተወጥረህ በዙሪያህ ተደራራቢ ፈተናዎች ሲደቀኑብህ በጭንቀት መርገፍገፍ ሰዋዊ ባህሪ ነው ።

ቅድሚያ ለየትኛው መስጠት እንዳለብህ እስኪያቅትህ ድረስ በፈተና መዛል የማይቀር ነው ።
ከቁጥጥርህ ውጭ ያሉ ነገሮችን መጋፈጥ አስቸጋሪ ቢሆንም በቁጥጥርህ ስር ያሉትን
መጋፈጥ ግን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ።
ህይወት ከውስጥና ከውጭ በሚመነጩ ፈተናዎች የተከበበች ነች ። የምትችለውን
ከሰራህ ቀሪውን መከራ የጥበብ ባለቤት የሆነው #አንድየ እግዚአብሔሬ ጣልቃ ገብቶ ነፃ እንደሚያወጣህ ልበ ሙሉነት ይሰማህ እመን የማይታለፍ የተባለውን ችግር ያሳልፍሃል።

አስቸጋሪና ውስብስብ የተባሉ ፈተናዎችን የምናልፈው በእኛ ብርታት ሳይሆን ጥብበኛው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለሆነ ነው፡፡
የሚጠብቀን አይተኛም አያቀላፋም !
....
@የኤፍሬም እይታዎች
፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡