Get Mystery Box with random crypto!

እንዲያው ቸር ከርመዋል? ዛሬም ስለጡረታ ልናወጋዎ ተመልሰናል! ኢትዮጵያ አዳዲስ የጡረታ አዋጆች ማ | የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት

እንዲያው ቸር ከርመዋል?
ዛሬም ስለጡረታ ልናወጋዎ ተመልሰናል!
ኢትዮጵያ አዳዲስ የጡረታ አዋጆች ማውጣቷን በቀደመው መልእክታችን ላይ ሳያነቡ አልቀሩም! እንደው በገጠመኝ ካመለጥዎት እንኳን እንዲህ እናስታውስዎ!
• የመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 714/2003 እና ማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 907/2007 በመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014፤
• የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 715/2003 እና ማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 908/2007 ደግሞ በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1268/2014
ተሽረዋል፤ ተተክተዋል።
እናም ስለጡረታ ህጎች ለወደፊት ሰፋ ያለ ትንተና ይዘን እንደምንመለስ የገባነውን ቃል እዚህ ጋር እያጸናን ለዛሬ በመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 ስለጡረታ መውጫ እድሜና የአገልግሎት ጡረታ አበል የተደነገገውን በጥቂቱ እናጋራዎ!

ስለጡረታ መውጫ ዕድሜ
1/ የጡረታ መውጫ ዕድሜ፣ የመንግሥት ሠራተኛው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀጠር በቅድሚያ የመዘገበውን የልደት ዘመን መሠረት ያደረገ፣ ሲሆን ከመከላከያ ሠራዊትና ከፖሊስ አባላት በስተቀር ለሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች 60 (ስልሳ) ዓመት ነው፤
2/ የሚኒስትሮች ምክር-ቤት በጥናት ላይ ተመስርቶ በልዩ ሁኔታ ለሚታዩ የሙያ መስኮች ወይም በከባድ ወይም ለጤንነትና ለሕይወት አስጊ በሆኑ የሥራ መስኮች ላይ ለተሰማሩ የመንግሥት ሠራተኞች ከ60 (ስልሳ) አመት የበለጠ ወይም ያነሰ የጡረታ መውጫ ዕድሜ ሊወስን ይችላል፤

ስለአገልግሎት ጡረታ አበል
1/ ቢያንስ 10 (አስር) ዓመት ያገለገለ የመንግስት ሠራተኛ የጡረታ መውጫ ዕድሜው በመድረሱ ከስራ ሲሰናበት የአገልግሎት ጡረታ አበል እስከ ዕድሜ-ልክ ይከፈለዋል፤
2/ ቢያንስ 10 (አስር) ዓመት ያገለገለ የመንግስት ሠራተኛ ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በራሱ ፈቃድ አገልግሎት ካቋረጠ የጡረታ መውጫ ዕድሜው ሲደርስ የአገልግሎት ጡረታ አበል እስከ ዕድሜ-ልክ ይከፈለዋል፤
3/ ቢያንስ 25 (ሐያ-አምስት) ዓመት ያገለገለ የመንግስት ሠራተኛ ከዲስፕሊን ጉድለት በስተቀር በራሱ ፈቃድ አገልግሎት ካቋረጠ የጡረታ መውጫ ዕድሜው ሊደርስ አምስት ዓመት ከሚቀረው ጊዜ ጀምሮ እስከ ዕድሜ-ልክ የአገልግሎት ጡረታ አበል ይከፈለዋል፤
4/ ቢያንስ አንድ ሙሉ የምርጫ ዘመን ያገለገለ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊ ወይም የምክር-ቤት አባል ከኃላፊነት ሲነሳ ዕድሜው 50 (ሀምሳ) ዓመት የሞላው ከሆነ የአገልግሎት ጡረታ አበል እስከ ዕድሜ-ልክ ይከፈለዋል፤
5/ በተራ ቁጥር (2) ወይም (3) መሠረት አገልግሎት ያቋረጠ የመንግስት ሠራተኛ የጡረታ መውጫ ዕድሜው ሳይደርስ በጤና ጉድለት ምክንያት ለሥራ ብቁ አለመሆኑ ከተረጋገጠበት ጊዜ ቀጥሎ ካለው ወር ጀምሮ የአገልግሎት ጡረታ አበል እስከ ዕድሜ-ልክ ይከፈለዋል፤ የሞተ ዕንደሆነም ከሞተበት ጊዜ ቀጥሎ ካለው ወር ጀምሮ ለተተኪዎች አበል ይከፈላል፤።
6/ የመንግሥት መሥሪያ ቤቱ ህልውና በማክተሙ፣ የሰው ኃይል ብዛት ከሚፈለገው በላይ በመሆኑ ወይም ከፕራይቬታይዜሽን ጋር በተያያዘ ከሥራ እንዲሰናበት የተደረገና አገልግሎቱ ከ25 ዓመት ያላነሰና ዕድሜው ከ50 ዓመት ያላነሰ የመንግስት ሰራተኛ በሚኒስትሮች ምክር-ቤት ሲወሰን የአገልግሎት ጡረታ አበል እስከ ዕድሜ-ልክ ይከፈለዋል፤

ሰኔ 02 ቀን 2014 ኣ.ም
ፋሲካ አጌና (የህግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ)