2022-05-20 14:54:41
ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለሴት የአሰተዳደር ሰራተኞች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጠ
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሴቶችና ህጻናት ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ለሴት የአሰተዳደር ሰራተኞች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጠ፡፡በስልጠናው በማህበራዊው፣ በኢኮኖሚው፣ በፓለቲካውና በሌሎችም ዘርፎች የሴቶች ተሳትፎ ሊጎለብት እንደሚገባው ተገልጿል።
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሴቶችና ህጻናት ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ አዲስ አስፋወሰን በስልጠናው ወቅት እንደተናገሩት ሴቶች በማህበራዊው፣ በኢኮኖሚው፣ በፓለቲካውና በሌሎችም ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት ውስን በመሆኑ ተሳትፏቸው ሊጎለብት ይገባል ብለዋል።ስልጠናው 100 ለሚሆኑ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሴት የአስተዳደር ሰራተኞች እንደተሰጠ ገልጸው ግንዛቤውን ካገኙ በኋላም ልምዶቻቸውንና ያገኙትን ተሞክሮ ለሌሎች የሚያጋሩ ይሆናል ብለዋል። አክለውም እንደዚህ አይነቱ ስልጠና ሴቶችን ለአመራርነት በማብቃት ደረጃም ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በስነ ልቦናና ስነ ማህበረሰብ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ዘነበ ደምሴ “ጀግኒትን ማጀገን” (Women Empowerment) በሚል ርዕስ የስልጠናውን ጽሁፍ በማዘጋጀት በየጊዜው ሴቶችን እያሰለጠኑ የሚገኙ ሲሆን የዛሬውን የስልጠና አላማ ሲገልጹ ጀግኒት እየገጠሟት ያሉትን ተግዳሮቶች በመለየት የጀግንነት ጉዞዋን እንድትቀጥል ማድረግ ነው ብለዋል። በተጨማሪም እውቅና እንድታገኝና የበለጠ የምትጀግንባቸውን መሰረታዊ ጉዳዮች በመለየት ማጀገን እንደሆነ ተናግረዋል።አገልግሎታቸው ለማይታወቁ ጉዳዮች ዋጋ መስጠትን፣ሲማሩ ደግሞ ጀግና ነኝ ማለትን እንዲለማመዱ እድል እንደሚፈጥርላቸውም አክለው ተናግረዋል።
ሰልጣኞቹ በበኩላቸው ከቤት ውስጥ ስራችን ጀምሮ ትልቅ ሃላፊነት ተጥሎብን ይህንን ሃላፊነት እየተወጣን ብንገኝም ጀግንነታችንን ሳንረዳ ቆይተናል ብለዋል።
ከስልጠናው በኋላም ያገኙትን ልምድና ተሞክሮ ለሌሎች በማካፈል እንደሚጠቀሙበትና በትምህርቱ፣ በጤናው፣ በማህበራዊው፣ በኢኮኖሚው፣ በሁሉም ዘርፎች ከቤት ውስጥ ሃላፊነት ጀምሮ ለጀግንነታቸው እውቅና እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
@debreberhan_university
@debreberhan_university
4.1K viewsedited 11:54