Get Mystery Box with random crypto!

ሰላም ለእርስዎ ይሁን! እርስዎ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን በመጠቆም የዜግነት ግዴታዎትን ከመወጣት ባለፈ | የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት

ሰላም ለእርስዎ ይሁን!
እርስዎ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን በመጠቆም የዜግነት ግዴታዎትን ከመወጣት ባለፈ ጠቀም ያለ ማበረታቻ ሊያገኙ እንደሚችሉ ያውቃሉ? ይከተሉኝማ!
በሀገራችን የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ በህገ-መንግስቱ በአንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 3 እንደሰፈረው የህዝብና የመንግስት ሀብት ሲሆን መሸጥ ወይም መለወጥ እንደማይቻል ተደንግጎ ሳለ በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ግን ሕገ-ወጥ የመሬት ይዞታና ግንባታ፣ እና የመሬት ወረራን ጨምሮ መሬት ነክ የሌብነትና የማጭበርበር ወንጀል ተስፋፍቶ ይገኛል።
በመሆኑም በከተማዋ እየተስፋፋ የመጣውን ህገ-ወጥነት ለማስቆምና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በህዝብ ተሳትፎ ወንጀሉን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር መከናወን እንዳለበት በመታመኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕገ-ወጥነትን ለሚጠቁሙ መረጃ አቅራቢዎች ስለሚሰጥ ማበረታቻ የሚደነግግ ደንብ ቁጥር 121/2013 አውጥቷል።
በቀደመው ልጥፋችን የጥቆማ አቀራረብ ስነ-ስርአቱን በአጭሩ አጋርተንዎት እንደነበር ይታወቃል። ለዛሬም ከዚህ ደንብ ላይ 3 ጥቆማ የሚቀርብባቸውን ሕገ-ወጥ ድርጊቶችና የሚያስገኙትን ማበረታቻ እናጋራዎታለን፤ ሌሎቹን በቀጣይ ልጥፎቻችንን የምንመለስባቸው ይሆናል።
ማንኛውም ሰው፥-
1. ወደ መሬት ባንክ ቢገባም ባይገባም አግባብ ያለው አካል ሳይፈቅድ ማንኛውም የከተማ መሬት መያዙን ወይም መወረሩን ከጠቆመ በተጠቆመው ይዞታ ልኬት ስፋት ልክ በወቅቱ የሊዝ መነሻ ዋጋ 10 (አስር) በመቶ ማበረታቻ ያገኛል፤
2. አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ በህጋዊነት ከተያዘ ይዞታ ጎን፣ (ከፊት ለፊቱ ወይም ከበስተ-ሗላው) ያለ የከተማ ቦታ ተስፋፍቶ መከለሉን፣ ጥቅም ላይ መዋሉን፣ መታጠሩን ወይም ከአዋሳኝ ይዞታ ጋር መቀላቀሉን ከጠቆመ ከተስፋፋው ይዞታ ልኬት ስፋት ልክ በወቅቱ የሊዝ መነሻ ዋጋ 10 (አስር) በመቶ ማበረታቻ ያገኛል፤
3. በአካባቢ ልማት ፕላን መሰረት ለመንገድ አውታር፣ ለማህበራዊ ተቋማት፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለአረንጓዴ ስፍራዎች፣ ለፓርክ፣ ለመንግስት ይዞታዎች እና ለተለያዩ አገልግሎቶች ተለይተው የተቀመጡ ባዶ ቦታዎች በህገ-ወጥ መንገድ መያዛቸውን ከጠቆመ ከተያዘው የይዞታ ልኬት ስፋት ልክ በወቅቱ የሊዝ መነሻ ዋጋ 10 (አስር) በመቶ ማበረታቻ ያገኛል፤
ሰኔ 15 2014 ኣ.ም