Get Mystery Box with random crypto!

ሰላም! በከተማችን አዲስ አበባ ተንሰራፍቶ የሚገኘው ሕገ-ወጥነት ያሳስብዎታል? እንደነዋሪ አንድ ነ | የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት

ሰላም!
በከተማችን አዲስ አበባ ተንሰራፍቶ የሚገኘው ሕገ-ወጥነት ያሳስብዎታል? እንደነዋሪ አንድ ነገር ማድረግ ብችል ብለው ይመኛሉ?
እነሆ የከተማ አስተዳደሩ ሕገ-ወጥነትን ለሚጠቁሙ መረጃ አቅራቢዎች የሚደረግን ማበረታቻ አስመልክቶ ደንብ ቁጥር 121/2013ን ማውጣቱን ስንገልጽልዎት በታላቅ ደስታ ነው! ይበሉ! ሕገ-ወጥነትን በመጠቆም የዜግነት ግዴታዎትን ከመወጣትዎ ባለፈ ጠቀም ያለ ማበረታቻ ያግኙ።
የጥቆማ አቀራረብ ስነ-ስርአቱም እንደሚከተለው ነው፥-
• አግባብ ባለው ተቋም የማይታወቅ ወይም ሊታወቅ ወይም ሊደረስበት የማይችል የተደበቀ ወይም የተሸፈነ ሕገ-ወጥ ድርጊትን የሚመለከት ጥቆማ ያለው ማንኛውም መረጃ አቅራቢ ጥቆማውን ለከንቲባ ጽ/ቤት በአካል፣ በቃል፣ በጽሑፍ፣ በስልክ፣ በፋክስ፣ በኢሜል ወይም አመቺ በሆነ በማናቸውም ሌሎች መንገዶች ሊያቀርብ ይችላል።
ጥቆማውም ከመረጃ አቅራቢው ሙሉ ስም እና አድራሻ በተጨማሪ የሚከተሉትን ዝርዝሮች መያዝ አለበት፥-
ሀ) ህገ-ወጥ ድርጊቱ የተፈፀመበትን ተቋም እና ድርጊቱን የፈጸመውን ሰራተኛ፣ ኃላፊ ወይም ግለሰብ ስም፤
ለ) ድርጊቱ የተፈፀመበት ቀንና ቦታ (ልዩ ቦታ)፤
ሐ) ጥቆማው የሚቀርብበት ዋናው ጉዳይ እና ደጋፊ መረጃዎች (ካለ)፤
መ) መረጃ አቅራቢው ወይም ጠቋሚው ህገ-ወጥ ድርጊት ከፈፀመው ሰው ጋር ያለው ግንኙነት፤
ሠ) በህገ-ወጥ ተግባሩ ተሳታፊ ወይም ተካፋይ ናቸው ብሎ የሚጠረጥራቸው ሰዎችን ዝርዝር መረጃ (ካለ)፤
• የከንቲባ ጽ/ቤት በዚህ አግባብ ጥቆማ ሲቀርብለት ጥቆማውን ለዚሁ አላማ በተዘጋጀው የባህር መዝገብ ላይ ይመዘግባል፤ እንደኣስፈላጊነቱም ጥቆማ የቀረበበትን ጉዳይ፣ ቀንና ጊዜ ጠቅሶ ለጠቋሚው የማረጋገጫ ደረሰኝ ይሰጣል፤ ጥቆማውንም በ48 ሰአታት ውስጥ ጉዳዩን የመመርመር ሀላፊነት ላለው ሀላፊ ማቅረብ አለበት።
• ለተመዘገበው መረጃ ማበረታቻው የሚከፈለው መረጃው አግባብ ባለው ተቋም ተመርምሮ ተጨባጭ መረጃ መሆኑ ሲረጋገጥ እና ህገ-ወጥ ተግባሩ ሲከሽፍ ወይም ንብረቱ ሲመለስ ወይም ህገ-ወጥ ተግባሩ የመጨረሻ ውሳኔ ሲያገኝ ነው።
• ሆኖም የቀረበው መረጃ ተጨባጭ መሆኑ ተረጋግጦ ሳለ በመንግስት የማስፈፀም ድክመት ምክንያት የመጨረሻ ውጤት ባይገኝም ጥቆማ አቅራቢው ማበረታቻውን የማግኘት መብት አለው።

ሰኔ 13 2014 ኣ.ም
ፋሲካ አጌና (የህ/ስ/ም/መ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ አቃቤ-ሕግ)